Sunday, 20 November 2016 00:00

የከበረ ስጦታ

Written by  ድርሰት፡ ኦ. ሄንሪ ትርጉም፡ ተፈራ ተክሉ
Rate this item
(1 Vote)

 አንድ ዶላር ከሰማንያ አምስት ሳንቲም፡፡ በቃ፡፡ አንድ፡ ሁለት እያለችና ከባለግሮሰሪው፣ ከአትክልት ሻጩና ከባለልኳንዳው ጋር ጉንጯ እስኪቀላና ሥሥታም እስኪያስብላት ድረስ ተከራክራ ያተረፈቻቸው ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ናቸው፡፡ ዴላ ሶሥቴ ቆጠረቻቸው፡፡ አንድ ዶላር ከሰማንያ አምስት ሳንቲም፡፡ የሚቀጥለው ቀን የገና በዓል ይከበራል። ለውድ ባለቤቷ ለጂም ስጦታ መግዛት አለባት፡፡ ያረጀው ሶፋ ላይ ዘፍ ብሎ ከማላዘን ውጭ ሊደረግ የሚችል ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ግልጽ ነበር፡፡ እና ዴላም ይህንኑ አደረገች፡፡ እስኪበቃት አነባች፡፡
ጂምና ዴላ ኒው ዮርክ ከተማ በኪራይ ቤት ውስጥ አብረው የሚኖሩ ወጣት ባለትዳሮች ናቸው፡፡ እጅግ ሲበዛ ድሆች ሲሆኑ በቅርቡም የጂም የሳምንት ገቢ የነበረው 30 ዶላር ወደ 20 ዶላር ዝቅ ብሏል። የቤት ኪራይ ከተከፈለና አስቤዛ ከተገዛዛ በኋላ ምንም ገንዘብ አይተርፋቸውም ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ ፍቅር የሞላበት የድህነት ጎጆ ውስጥ ጂምና ዴላ የሚኮሩባቸው ሁለት ንብረቶች አሉ፡፡ አንዱ የጂም አባትና አያት ንብረት የነበረው ማሰሪያው ከቆዳ የተሰራ የወርቅ ሰዓት ነው፡፡ ሌላው እንደ ቡናማ ጅረት ወገቧን አቋርጦ ጉልበቷ ድረስ የሚወርደው የዴላ ረዥም ጸጉር ነው፡፡
ከሶፋው ስትነሳ ትንሽ እንደ ማዞር ሲያደርጋት ባለችበት ለደቂቃ ቀጥ ብላ ቆመች፡፡ ከዚያም ቡናማውን ጃኬቷን ደርባ፣ ቡናማውን ኮፍያዋን አድርጋ ሽር ብትን እያለች ደረጃዎቹን ወርዳ መንገድ ጀመረች፡፡ ጥቂት እንደተጓዘች ዐይኖቿ አንድ ምልክት ላይ አረፉ፡፡ “ሁሉም አይነት የጸጉር ምርቶች ይገኛሉ!” ይላል፡፡
እየተጣደፈች ገባች፡፡ ትንፋሿ ቁርጥ ቁርጥ ሲልባት ራሷን ለማረጋጋት ሞከረች፡፡
“ጸጉሬን ልትገዥው ትችያለሽ?” ዴላ ጠየቀች፡፡
“እገዛዋለሁ” አለች፤ ግዙፏ የሱቁ ባለቤት “ኮፍያሽን አውልቂውና ምን እንደሚመስል እንየው”
ኮፍያዋን ስታወልቅ ጸጉሯ ዘፍ ብሎ ወረደ፡፡
“ሃያ ዶላር” አለች ባለሱቋ፤ ልምድ ባካበቱት እጆች የተንዘረፈፈውን ጸጉር እየነካካች፡፡
“በፍጥነት ስጭኝ” አለች ዴላ፡፡
የጂምን ስጦታ ፍለጋ የሚቀጥሉትን ሁለት ሰዓታት ፉት አደረጋቸው፡፡ በመጨረሻ አገኘችው። ለጂም ተብሎ የተሰራ ነው የሚመስለው፡፡ ከሰዓቱ ጋር የሚሄድ የፕላቲነም ሰንሰለት ነው፡፡ ይህንን ሰንሰለት በዚያ ሰዓት ላይ አስሮ ከማንም ጋር ቢሆን ሰዓቱን ለማየት ፍላጎቱ ይጨምራል፡፡ ሃያ አንድ ዶላር አስከፈሏት፡፡ ሰማንያ አምስት ሳንቲሟን ይዛ በፍጥነት ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
ቤት ገብታ መስታወቱ ፊት ለፊት ቆማ አፈጠጠች፡፡ ጸጉሯን አርባ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሸልተው፣ ከትምህርት ቤት እየሾለከ የሚወጣ ሮጦ ያልጠገበ ልጅ አስመስለዋታል፡፡
“ጂም ምን ይለኝ ይሆን? ግን ሌላ ምን ላደርግ እችል ነበር- አህ! በአንድ ዶላር ከሰማንያ አምስት ሳንቲም ምን ላደርግ እችል ነበር?”
ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን ቡና አፍልታ፣ የከተፈችውን ሥጋ ለመጥበስ መጥበሻውን ምድጃው  ላይ ጣደችው፡፡ ጂም አምሽቶ አያውቅም፡፡ ዴላ በሩ ጥግ ካለው ጠረጴዛ ጎን ባለችው ወንበር ላይ ተቀመጠች፡፡ ከዚያም የጂም ኮቴ ደረጃዎቹን አቆራርጦ ጆሮዋ ውስጥ ሲገባ ለቅጽበት ገረጣች። ሁሌም በየቀኑ ለሚያጋጥሟት ጥቃቅን ነገሮች የአርምሞ ጸሎት የማድረግ ልማድ አለባትና አሁንም እንዲህ ስትል አንሾካሾከች፤ “እባክህ ፈጣሪ፤ አሁንም ቆንጆ እንደሆንኩ እንዲያስብ አድርገው”
ጂም እንደገባ በሩን ዘግቶ ባለበት እንደቆመ ቀረ፡፡ ዴላ ላይ ተተክለው የቀሩት ዐይኖቹ ውስጥ ልታነበው ያልቻለችው አንዳች ነገር አለ፡፡ ፍርሃት ተሰማት፡፡ ንዴት አይደለም፣ መደነቅም አይደለም፣ ተቃውሞም አይደለም፣ ድንጋጤም አይደለም ወይም ሌሎች ስትጠብቃቸው የነበሩት ስሜቶች አይደሉም። ፊቱ ያንን እንግዳ የሆነ ገጽታ እንደተላበሰ፣ ዐይኖቹ እሷ ላይ አፍጥጠው ቀርተዋል፡፡
ዴላ ጠረጴዛውን ቀስ ብላ አልፋ ወደሱ ሄደች፡፡
“ጂም የኔ ውድ፤” አለች በመለማመጥ፤ “እባክህ እንደዛ አትየኝ፡፡ ጸጉሬን ቆርጬ የሸጥኩበት ምክንያት የገና ስጦታ ሳልሰጥህ በዓሉን ማሳለፍ ስለማልችል ነው፡፡ እንደገና ያድጋል እኮ - ቅር አይልህም አይደል፤ ይልሃል? ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ጸጉሬ በፍጥነት ነው የሚያድገው፡፡ ጂም፤ ‘መልካም የገና በዓል!’ በልና ደስ ይበለን፡፡ እንዴት ጥሩ- እንዴት የሚያምር፣፡ ምርጥ ስጦታ እንዳገኘሁልህ አላወቅክም፡፡”
“ጸጉርሽን ተቆረጥሽው?” ጂም እንደምንም ታግሎ ጠየቀ፤ ከብዙ ማውጣት ማውረድ በኋላም እውነታውን ማመን ያቃተው በሚመስል መልክ፡፡
“ቆርጬ ሸጥኩት” አለች ዴላ፤ “አሁን አትወደኝም ማለት ነው፤ ምንስ ቢሆን? እኔ ያለ ጸጉሬም እኔ ነኝ፤ አይደለሁም?”
ጂም በጉጉት ክፍሉን ቃኘው፡፡     
“ጸጉርሽ የለም እያልሽ ነው?” አለ ድንዝዝ እንዳለ።
“መፈለግ አያስፈለግህም” አለች ዴላ፤ “ተሽጧል፤ እየነገርኩህ ነው- ተሽጧል፣ ሄዷልም፡፡ የገና ዋዜማ ነው፡፡ መልካም ሁንልኝ፤ የሄደው ላንተ ስለሆነ። ምናልባት ጭንቅላቴ ላይ ያሉ ጸጉሮቼ ሊቆጠሩ ይችሉ ነበር” ጥፍጥ በሚል ድንገተኛ ኮስታራነት ቀጠለች፡ “ነገር ግን ላንተ ያለኝን ፍቅር ማንም፣ መቼም ሊቆጥረው አይችልም፡፡ የከተፍኳቸውን ሥጋዎች መጥበሻ ላይ ላድርጋቸው፤ ጂም?”
ጂም ከቁም ቅዠቱ እንደምንም ነቃ፡፡ የሱን ዴላ እቅፍቅፍ አደረጋት፡፡ በሳምንት ስምንት ዶላር ወይም በዓመት አንድ ሚሊየን- ልዩነቱ ምንድን ነው? ሒሳብ አዋቂ ወይም ሊቅ የተሳሳተ መልስ ይሰጣችኋል፡፡ ሰብአ ሰገል ኢየሱስ በግርግም በተወለደ ጊዜ ውድ የሆኑ ስጦታዎች ይዘዉ መጡ፤ ያ ግን በእነ ጂምና ዴላ መሃል አልነበረም፡፡ ይህ ጥልመት ማስረገጫ በኋላ ብሩህ ይሆናል፡፡
ጂም ከካፖርቱ ውስጥ ጥቅል ነገር አውጥቶ ጠረጴዛው ላይ ጣለው፡፡
“ምንም አይነት ስሕተት አትስሪ፤ ዴል” አለ፤ “ስለኔ፡፡ ምንም አይነት የጸጉር ቁርጥ ወይም አለጫጨት ወይም ሻምፑ፤ ለዉድ ባለቤቴ ያለኝን ፍቅር እንድቀንስ ሊያደርግ የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ያንን ጥቅል ብትፈችው ግን መጀመሪያ ላይ ለምን እንደዛ እንደሆንኩ ትረጃለሽ”
በቀልጣፋና ነጫጭ ጣቶቿ ሲባጎውንና ወረቀቱን በጣጠሰቻቸው፡፡ ከዚያም በደስታ ስካር ጩኸቷን ለቀቀችው፡፡
ያው፤ ማበጠሪያዎቹ ተጋድመዋል - ጎን ለጎን ተደረድረው- ብሮድዌይ በሚገኝ ሱቅ ውስጥ በመስኮት የምትመለከታቸውና ለረዥም ጊዜ ታመልካቸው የነበሩ አንድ ላይ የሚሸጡ ማበጠሪያዎች፡፡ ውብ ማበጠሪያዎች፣ ከንጹህ የኤሊ ቅርፊት የተሰሩ፣ ጫፎቻቸው የተለያዩ ጌጣጌጦች የተደረጉባቸው፡፡ ውድ ማበጠሪያዎች እንደነበሩ ታውቃለች፤ እና የራሷ የማድረግ ተስፋዋ የመነመነ ቢሆንም በልቧ እጅግ ትመኛቸውና ትጓጓላቸው ነበር፡፡ ታዲያ አሁን የራሷ ሆነው ነበር፤ ነገር ግን እነዚህ ውድ ማስጌጫዎች የሚያርፉበት ያ ረዥም የተዘናፈለ ጸጉር የለም፡፡
ሆኖም  በደረቷ እቅፍ አድርጋቸው፣ ከአንገቷ ቀና ብላ፣ በቦዙ ዐይኖችና ፈገግታን እንደተላበሰች፤ “ጸጉሬ በፍጥነት ነው የሚያድገው፤ ጂም!” አለች፡፡ ከዚያ እንደገና አነባች፡፡
ጂም የሚያምረውን ስጦታውን እስካሁን አላየውም፡፡ መዳፏ ላይ አድርጋው በጉጉት ወደሱ እጇን ዘረጋች፡፡ ደብዛዛው ውድ ብረት የሷ ብሩህና ጠንካራ መንፈስ ሲያርፍበት አንፀባረቀ፡፡
“ዘናጭ አይደለም፤ ጂም? ከተማውን በሙሉ አስሼ ነው ያገኘሁት፡፡ አሁን ሰዓቱ ስንት እንደሆነ ለማወቅ በቀን መቶ ጊዜ ማየት ይኖርብሃል፡፡ ሰዓትክን ስጠኝ፡፡ በዚህ ሰንሰለት ምን እንደሚመስል ማየት እፈልጋለሁ፡፡”
ጂም በመታዘዝ ፋንታ እጆቹን የኋላ ጭንቅላቱ ላይ አድርጎ ሶፋው ላይ ዘፍ ብሎ ፈገግ አለ፡፡
“ዴል፤” አለ፤ “የገና ስጦታዎቻችንን ለጥቂት ጊዜ ገለል አድርገን እናስቀምጣቸው፡፡ አሁን ላይ ልንጠቀምባቸው የማንችላቸው እጅግ ድንቅ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ማበጠሪያዎችሽን ለመግዛት ስል ሰዓቱን ሽጨዋለሁ፡፡ አሁን የከተፍሻቸውን ስጋች  መጥበሻ ላይ አድርጊያቸው፡፡”
ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች)፤ እንደምታውቁት፣ በግርግም ለተወለደው ሕጻን ስጦታ ያመጡ ብልሆች ነበሩ፡፡ ለገና ስጦታዎችን የመስጠት ጥበብን የፈጠሩት እነሱ ናቸው፡፡ ብልህነታቸውን ስጦታዎቻቸውም ያመላክታሉ፡፡
(The Gift of the Maji
ከተሰኘው ድርሰቱ የተተረጎመ)

Read 1408 times