Sunday, 06 November 2016 00:00

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ 349.8 ሚ. ብር አተረፈ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ትርፉ በ152 በመቶ አድጓል፤ የባለአክስዮኖች የትርፍ ድርሻ 39.5 በመቶ ደርሷል
    ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው የ2015/16 የበጀት አመት ከትርፍ ግብር በፊት 349.8 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ባንኩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በበጀት አመቱ ያስመዘገበው ትርፍ ባለፈው አመት ከነበረው የ152 በመቶ ብልጫ እንዳለው የጠቆመው የባንኩ መግለጫ፣ የባንኩ ባለአክስዮኖች የትርፍ ድርሻ መጠንም ባለፈው አመት ከነበረበት 20.3 በመቶ ወደ 39.5 በመቶ ማደጉን ገልጧል፡፡
ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት አመት አሰራሩንና ቅልጥፍናውን በማሳደግና ከደንበኞቹ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት  ውጤታማ ስኬት ማስመዝገቡንና ተቀማጭ ገንዘቡም ባለፈው አመት ከነበረበት የ72.6 በመቶ እድገት በማሳየት 5.3 ቢሊዮን ብር መድረሱንም መግለጫው አስታውቋል።
ባንኩ በበጀት አመቱ የሰበሰበው የውጭ ምንዛሬ ካለፈው አመት የ88 በመቶ ብልጫ በማሳየት 130.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱም 3.8 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ አጠቃላይ ሃብቱ ካለፈው የበጀት አመት የ3 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 7.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የተከፈለ ካፒታሉ 730.6 ሚሊዮን ብር መድረሱን እንዲሁም ጠቅላላ ካፒታሉ ወደ 1.1 ቢሊዮን ብር ማደጉን መግለጫው አብራርቷል፡፡
ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በአመቱ 33 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 105 ማድረሱን የጠቆመው መግለጫው፣ የባንኩ ደንበኞች ቁጥር በበጀት አመቱ መጨረሻ 195 ሺህ 412 መድረሱንም የባንኩ መግለጫ አክሎ አስታውቋል፡፡

Read 1913 times