Sunday, 27 November 2016 00:00

የካዛኪስታን ዋና ከተማ በፕሬዚዳንቱ ስም ልትጠራ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የካዛኪስታን ርዕሰ መዲና አስታና ስያሜ እንዲቀየርና ከተማዋ በ76 አመቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኑርሱልጣን ናዛርባየቭ ስም እንድትጠራ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ በፓርላማ መውጣቱን ሮይተርስ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡ፓርላማው ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን በቅጡ በመምራት ላደገሩት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት በማሰብ ከተማዋን በስማቸው ለማስጠራት ያቀረበው እቅድ ስኬታማ የሚሆን ከሆነ፣ ወትሮም የግል ዝና በማካበት ሲታሙ የኖሩትንና ላለፉት 27 አመታት አገሪቱን ያስተዳደሩትን ፕሬዚዳንቱን የባሰ ሀሜትና ትዝብት ይጥላቸዋል ተብሏል፡፡የአገሪቱ ርዕሰ መዲና አስታና የሚለውን ስያሜ ላለፉት 18 አመታት ስትጠራበት እንደቆየችና ቃሉበካዛክ ቋንቋ ዋና ከተማ የሚል ትርጉም እንዳለው ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱ ፓርላማው ያቀረበውን የስያሜ ለውጥ እቅድ በተመለከተ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ምላሻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የፕሬዚዳንት ናዛርባየቭንፎቶ ግራፍ በመገበያያ ገንዘብ ላይ እንደሚያትምና ገንዘቡ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ በስራ ላይ እንደሚውል ባለፈው ሳምንት ማስታወቁንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

Read 1245 times