Sunday, 13 November 2016 00:00

9ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተከፈተ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው 9ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተከፈተ፡፡
ከትናንት በስቲያ በኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተውና እስከ ሰኞ በሚቆየው የንግድ ትርዒት ከ160 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ማለትም ከሕንድ 40፣ ከሱዳን 13፣ ከኢጣሊያ 4፣ ከቻይናና ከቱርክ አንድ አንድ የንግድ ድርጅቶች በግንባር የተሳተፉ ሲሆን ኢንዶኔዢያና ፊጂ በኤምባሲዎቻቸው ተወክለዋል፡፡
የንግድ ትርዒቱ ዓላማ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ከውጭ አቻ ድርጅቶች ጋር ማስተዋወቅና ማቀራረብ እንደሆነ የጠቀሱት የንግድ ም/ቤቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ አበበ የንግድ ትርዒቱ፣ በሽርክና ለመስራት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያደርጉና በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዕድል ሊከፍትላቸው ይችላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቢዝነስ ያመቻቻል፣ ቢዝነሱ በንግድ ይጀምርና ቀስ በቀስ ወደ ኢንቨስትመንት ይሸጋገራል ያሉት የንግድ ም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ ከዚህ የ5 ቀን የንግድ ትርዒት፣ አዳዲስ የንግድ ስምምነቶች ይፈረማሉ፣ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ሊመነጭ፣ የስትራቴጂ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡
ጠንካራ የሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ትልቅ ተስፋ ነው ያሉት የንግድ ም/ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ የእኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ደካማው የኢኮኖሚ አካል ከመሆኑም በላይ ከሌሎች አገሮች ጋር መወዳደር አቅቶት ብርቱ ችግር ውስጥ ገብቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አገሪቷ በተፈጥሮ አየር ንብረት የታደለች በመሆኑ እንደ ቡናና ሰሊጥ ያሉ በርካታ የእርሻ ውጤቶች ታመርታለች፡፡ የቡና መገኛ አገር መሆኗ ይቅርና በዓለም ቡና ኤክስፖርተሮች ዝርዝር ውስጥ ስሟ ጎልቶ አይታይም፡፡ ይህ ድክመት እያለባት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት “የኢትዮጵያን ግዙ” የሚል መርህ አንግቦ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ለ9ኛ ጊዜ ማዘጋጀቱ የአገሪቷን ገጽታ ከመገንባት፣ የአገር ውስጥ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች የባህርይ ለውጥ አድርገው ጥራት ላይ እንዲያተኩሩ የተከበረ መነሳሻ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
9ኛው የንግድ ትርዒት በክብር እንግድነት መርቀው የከፈቱት የንግድ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ናቸው፡፡

Read 1063 times