Sunday, 06 November 2016 00:00

ተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት ታሸገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በፊደል ገበታ፣ አቡጊዳንና መልዕክተን ለትውልድ በማቅረብ በሚታወቁት ቀኛዝማች ተስፋ ገ/ስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ በ1910 ዓ.ም የተከፈተውና ከ300 በላይ አይነት ያላቸውን ልዩ ልዩ የህትመት ውጤቶች የሚያትመው ተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ማተሚያ ቤት ባለፈው ሰኞ ታሸገ፡፡ ማተሚያን ቤቱ ለመታሸግ ያበቃው የድርጅቱ ባለአክሲዮኖች እህትና ወንድማማቾች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ድርጅቱን ለበርካታ ጊዜ ሲመሩት የነበሩት አቶ እንዳልካቸው ተስፋ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ ላለፉት መቶ አመታት ድርሳናትን፣ ገድሎችን የቤተክርስቲያን ማስተማሪያዎችን መልካመልኮችንና ከ300 አይነት በላይ የህትመት ውጤቶችን ሲያትምና ለ93 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሮ እንደነበር የገለፁት ስራ አስኪያጁ እህትና ወንድሞቻቸው እሳቸው በሌሉበት ከስራ አስኪያጅነት አንስተው በውሸት ቃለ መሀላ ተፈራርመው በፍ/ቤት በማፅደቃቸው እንዲሁም ይህን ስራ አስኪያጁ በመቃወማቸው ፍ/ቤት ማተሚያ ቤቱን ማሸጉን አቶ እንዳልካቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
‹‹በ2007 ዓ.ም እኛ ቦርድ ሆነን ድርጅቱን በደንብ የሚመራ ብቃት ያለው ስራ አስኪያጅ ከውጭ ይቀጠር የሚል ሀሳብ ለእህትና ለወንድሞቼ አቅርቤ ነበር›› ያሉት ስራ አስኪያጁ ይህንን አባባላቸውን በሌላ በመተርጎም ስራ አስኪያጅ አልሆንም ብለሀል በቃ ውጣ ብለው ህግና ደንብን ባልተከተለ መንገድ ሌላ መሾማቸውን እንደማይቀበሉት ስብሰባውና ሹምሽሩም ሆነ ፍ/ቤት የወሰነው ውሳኔ እኔ ባልተገኘሁበትና ተጠርቼ ባልተጠየቅኩበት ሁኔታ በመሆኑ ውሳኔውን እቃወማለሁ ብለዋል፡፡
‹‹ችግሩ የስልጣን ሽኩቻም የስልጣን ጥማትም አይደለም›› ያሉት ስራ አስኪያጁ አሁን በስራ አስኪያጅነት የተመረጡ ታላቅ ወንድማቸው ጥበቡ ተስፋና ቆንጂት ተስፋ ታናሽ እህታቸው ድርጅቱን ለመምራት የስራ ልምድ የሌላቸው በመሆኑ ድርጅቱ እንዳይበተንና ታሪክ እንዳይጠፋ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አባቴ በ1992 ዓ.ም ሲሞቱ ድርጅቱን እንድመራ ሹመውኝና አደራ ብለውኝ ነበር” ያሉት ግለሰቡ አደራቸውን በመጠበቅ ድርጅቱን በአግባቡ መርተው ለዚህ ማብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ገና ይህ ችግር በመካከላችን ሲነሳ ነገሩ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ጳጳሳትን፣ ነባር ሰራተኞችንና የቅርብ የቤተሰብ አባላትን ሰብስቤ አማላጅ ልኬ ነበር›› ያሉት አቶ እንዳልካቸው እነሱ አሸፈረኝ ብለው ያለ አግባብ ከሀላፊነቴ እንድነሳ አድርገዋል ፍ/ቤቱም እኔን ሳይጠይቅ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ብያለሁ ብለዋል፡፡
ችግሩ ታውቆ ፍ/ቤት ጉዳዩን በማየት ላይ እያለ ንብረት እያሸሸና ማሽኖችን እየፈታ ነው በሚል የሀሰት ውንጀላ ለፍርድ ቤት ክስ አቅርበው ፍ/ቤቱ እኔን ጠርቶ ሳይጠይቅ ባለፈው ሰኞ መጥቶ ማተሚያ ቤቱን አሸጎታል ያሉት አቶ እንዳልካቸው በዚህ ምክንት ከ90 በላይ ሰራተኞች መፅሀፍ እየወሰዱ የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎችና በዚህ ስራ የሚተዳደሩ በርካታ ሰዎች እየተጉላሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው፡፡ አዲስ የተመረጡት የአቶ እንዳልካቸው ተስፋ ታላቅ ወንድም አቶ ጥበቡ ተስፋ ጉዳዩ በፍ/ቤት ተይዞ እየታየ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት እቆጠባለሁ ብለዋል፡፡



Read 1751 times