Monday, 12 December 2016 12:33

‹‹Hotel and Painting›› በራዲሰን ብሉ ለእይታ ቀረበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ሆቴሎችን ያለመ አውደ ርዕይ ይዘጋጃል

      በአፍሪካ አርት ጋለሪ ሰዓሊያን ቡድን የተሳሉ 90 ያህል ስዕሎች የተካተቱበት አውደ ርዕይ ባለፈው ሳምንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል ለዕይታ የቀረበ ሲሆን አውደ ርዕዩ የትላልቅ ሆቴል ባለቤቶችን ትኩረት እንደሳበ ተጠቆመ፡፡
የ11 ሰዓሊያን ሥራዎች በቀረቡበት ‹‹Hotel and Painting›› የተሰኘ የስእል አውደ ርዕይ ላይ ኢትዮጵያውያን የሆቴል ባለቤቶችም ታድመው የነበረ ሲሆን ስዕሎቹም ለትላልቅ ሆቴሎች ታልመው የተሰሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ አውደ ርዕዩ በተከፈተበት ዕለት ከቀረቡት ስዕሎች መካከል 40 ያህሉን የሆቴል ባለቤቶች ገዝተውታል ተብሏል፡፡ የአፍሪካ አርት ጋለሪ ሰዓሊያን ሁለት ቡድኖች እንዳሉት የጠቆመው የሰዓሊያኑ ተወካይ ሰዓሊ አምደአብ በቀለ፤አንዱ ቡድን ለሆቴል የሚሆኑ ስዕሎችን የሚሰራ፣ የሆቴሎች የውስጥ ማስጌጥ ዲዛይን ላይ የተሰማራና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነ አብራርቷል፡፡ የአገራችን ባለሆቴሎች ለሆቴሎቻቸው የሚሆኑ ስዕሎችን ከውጭ አገራት በውድ ዋጋ ገዝተው ያመጡ እንደነበር የገለጸው ሰዓሊው፤አሁን በኢትዮጵያውያን ሰዓሊያን በአገር ውስጥ የሚሰሩ የሥዕል ሥራዎችን  መግዛት መጀመራቸውን ጠቁሞ፣ ይሄም ለዘርፉ አበረታች ነው ብሏል፡፡   
በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡትን ስዕሎች ከገዙት መካከል በቅርቡ በሃዋሳ የሚከፈተው ባለአራት ኮከብ ‹‹አልታ ላንድ ሆቴል›› ባለቤቶች ይገኙበታል። አፍሪካ አርት ጋለሪ ሌሎች የሆቴል ባለቤቶችም በአገራቸው በተሰሩ ስዕሎች ሆቴሎቻቸውን እንዲያሳምሩ ተመሳሳይ አውደ ርዕዮችን ለማዘጋጀትና ስዕሎችን በትዕዛዝ ለመስራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡  

Read 1741 times