Monday, 12 December 2016 12:18

ነፍሱ በዳንስ ፍቅር የከነፈችው ጥበበኛ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 • በ1.5 ሚ.ብር የዳንስ ፊልም ሰርቶ ሊያስመርቅ ነው
                    • የዳንስ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው የማየት ህልም አለው
                    • ”ዳንስ ለእኔ የአንድ አገር የውስጥ ባንዲራ ነው”
     ዳንሰኛና አሰልጣኝ ልጅ ተመስገን መለሰ፤ በዳንስ ፍቅር የወደቀው ገና በለጋ እድሜው መሆኑን ይናገራል፡፡ በቤተሰቡ ዘንድ በበዓላት ወቅት መጨፈር የተለመደ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከቤቱ ውጭ ዳንስን መስራትና መለማመድ የጀመረው ተወልዶ ባደገበት ሽሮሜዳ እንደሆነ የሚናገረው ተመስገን፤ በ12 ዓመቱ በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ውስጥ ከሰፈሩ ልጆች ጋር የመሥራት እድል እንደገጠመው ያስታውሳል፡፡ ይኸም በሙያው እንዲገፋበት
አድርጎታል፡፡ ከራሱም አልፎ “የተመስገን ልጆች” የሚል የዳንስ ቡድን አቋቁሞ ከፍተኛ ተቀባይነትና እውቅናን ለማግኘት እንደበቃ ይናገራል፡፡ ለባህልና ለዳንስ ልዩ ፍቅር እንዳለውና ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈለ የሚገልጸው ዳንሰኛ፤ በቅርቡ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ‹‹መቅረዝ›› የተሰኘ የዳንስና የሙዚቃ ፊልም ሰርቶ ሊያስመርቅ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ የዳንስ ጥበበኛው ተመስገን መለሰ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር አዲስ
በሰራው ፊልምና በዳንስ ህይወቱ ዙሪያ አውግተዋል፡፡

     ከቀበሌ ወደ ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ስትገባ፣ ከዳንስ በተጨማሪ ሌሎች ነገሮችንም ትሰራ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ በምን በምን ጉዳዮች ላይ ትሳተፍ ነበር?
ዳንስ የጀመርኩት ቤት ውስጥ ነው፤ በልጅነታችን የምናውቃቸው አቡ ገብሬ የተባሉ ሙዚቀኛና ሰለሞን መንግስቴ የተባለ የፊልምና የቴአትር ተዋናይ ነበር፡፡ እነሱን ስናይ ሙዚቀኛም የፊልም ተዋናይም መሆን እየተመኘን ነው ያደግነው፡፡ ወደ ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ስገባ ዳንሰኛም ተዋናይም ነው የሆንኩት፡፡ ለምሳሌ ‹‹ትንሹ ሙዚቀኛ›› የተሰኘ የፋሲል ሽመልስ ድራማ ላይ እተውን ነበር፡፡ በህፃናት ቴአትር በርካታ ነገሮችን የማየትና የመስራት እድል ገጥሞኛል፡፡
በፕሮፌሽናል ደረጀ ዳንስ መደነስና ስራህን ለታዳሚ ማቅረብ የጀመርከው መቼና የት ነው?
ለእኔ ትልቁ ፕሮፌሽናል መድረኬና ት/ቤቴ ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ነው፡፡ በልጅነቴ ነው ፕሮፌሽናል የዳንስ ስራዎች ለእይታ ማቅረብ የጀመርኩት፡፡ በዚያ እድሜዬ ከብዙዎች ጋር የመገናኘትና የመስራት እድል ገጥሞኛል፡፡ ሀገር ፍቅርም ገብቼ ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹የተመስገን ልጆች›› የተሰኘውን የዳንስ ቡድን አቋቋምኩ፡፡  
‹‹የተመስገን ልጆች››ን ያቋቋምከው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነው፡፡ በምን አላማ ነው ያቋቋምከው?
አላማው እኔ ራሴ ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር እያለሁ ያለኝ የዳንስ ብቃትና እውቀት አለ፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ያንን ብቃታችንን በትክክል እየተጠቀምንበት ነው ወይ የሚለው ሀሳብ ነው። በእርግጥ በብቃታችን መድረስ የምንችልበት ደረጃ ደርሰናል? ብዬ ሁሌ ራሴን ስጠይቅ መልስ አላገኝም፡፡ ስለዚህ እኔ በልጅነቴ መድረስ ፈልጌና ተመኝቼ ያልደረስኩባቸውን፣ እኔ አግዣቸው ለምን አያገኙም በማለት ቡድኑን አቋቋምኩ፡፡ በልጆች ትልቅ ትርኢትና ስራ መስራት እንደሚቻል የገባኝ እኔ ራሴ ህፃናት ቴአትር በነበርኩበት ወቅት ነው፡፡ እዚያ እያለን የነበረን አቅም ትልቅ ነበር፡፡ በእርግጥ ቴአትር ቤቱ እንደ መንግስት መስሪያ ቤትነቱ የራሱ መዋቅርና አሰራር አለው፡፡ ያ እንዳለ ሆኖ እኛ በዚያ እድሜያችን ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መቆም እንደምንችል፣ ያንን እኔ ባላገኘውም በስሬ በዳንስ በምፈጥራቸው ልጆች ያንን ማድረግ እንደምችል ለማሳየት ነው ቡድኑን ያቋቋምኩት። ያን ጊዜ ቡድኑ ሲቋቋም 37 ህፃናትና ታዳጊዎች ይዤ ነበር፤ አሁን ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ ህፃናትን አሰልጥኜ በተለያዩ ትልልቅ አገራዊ ሁነቶች ላይ እየተጠራን፣ ትልልቅ ስራዎችን በመስራት ትልልቅ ክፍያዎችን እያገኘን ነው። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አገራችንን ሊጎበኙ ሲመጡ በትልቅ የዳንስ ትርኢት  የተቀበልናቸው እኛ ነን፤ አብረውን ጨፍረዋል፡፡
የዳንስ ዩኒቨርስቲ ይቋቋምልን የሚል ጥያቄ ማቅረባችሁን ሰምቻለሁ፡፡ ተሳሳትኩ?
ትክክል ነው፡፡ ይህን ጥያቄ በይፋ አቅርበናል። ፕሮጀክት ቀርፀን ለሚመለከታቸው በአዳራሽ ውስጥ ስናቀርብ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካዩን ልኳል። ሆኖም ምንም መልስ የለም። እኔ እንደማስበው ለተመስገን ልጆች መልስ መስጠት ለአገርና ለተተኪዎች መልስ መስጠት ነው፡፡ በመንግስት በኩል ያለው ነገር ደክሞኝ ስልችቶኝ ትቼዋለሁ፡፡
ዳንስ የራሱ ሳይንስና ፍልስፍና አለው ይባላል፡፡ ዳንስ ለአንተ ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር ዳንስ ካልሺውም በላይ ነው። አሁን እኔና አንቺ ቆመን በምናወራበት በዚህ ሰአት ተወርቶ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ አንድ ልነግርሽ የምፈልገው ነገር ግን “ዳንስ ምንድን ነው? ምን ምን ነገሮችን ይይዛል? ዳንሰኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?” በሚሉትና በአጠቃላይ በዚህ ጥበብ ዙሪያ የሚያጠነጥን መፅሀፍ እየፃፍኩ ነው፡፡ ላንተ ምንድ ነው? ላልሺኝ፣ ዳንስ የአንድ አገር የውስጥ ባንዲራ ነው፡፡ አናየውምና አናስተውለውም እንጂ የባህላችንና የባንዲራችን ቅጂ ለእኔ ዳንስ ነው። መፅሐፌ ላይ አንድ ነገር ብያለሁ፤ ‹‹አንድ አገር ባህል ከማይኖረው ባንዲራ ባይኖረው ይሻላል››
እንዴት ማለት?
ምክንያቱም የባንዲራ ሳይንስ የተፈጠረው ከባህል በኋላ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ የባህል ሳይንስ መቼ ተፈጠረ የሚለውን የሚያውቅ የለም፡፡
ቃለ-ምልልሱን ከመጀመራችን በፊት ዳንስ በማይክሮ ሰከንድ ውስጥ ብዙ ማሰብን የሚጠይቅና ሰውነትን ለብዙ አደጋ የሚያጋልጥ ጥበብ መሆኑን ነግረኸኛል፡፡ እስከ ዛሬ ዳንስ እየደነስክ አደጋ ደርሶብህ ያውቃል?
ብዙ ጊዜ ደርሶብኝ ያውቃል፤ ትከሻዬ ወላልቆ ያውቃል፤ እጆቼ እግሮቼ ተሰብረው ያውቃሉ። በቅርቡም ‹‹መቅረዝ›› ፊልም ቀረፃ ላይ እያለሁ፣ የቀኝ እግሬ አጥንት የመሰንጠቅ አደጋ ደርሶበታል። የነርቭ በሽተኛ የሆነ ዳንሰኛ በመካከላችን ይገኛል። እስካሁን እግሩ ውስጥ ብረት ገብቶለት የሚደንስ ልጅ አለ፡፡ ብዙ ጉዳትና አደጋ ይደርሳል፡፡ በነገራችን ላይ ፊልሙ ታይቶ ከሚገኘው ገቢ 10 በመቶው ለጓደኛችን የነርቭ ህክምና ይውላል፡፡ እንዲህ አይነት አደጋዎች ሲደርሱብን የምንታከመው በራሳችን ተሯሩጠን፣ ገንዘብ አሰባስበን እንጂ የሚደግፈን አካል የለም፡፡ ነፃ ህክምናና በየወሩ የጤና ሁኔታዎችንን የምናይበት ዕድል ያስፈልገናል እላለሁ፡፡ እነዚህ ተወዛዋዦች ይነስም ይብዛም የአገር ምልክት፣ የቀጣዩ ትውልድ ድልድይና የባህል አምባሳደሮች ነን፡፡ ይህን ስናገር በልበ ሙሉነት ነው፡፡ ይህን የሚከራከር አለ ብዬም አላምንም፡፡ ከአንድ ወይም ከሁለት ብሄር ልንፈጠር እንችላለን፤ እኛ የምንደንሰው የመላው ኢትዮጵያን  ዳንስ፣ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ዳንስ ነው። የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ዳንስ ስንደንስ በስሜትና በደስታ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሥራ ላይ ስንጎዳ፣ ድጋፍና የህክምና ክትትል በነፃ ልናገኝ ይገባል፡፡
በተመስገን ልጆች ውስጥ ሰልጥነው ዝነኛ የሆኑ አሉ?
ብዙ አሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የኛ›› ከተሰኘው የአምስት ሴቶች ሙዚቀኞች መካከል ራሄል የተባለችዋ የተመስገን ልጆች ውስጥ ነበረች። “ቤቶች” ድራማ ላይ በዛብህን ወክሎ የሚጫወተው ልጅ ከእኔ የወጣ ነው፡፡ ናይት ክለብ ተቀጥረው የሚሰሩ፣ ዱባይ ቱርክና ሌሎችም አገሮች ሄደው እየሰሩ የሚገኙ አሉ። ‹‹ጃ ቤዛ›› እና ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የተሰኙትና ባለፈው የ”ባላገሩ አይዶል” ላይ ያሸነፉት የዳንስ ቡድኖች፣ በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ እኔ ያሰለጠንኳቸው አምስትና ስድስት ልጆች አሉ፡፡
እነሱን ሳይ የድካሜን ዋጋ ደሞዜን እያገኘሁ ነው እላለሁ፤ ደስታ ይሰማኛል። በነገራችን ላይ በዘጠኝ አመት ውስጥ ይህን ሁሉ ሰው ሳሰለጥን ከማንም ምንም አይነት ክፍያ ጠይቄም አግኝቼም አላውቅም፤ አገልግሎቱን በነፃ ነበር ስሰጥ የነበረው፡፡ አሁን ከቡድኖቼ ጋር በምንሰራው ስራ ግን ከፍተኛ ክፍያዎችን እያገኘን ነው፤እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
አሁን ደግሞ ፊትህን ወደ ፊልም አዙረሃል፡፡ “መቅረዝ” የተሰኘ ፊልም ሰርተሃል----
እንደምታዪው ሰው ፊልም ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ፊልም የማየት ልምድ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ማህበረሰቡ እስካሁን ለዳንስ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው፡፡ ዳንሱን ብቻውን ከምናቀርብ እውነተኛ ታሪኮች ላይ ተመስርተን ለምን በፊልም አናቀርብምና ህብረተሰቡ ለዳንስ ያለውን አመለካከት ከፍ አናደርገውም በሚል ዳንስና ፊልምን አያይዘን መጥተናል፡፡ ከእኔ ፊልም በፊት ‹‹ፍቅርና ዳንስ››፣ “ጢባጥቤ” እና “ፍሪደም” የተሰኙ ሶስት ብቻ የዳንስ ፊልሞች ተሰርተዋል። በፍቅርና በሌላ በሌላ ጉዳይ የተሰሩ ፊልሞች ግን የትየለሌ ናቸው፡፡ ይህ ለዳንስ ጥበብ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ስለዚህ የዳንስ ፊልም ስሰራ እኔ አራተኛ ነኝ፡፡
በዚህ ፊልም ዳንሰኛው ምን ያህል ፈተና እንደተጋፈጠ፣ በምን አይነት ችግር ውስጥ እንደሚያልፍ፣ ከህብረተሰቡ የሚገጥመው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ ባህልና ዳንስን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ዳንሰኛው የሚያደርገውን ተጋድሎ ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡ እግረ መንገዳችንንም የኛ ሙያ ለዚህ አገር ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑንን እያዝናናን ለማሳየት ጥረናል።  
ፊልሙን ለመስራት ስምንት አመት ፈጅቷል ልበል?
እውነት ለመናር እኔ ፀሀፊ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ሀሳቡን መፃፍ የጀመርኩት የተመስገን ልጆችን ካቋቋምኩ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡ መጀመሪያ ፃፍኩት፤ እንደገና በስክሪፕት መልክ ስፅፍ አንዱን ስጥል አንዱን ሳነሳ፣ ይሄው ስምንት አመት ፈጀ፡፡ ሌላው ፕሮዱዩሰር ፍለጋ ባዘንን፤ አንድም ፕሮዱዩሰር ማግኘት አልቻልንም፡፡
አሁን ማን ፕሮዱዩስ አደረገው ታዲያ?
“ሬና ፊልም ፕሮዳክሽን” - የተመስገን ልጆች እህት ኩባንያን ነው፤ ለዚህ ፊልም ስል ነው ያቋቋምኩት፡፡ ሬና ባይቋቋም ሀሳቤ ተዳፍኖ ይቀር ነበር፡፡ ሬና ፊልም ፕሮዳክሽን ስለተቋቋመ ብቻም አይደለም ፊልሙ እውን የሆነው፡፡ የብዙ ሙያተኞች ምክር፣በገንዘብ የማይለካ ድጋፍም ጭምር ነው ህልሜን እውን ያደረገው፡፡
የፊልም ዳይሬክተርም ለማግኘት ተቸግራችሁ ነበር እንዴ?
እውነት ነው የብዙ የዳይሬክተሮች በር አንኳኩተናል፣ የሰው ፊት አይተናል፡፡ መጨረሻ ላይ ቅንና ትሁት ሆኖ፣ የስራችን አላማና ግብ ገብቶትና ነክቶት የተቀበለን ዳይሬክተር ዳግማዊ ፈይሳ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ። ከዚህ በፊት የተሰሩት የዳንስ ፊልሞች አንድ ሀሳብ ይዘው በመነሳት የተሰሩ ናቸው። የእኛ ለየት የሚለው የአገር ሀሳብ፣ የአገርን ውክልና የያዘ ሰፊ ሀሳብ ያለው ነው። ሁሉንም ለመወከልና ታሪኩን ለማዳበር ብዙ ተዋናይ፣ ብዙ ባለሙያ ተጠቅመናል፡፡ ነገር ግን ዳንስ ላይ ያለው አመለካከት አናሳ በነበረበት ሰዓት እነ ብርሃኔ ንጉሴ፣ እነ ቅድስት ይልማን የመሳሰሉት ባለሙያዎች ዳንስን መሰረት ያደረገ ፊልም በመስራት ፈር ቀዳጅ መሆናቸው እኛንም አነቃቅቶናል፤ ግብአትም ሆነውናል፤ እናመሰግናቸዋለን፡፡ እኛ የውስጥ ህመማችንን፣ ቃጠሏችንን ለማሳየት ነው የተነሳነው። ይህ የሁሉም የኢትዮጵያ ዳንሰኞች ታሪክ ነው፡፡ ወደ ራሳችን ወደ ባህላችን ለመመለስና ከባህል ወረራ ነፃ ለመውጣት የሚረዳ ሥራ ነው - ፊልማችን፡፡
ፊልሙ 1.5 ሚ ብር ፈጅቷል ተብሏል፡፡ በአወጣኸው መጠን አገኛለሁ ብለህ ታስባለህ?
በእርግጠኝነት ህዝቡ ካየው ይወደዋል። የሰራንበት አላማም ይገባዋል፡፡ ገቢ ቢገባም ባይገባም ግድ የለኝም፤ ዋናው አላማዬ ሀሳቤ ህዝብ ጋ ደርሶ ማየት ነው፡፡
የወደፊት ህልምህ ምንድ ነው?
ዳንስ ሳይበረዝና ሳይከለስ፣ ማንነቱን ጠብቆ ሲቀጥል ማየት፣ የመጀመሪያውና የመጀመሪያው ምኞቴ ነው፡፡
ቀጥሎ የዳንስ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተው፣ ዳንስ እንደ ማንኛውም ሙያ ተከብሮ፣ ፍላጎት ያላቸው በድግሪና ከዚያም በላይ ደረጃ ሲማሩ ማየትም ትልቁ ምኞቴ ነው፡፡
በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ባሉበት ትልልቅ ሾዎች ማቅረብ ቢለመድ ደስ ይለኛል፡፡ ብቻ ምኞቴ ብዙ ነው፤ ጊዜ ቢወስድም ይሳካል ብዬ አስባለሁ፡፡

Read 2356 times