Monday, 12 December 2016 12:10

የሙያና ብዙኃን ማህበራት ሚናቸውን እየተወጡ ነው?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• በመልካም አስተዳደር---በዲሞክራሲ ግንባታ----በግልጽነት---??
• መንግስትስ እንዲጠናከሩ በምን በኩል ደገፋቸው?
   የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እንዲስፋፉና ተልዕኳቸውን በሕግ መሰረት እንዲወጡ ብሎም አሰራራቸው ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ኤጀንሲው በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 31 የተደነገገውን የዜጎች የመደራጀት መብት እውን ለማድረግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን መዝግቦ ፈቃድ በመስጠት ዘርፈ ብዙ የክትትልና ድጋፍ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ማህበራት በሀገራቸው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ የመሳተፍ እድል አግኝተዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሙያና የብዙኃን ማህበራት ተደራጅተው ፍቃድ በመውሰድ በሀገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳ አብዛኞቹ ማህበራት ተመዝግበው መንቀሳቀስ የጀመሩት በቅርብ ዓመታት ቢሆኑም ከተመሰረቱ ግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ማህበራትም አሉ፡፡ ሆኖም እንደ ቁጥራቸው ብዛትና እንደ እድሜያቸው ልክ የሙያ ማህበራት በሀገሪቷ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ የሙያም ሆኑ የብዙሃን ማህበራት የህዝብን ጥያቄ በተደራጀ መልኩ እያቀረቡ እንዲፈቱ ለማስቻል፣ በመንግስትና በህብረተሰቡ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ አይደለም። በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ተመዝግበው ፍቃድ የወሰዱ በጥቅሉ 333 ገደማ የሚሆኑ የሙያና የብዙኃን ማህበራት ቢኖሩም የረባ ስራ ሰርተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም በጥቅሉ ሁሉም ማህበራት ለተቋቋሙለት ዓላማ በተገቢው መልኩ አስተዋፅኦ አላበረከቱም ማለታችን አይደለም። ለዓብነት የሚጠቀሱ ስኬታማ ስራ መስራት የቻሉ ማህበራት መኖራቸው አይካድም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ያሉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ማህበራት መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡  
አብዛኞቹ የሙያና ብዙኃን ማህበራት የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ እንቅፋት የሆነባቸው ሀገሪቱ በዘርፉ የምትከተለው ህግ መሆኑን በአፅንኦት ይገልፃሉ፡፡ ለምሳሌ የ10/90 ህግ፣ ማህበራት የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ ሀገር እንዳያገኙ በማድረጉ ለመዳከማቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይናገራሉ። ሆኖም ህገ-መንግስቱ በደነገገው መሰረት፣ በማህበር የመደራጀት መብት የተሰጠው ለዜጎች ብቻ ነው፡፡ በአዋጅ 621/2001 መሠረት፣ የኢትዮጵያ ማህበራት ፍቃድ ወስደው ለመስራት ሁሉም አባላት ኢትዮጵያዊ መሆን ይኖርባቸዋል እንዲሁም የገቢ ምንጫቸው ከሀገር ውስጥ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም በህግ ከተፈቀደው ውጪ ከውጭ የገንዘብ ምንጭ መጠቀም አይቻልም፡፡ የሙያና ብዙሃን ማህበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰሩ በመሆናቸው፣ እንደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሰፊ የሀብት መጠን ላያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ 90 ከመቶ የሚሆነውን ሀብት ከሀገር ውስጥ በማመንጨት እንዲሁም 10 ከመቶ የማይበልጠውን ከውጭ ሀገር በማምጣት ከሰሩ የተቋቋሙለትን አላማ ከዳር ማድረስ ይችላሉ፡፡ ማህበራት የአባላትን መብትና ጥቅም ለማስከበር የውጭ እርዳታ ሳያስፈልግ በሀገር ውስጥ ሀብት መስራት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በሀገራችን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ማህበራት የ10/90 ህግ ውጤታማ ላለመሆናቸው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ህግ ሲወጣ ማህበራት ሀብት የማግኘት አቅማቸው እንዳይዳከም ብዙ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለዓብነት ያህል ማህበራት ከተቋቋሙለት ዓላማ ጋር ግንኙነት ባላቸው ብሎም ዓላማቸውን ለማስፈፀም ብቻ የሚውል የተለያዩ ገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ የንግድ ህግ ጠብቀው ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ መሰማራት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው ህዝባዊ መዋጮ በማካሄድ ከሀገር ውስጥ ሀብት ማመንጨት ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ አማራጮችን ተጠቅመው ከጥገኝነትና ከተመፅዋችነት አመለካከት ተላቀው፣ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ስለሚችሉ የ10/90 ህግ አላሰራንም ማለት ምክንያት ማብዛትና ከህግ አንፃርም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ፣ ማህበራት ቆም ብለው ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ህልውናቸው የሚወሰነው እራሳቸውን ለማጠናከር በሚሰሩት ስራ ነው፡፡
ይህ ሲባል የብዙሃንና የሙያ ማህበራት ምንም ተግዳሮቶች የሉባቸውም ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ስራ መስሪያ ቢሮ የላቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለስራቸው ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የማግኘት ችግር አለባቸው፡፡ በየዘርፉ ያሉ የመንግስት ተቋማት ለሙያና ብዙሃን ማህበራት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ የሙያ ማህበራትም ለአባላት ስልጠና እና የትምህርት እድልን ከማመቻቸት ባለፈ ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፣ ለፖሊሲና ስትራቴጂዎች ግብዓት የሚሆኑ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማቅረብ እንዲሁም መንግስትን በማማከር ለሀገሪቷ አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ማህበራት የጎላ አስተዋፅኦ አድርገዋል ማለት አይቻልም፡፡ በቀጣይ በመስኩ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ፣ የሙያ ማህበራት በየዘርፋቸው ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት ጋር የጠበቀ ቁርኝት ፈጥረው፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እጅና ጓንት ሆነው መፍታት አለባቸው፡፡ የሙያ ማህበራት ውጤታማ የሚሆኑት ያላቸውን እምቅ እውቀትና ክህሎት ሳይሰስቱ ለሀገራቸው ማበርከት ሲችሉ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት፣ እነዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እንዲጠናከሩ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፈንድ (Social Accountability fund) ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርበታል፡፡   
የሙያና ብዙሃን ማህበራት በራሳቸው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተምሳሌት መሆን መቻል አለባቸው፡፡ የአባላትን መብትና ጥቅም በማስከበር፣ በጠቅላላ ጉባኤ መሪዎችን መምረጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲፈቱ ማድረግ፣ ያልተመለሱ መብቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለሱ አባላትን በማለማመድ እንደ ሀገር በሚደረገው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መነሻና ትምህርት ቤት መሆን አለባቸው፡፡ የአንዳንድ ማህበራት የስራ ኃላፊዎች የጊዜ ሰሌዳቸውን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የስራ አፈፃፀማቸውን አያቀርቡም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ አመታት ስልጣናቸውን ለሌሎች አባላት ሳይለቁ የሚቆዩበት ሁኔታ አግባብነት የለውም፡፡ የመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው መሰረት በየሁለት ዓመቱ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎችን በማካሄድ፣ ስልጣናቸውን አዲስ ለሚመረጡ ሌሎች አባላት አሳልፈው መስጠት አለባቸው፡፡ የማህበራት አመራር አባላቱን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እያወያዩ፣ ዜጎች የጠራ አመለካከት ይዘው ለልማት እንዲነሳሱ የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ የሙያና ብዙሃን ማህበራት የሀገሪቷ አይን፣ ጆሮና አፍ መሆን አለባቸው፡፡ ማህበራቱ ሰፊ ቁጥር ያላቸው አባላትን ከመያዛቸው አንጻር ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው የጠራ ግንዛቤ፣ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላል፡፡
የሙያና ብዙኃን ማህበራት ውስጣዊ አሰራርም ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው  መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ አሰራር ሊጎለብት የሚችለው፡፡ ማህበራት በሀገሪቷ የፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር ረገድ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ አቅም ሲፈጥሩ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሙያም ሆኑ ብዙኃን ማህበራት በጉልህ የሚታይ ነገር አልሰሩም፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የብዙኃን ማህበራት ገዢው ፓርቲ ያቋቋማቸውና ለሱ በመወገን የፖለቲካ ስራ እንደሚሰሩ አድርገው የሚቆጥሩ አካላት አሉ። ነገር ግን የሙያና ብዙኃን ማህበራት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ሆነው በገለልተኝነት ለዜጎች እኩል የሚሰሩ ናቸው፡፡ ህጉም ይህንኑ ነው የሚደነግገው፡፡ በሌላ መልኩ የሙያና ብዙኃን ማህበራት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ነቅሰው በማውጣት እንዲፈቱ ጫና እየፈጠሩ አይደለም፡፡ በእርግጥ ማህበራት ይህንን እንዲያደርጉ መንግስት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ አልደረሱም። ምንም እንኳን ሁሉንም ማህበራት የሚገልፅ ባይሆንም ማህበራት የሙያ ብቃት ባላቸው ግለሰቦች እየተመሩ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ማህበራት ስልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ሽኩቻ በመጠመዳቸው፣ ትርጉም ባለው መልኩ ሀገራዊ ራዕይ አንግበው ሙያውን ለማሳደግ እየሰሩ አይደለም። ይህም በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርጓል፡፡  
የሙያም ሆኑ ብዙኃን ማህበራት በስነ-ምግባር የታነፁና በእውቀት የበለፀጉ፣ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡ የአባላትን አቅም በመገንባት ዙሪያ ብዙም የተሰራ ስራ የለም፡፡ ማህበራት በተጨባጭ አባላትን ማፍራትና አቅም መገንባት መቻል አለባቸው፡፡ ማህበራት ሲጠናከሩ የአባላትን መብትና ጥቅም ማስከበር ይችላሉ፡፡ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጠናከር የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥረት ማድረግ አለባቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን ማህበራት እንቅስቃሴያቸው በበጎ ፍቃደኞች እንዲደገፍ ለማስቻል፣ የበጎ ፍቃደኝነት ባህል እንዲዳብር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በሀገሪቱ የሚገኙ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ትኩረት ሰጥተው የሙያና ብዙኃን ማህበራትን የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም ያሉባቸው ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሰፊው መስራት አለባቸው፡፡ ሚዲያዎች በዘርፉ ያሉ ድክመቶችን ለመፍታት የሚያስችል ጥልቅ እይታና አቅጣጫ አመላካች የመፍትሄ ሀሳቦችን መስጠት መቻል አለባቸው፡፡
የሙያ ስነ-ምግባርና ብቃትን ከማሳደግ አንፃር የሙያ ማህበራት ብዙ ርቀት መጓዝ ቢኖርባቸውም ስንዝር እንኳን መራመድ አልቻሉም፡፡ ተዝቆ የማያልቅ ትልቅ አቅም ቢኖራቸውም፣ ከስብሰባ የዘለለ ትርጉም ያለው ስራ ለመስራት ለማከናወን  የቁርጠኝነት ማነስ እንዳለባቸው ይጠቀሳል፡፡ ይሄን ድክመታቸውን ማሻሻል አለባቸው፡፡ ነገር ግን ለማህበራት ተገቢውን እገዛ ሳያደርጉ በድፍኑ መውቀስም ተገቢ አይሆንም። ስለዚህ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ለሙያና ብዙኃን ማህበራት ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ የብዙኃንና የሙያ ማህበራት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ ቀምሮ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ውስጥም ሆነ ያደጉ ሀገራት ተሞክሮዎችን ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስፋፋት፣ ለነገ የማይባል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ሊሆን ይገባል:: እንደ ሀገር የሙያም ሆኑ የብዙኃን ማህበራት፣ በዜጎች መብት ነክ ጉዳዮችና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፍ የሚያስችላቸው አሰራር መዘርጋት አለበት እንላለን፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ
ኢሜይል አድራሻ - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 1626 times