Sunday, 06 November 2016 00:00

የዶናልድ ትራምፕ እና የሂላሪ ክሊንተን በቅሌት የጦዘ ምርጫ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

• የምርጫው ውጤት በአብዛኛው ይታወቃል።ከ48ቱ ግዛቶች መካከል፣ የ30ዎቹ ውጤት አያጠራጥርም።
• በካሊፎርኒያ፣ በኒውዮርክ... ሂላሪ ክሊንተን ያሸንፋሉ። በቴክሳስ፣ በሚዙሪ... ዶናልድ ትራምፕ ያሸንፋሉ።
• ዋናው ጥያቄ፣ የፍሎሪዳና የኦሃዮ፣የፐንስልቫንያና የኖርዝ ካሩላይና፡ የሚሺጋንና የቨርጂንያ ፉክክር ነው!
• የዘንድሮው ምርጫ ከወትሮው ይለያል።ሰሞኑን ደግሞ ብሶበታል - “የጥቅምት ዱብዳ” ይሉታል።
• የዶናልድ ትራምፕ “ሴቶችን የመጎንተል ቅሌት”፤ የሂላሪ ክሊንተን “የሙስናና የማናለብኘት ቅሌት”!
• ታሪከኛው የኤፍቢአይ ዳሬክተር ‘ጂም ኮሚ’፣ምርጫውን በዱብዳ አጡዘውታል - ባለፈው አርብ።
• ለመሆኑ፣ ምርጫው፣ ለኛ ምናችን ነው?ማናቸውም ቢያሸንፉ ብዙም ለውጥ የለውም። ነገር ግን...
• የመጪዎቹ አመታት ፖለቲካ፣ ይበልጥ እየተሳከረና ስርዓት እያጣ እንደሚሄድ ያሳያል - ጠንቀቅ ነው!


አምና፣ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻቸውን በይፋ ሲያውጁ፣ በርካታ ጋዜጠኞች በቦታው ተገኝተዋል። በርካታ ካሜራዎች ተደግነው፣ ዜናው በቀጥታ ተሰራጭቷል። ነገር ግን፣ የትራምፕን የምርጫ ዘመቻ እንደ ቁምነገር መቁጠር አይደለም። ሰውዬው፣ ትልቅ ባለሃብት ናቸው። የቢዝነስ ችሎታ ውድድር በቲቪ በማዘጋጀትም፣ በሰፊው ይታወቃሉ። በዚያ ላይ ደግሞ፣ በአወዛጋቢ ንግግር፣ በየጊዜው የአገር መነጋገሪያ ሲሆኑ ቆይተዋል። እናም፣ “የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ፣ ከዋናዎቹ ፖለቲከኞች ፉክክር ጋር፣ እንደ ማጣፈጫ እንደ ማዋዣ ሊያገለግል ይችላል” ተብሎ ነበር የታሰበው። ታዲያ ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። የትራምፕ ዘመቻ ከጥቂት ሳምንታት ሆይሆይታ ያለፈ፣ ረዥም እድሜ እንማይኖረው በእርግጠኝነት ተናግረዋል - ታዋቂዎቹ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን።
በተቃራኒው፣ የሚዲያዎቹና የአዋቂዎቹ “እርግጠኝነት”፣ በአጭር ተቀጨ። ዶናልድ ትራምፕ፣ በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ የተካሄደውን የማጣሪያ ምርጫ፣ በከፍተኛ ብልጫ በመሪነት ሲያጠናቅቁ፣ “ጉድ” ተባለ። ያው፣ እንግሊዝ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ለመቆየት ወይም ለመውጣት፣ ምርጫ የተካሄደ ጊዜም፣ ውጤቱ አለምን “ጉድ” አሰኝቷል። የአለም ፖለቲካ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ እየተለወጠና እየተሳከረ መጥቷል። በግጭቶችና በጦርነቶች የሚፈራርሱና የሚተራመሱ አገራት በርክተዋል። በመግስታት የእዳ ክምር፣ በኢኮኖሚ መዳከምና በስራ አጥነት ሳቢያ፣ የሚቃወሱ አገራትማ... በየአህጉሩ ብዙ ናቸው። በዚህ ላይ፣ የደርዘን አለማቀፍ ተቋማት ማስፈራሪያንና የእልፍ ፖለቲከኞች ስብከትን ቸል በማለት፣ አብዛኞቹ እንግሊዛዊያን ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት በምርጫ መወሰናቸው ታከለበት። ምን ይሄ ብቻ!
ዶናልድ ትራምፕ፣ ብዙዎች ባልገመቱት ‘ትንግርት’፣ ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ለመሆን መብቃታቸው ተጨመረበት። ቢሆንም ግን...
ቢሆንም ግን፣ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይዋ ከሂላሪ ክሊንተን ጋር በሚያካሂዱት ፉክክር፣ ትራምፕ የምርጫ አሸናፊ ለመሆን ቅንጣት እድል እንደማይኖራቸው... እልፍ ጊዜ በተደጋጋሚ ‘ተረጋግጧል’ - በሚዲያ ተቋማት፣ በፖለቲከኞችና በአዋቂዎች።
ከሦስት ሳምንት በፊት፣ የኤንቢሲ ዋና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ቸክ ቶድ፣ በምርጫው ሂላሪ ክሊንተን እንደሚያሸንፉ አያጠራጥርም በማለት ተናግሯል። እናም ከምርጫው በኋላ፣... ማለትም ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ከተሸነፉ በኋላ፣ በፖለቲካው አለም ይቀጥላሉ? ወይስ ወደ ነባሩ የቢዝነስ ስራቸው ይመለሳሉ? በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ነበር፣ ትንታኔው። ይሄ፣ ሌሎች በርካታ ምሁራንና ጋዜጠኞች ከሰጡት ትንታኔ የተለየ አይደለም። ዋሺንግተን ፖስት እና ሲኤንኤን የመሳሰሉ ተቋማት፣ ገና ድሮ ነው፣ የሂላሪ አሸናፊነትን ያለጥርጥር ያወጁት። ሲኤንኤን ማለት፣ “ኬብል ኒውስ ኔትዎርክ” ማለት ሳይሆን፣ “ክሊንተን ኒውስ ኔትዎርክ” ማለት እስከመባል የተደረሰው፣ አለምክንያት አይደለም።
ነገር ግን፣ ዶናልድ ትራምፕን ወደ መደገፍ ያዘነበለው ፎክስ ኒውስ ሳይቀር፣ የምርጫው አሸናፊ ሂላሪ ክሊንተን እንደሚሆኑ ነበር በዘገባዎቹ የሚጠቁመው። ለምን? ከመራጮች የሚሰበሰቡ አስተያየቶች፣ በየእለቱ እየጠኑና እየተጠናቀሩ የፉክክሩን አዝማሚያ በግልፅ ያሳያሉ። የጥናቶችን ጠቅላላ ውጤት በማስላት የሚታወቀው አርሲፒ፣ የዛሬ ሦስት ሳምንት የነበረውን መረጃ ተመልከቱ። ሂላሪ ክሊንተን 333 ለ205 በሆነ ድምፅ እንደሚያሸንፉ የያኔው ጥናቶች አሳይተዋል። ይሄ በጣም ሰፊ ልዩነት ነው። እስከ ምርጫው እለት ድረስ፣ በሦስት ሳምንት ውስጥ፣ የመራጮችን ሃሳብ ለማስቀየርና ሰፊውን ልዩነት ለማጥበብ የሚያስችል፣ ተአምረኛ ቅስቀሳ ከየት ይመጣል? ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።
ደግሞም፣ ሂላሪ ክሊንተን፣ ዶናልድ ትራምፕን በሰፊው መብለጣቸው፣ ያን ያህልም አነጋጋሪ አልሆነም። ትራምፕ፣ የፖለቲካ ልምድ የላቸውም። ሂላሪ ክሊንተን ግን፣ በፖለቲካ ነው ጥርሳቸውን የነቀሉት። ቢያንስ ቢያንስ ከወጣትነታቸው እድሜ እስካሁን ድረስ፣ ለ30 ዓመታት በፖለቲካው መድረክ የዋና ተዋናዮች ዝርዝር ጠፍተው አያውቁም። ትራምፕ፣ በዘፈቀደ ይናገራሉ። ሂላሪ ክሊንተን ግን፣ በስርዓት ከመናገር አልፈው እንደማሽን ለመሆን የተቃረቡ፣ ምራቃቸውን የዋጡ ፖለቲከኛ ናቸው።
በዚህ ላይ፣ ወደ ምርጫው እለት የሚያዳርስ የመጨረሻው ወር፣... የጥቅምት ወር... ለዶናልድ ትራምፕ፣ እንደ እሳት የሚለበልብ ወር ሆኖባቸዋል። ከ15 ዓመታት በፊት የተቀረፀ የዶናልድ ትራምፕ የዋዛ ወሬ፣ ተፈልፍሎ ተገኘ። አገሬውን አናጋው። ሴቶችን ስለመጎንተል ነበር የሚያወሩት። “የተቀረፀው ወሬ፣ የዋዛ የቀልድ ወሬ ነው” በማለት ለመከራከር የሞከሩት ዶናልድ ትራምፕ፣ “ቢሆንም ግን ይቅርታ እጠይቃለሁ” በማለት መራጮችን ለማረጋጋት ጥረዋል። ምን ዋጋ አለው? “የትራምፕ ወሬ፣ የቀልድና የዋዛ አይደለም። የምር ነው” የሚሉ ዘገባዎች፣ እንደ ጎርፍ አገር ምድሩን አጥለቀለቁት። ግማሽ ደርዘን ሴቶች፣ ከአምስት እና ከአስር ዓመት በፊት ‘በትራምፕ ተጎንትለናል’ ማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋላ። ትራምፕ አለቀላቸው! ተባለ!
የምርጫ ሰሞን ሲቃረብ፣ ፉክክሩን የሚያናጉ እንዲህ አይነት መረጃዎችና ዘገባዎችን ነው፣ “ኦክቶበር ሰርፕራይዝ” ተብለው የሚጠሩት።
ያው፣ ልትጠልቅ ተቃርባ የነበረችው የትራምፕ ፀሐይ፣ ቁልቁል አዘቀዘቀች። አንድ ሐሙስ የቀረው የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ፣ ግብአተ መሬቱ ደረሰ ተባለ። እውነትም፣ ከመራጮች የተሰበሰቡ መረጃዎችም፣ ሂላሪ ክሊንተን፣ ከትራምፕ በሰፊ ብልጫ እንደሚመሩ አሳይተዋል። ሂላሪ ክሊንተን በምርጫው እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ከመሆናቸው የተነሳ፣ እነማንን በሚኒስትርነት እንደሚሾሙ ማሰላሰልና መመልመር ጀምረው ነበር። ትራምፕ ደግሞ፣ የአገሬው የፖለቲካ ስርዓት ለነሂላሪ ክሊንተን ያደላ በማለት ማውገዝ አዘውትረው ነበር - “ፖለቲካው ተጭበርብሯል” እንደማለት ነው። ይሄማ “የተሸናፊ እፍርት ነው” ብለዋል - ሂላሪ ክሊንተን በአፀፋው።
እንግዲህ... አሸናፊና ተሸናፊ ከወዲሁ ታወቋል ቢባል ማጋነን አይሆንም ነበር።
ነገር ግን፤ ያልታሰበ ዱብዳ ድንገት ፈነዳ - ባለፈው ሳምንት አርብ። ይሄኛው የጥቅምት ዱብዳ፣ በሂላሪ ክሊንተን ላይ ነው የወረደባቸው። በእርግጥ፣ የዱብዳው ሰበብ፣ አዲስ ጣጣ አይደለም። የቆየ ጉዳይ ነው -ሂላሪ ክሊንተን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የተፈፀመ ከባድ ስህተት። የሰነድ አያያዛቸውና የመልእክት ልውውጣቸው፣ ከሌሎች ባለስልጣናት ይለያል። በመንግስት የሚመደብላቸውን ኢሜይል ትተው፣ ቤት ውስጥ ራሳቸው ባስተከሉት ዌብሳይት ነበር የሚጠቀሙት። ይሄ፣ የመንግስት መዝገብ ቤትን በመተው፣ መንግስት የማያውቀው መዝገብ ቤት እንደመክፈት ነው - ለዚያውም ሚስጥራዊ የመንግስት ሰነዶችን ጭምር ለማከማቸት።
ምርመራውን ሲያካሂድ የነበረው የአገሪቱ ፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ)፣ ሂላሪ ክሊንተን በርካታ ደንቦችን እንደጣሱ አረጋግጧል። ነገር ግን፣ ድርጊቱ የተፈፀመው፣ ሆን ተብሎ ደንቦችን ለመጣስና ሚስጥር ለማባከን እንደሆነ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘንም በማለት የተናገሩት የኤፍቢአይ ዳሬክተር ጂም ኮሚ፣ በዚህም ምክንያት ወደ ክስ ላለመሄድ በመወሰን ምርመራውን ዘግተናል ብለዋል - ሐምሌ ወር ላይ። አቤት፣ ከግራና ከቀኝ የዘነበው የድጋፍና የትችት፣ የአድናቆትና የውግዘት ብዛት! ሂላሪ ክሊንተን፣ በርካታ ጥፋቶችን መፈፀማቸው እየታወቀ፣ ከክስ ነፃ እንዲሆኑ የተደረገው በፖለቲካ አድልዎ ነው በማለት በርካታ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች ተችተዋል። በርካታ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አውራ ፖለቲከኞች ደግሞ፣ ጂም ኮሚ በቅንነት የሚሰሩ ታላቅ የሙያ ሰው ናቸው በማለት አድናቆታቸውን ያለቁጠባ ዘርግፈዋል።
ዛሬ ግን፣ ነገሩ ተገለባብጧል። ሂላሪ ክሊንተን እና በርካታ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ከሰሞኑ ጂም ኮሚን ሲያወግዙ ሰንብተዋል። ለምን?
“አዲስ መረጃ ስለተገኘ፣ በሂላሪ ክሊንተን ላይ እንደገና ምርመራ ምረናል” በማለት ጂም ኮሚ ባለፈው አርብ ባስተላለፉት መልእክት፣... ቀድሞውኑ ሲሳከር የቆየው የምርጫ ዘመቻ ይብሱኑ ቀለጠ።
አህስ? በዶናልድ ትራምፕና በሂላሪ ክሊንተን መካከል የነበረው ሰፊ የብልጫ ልዩነት፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ማሸሸ። ፉክክሩ አንገት ለአንገት ሆነ። በእርግጥ፣ ከሰላሳ በሚሆኑ ግዛቶች ውስጥ፣ የምርጫው ውጤት ምን እንደሚሆን ይታወቃል። ከእያንዳንዱ ግዛት የሚገኘው ነጥብ ይለያያል - እንደ ህዝቡ ቁጥር። በካሊፎርኒያ፣ የሂላሪ ክሊንተን ብልጫ በጣም ሰፊ ስለሆነ፣ ማሸነፋቸው አያጠራጥርም። በዚህም 55 ነጥብ ያገኛሉ። በኒውዮርክም እንዲሁ፣ ያሸንፋሉ፤ 29 ነጥብ ያስገኝላቸዋል። 20 ነጥብ በሚያስገኘው በኤለኖይ ግዛትም፣ ሂላሪ በሰፊው ያሸንፋሉ። ትራምፕ፣ በቴክሳስ ስለሚያሸንፉ፣ 38 ነጥብ ያስገኝላቸዋል። በኢንዲያና 11 ነጥብ፣ በሚዙሪ 10 ነጥብ ወዘተ።
ምርጫውን በጠቅላላ ለማሸነፍ፣ 270 ነጥብ መሰብሰብ ያስፈልጋል። ለዚህም፣ ወሳኞቹ የፉክክር ግዛቶች፣ ፍሎሪዳ፣ ኦሃዮ፣ ፐንስልቫኒያ፣ ኖርዝ ካሩላይና፣ ሚሺጋን፣ የመሳሰሉ ከአስር ገደማ ግዛቶች ናቸው። ማክሰኞ ይለይለታል።
ለመሆኑ ለኛ ምናችን ነው?
ትራምፕ ቢመረጡ፣ ምናልባት የአሜሪካ እርዳታ የተወሰነ ያህል ሊቀንስ ይችላል። ከዚያ ውጭ፣ ብዙም የሚለወጥ ነገር የሚኖር አይመስልም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ፣ ከአሜሪካ በኩል የሚሰነዘሩ አስተያየቶችም ቁጥራቸው ሊቀንስ፣ ድምፃቸው ሊደበዝዝ ይችላል።
ሂላሪ ክሊንተን ቢመረጡስ? ባራክ ኦባማ ቁጥር 2 እንደማለት ነው። ብዙም የሚለወጥ ነገር አይኖርም።
ለክፉም ለደጉም፣ ለኛ ያለነው እኛው ነን።              


Read 1415 times