Monday, 12 December 2016 12:37

ኢራን በኒውክሌር ስምምነት ጉዳይ አሜሪካን አስጠነቀቀች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ትራምፕ ስምምነቱን እንዲያፈርሱ አልፈቅድም ብላለች

        ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቡትን የኒውክሌር ስምምነት የማፍረስ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አገራቸው እንደማትፈቅድላቸው  የገለጹት የኢራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ፤ ትራምፕ ስምምነቱን የሚያፈርሱ ከሆነ ግን የከፋ ነገር እንደሚከሰት ማስጠንቀቃቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኒዩክሌር ስምምነቱን በመጣስ አሜሪካ በኢራን ላይ ከጣለቻቸው ማዕቀቦች አንዳንዶቹ ለ10 አመታት እንዲራዘሙ የሚፈቅደውን ህግ በፊርማቸው የሚያጸድቁ ከሆነ፣ አገራቸው ምላሽ እንደምትሰጥና ይህም አሜሪካን አላስፈላጊ ዋጋ እንደሚያስከፍላትም ሩሃኒ አስጠንቅቀዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አገራቸው ከፈረመቻቸው አደገኛና አክሳሪ ስምምነቶች መካከል፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2015 ከኢራን ጋር የተፈጸመው የኒውክሌር ስምምነት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፣ ስልጣን ከያዙ ለውጥ የሚያደርጉበት አንደኛው ጉዳይ ይህ ስምምነት እንደሆነ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንት ሩሃኒ ግን ባለፈው ማክሰኞ ባደረጉት ንግግር ትራምፕ ስምምነቱን ለማፍረስ ከሞከሩ፣ መንግስታቸውና ህዝባቸው በዝምታ እንደማይመለከቱ አስጠንቅቀዋል፡፡
“አሜሪካ ጠላታችን መሆኗ አንዳች እንኳን የማያጠራጥር ሃቅ ነው፣ በቻለቺው አቅም ሁሉ በእኛ ላይ ጫና ለማሳደር ትፈልጋለች” ያሉት ፕሬዚዳንት ሩሃኒ፤ ሰውዬው ወደ ስልጣን ሲመጡ የተለያዩ የለውጥ ተግባራትን የመፈጸም ፍላጎት አላቸው፣ ያም ሆኖ ግን ትራምፕ ከሚወስዱት እርምጃ ኢራንን ተጎጂ የሚያደርግ አንድ እንኳን አይኖርም ብለዋል በቴህራን ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር፡፡ ኢራን ለአለማቀፍ ሰላም ስጋት አይደለቺም፣ አለም በእኛ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ያደረገው የአሜሪካና የእስራኤል ፕሮፓጋንዳ ነው ብለዋል- ፕሬዚዳንት ሩሃኒ፡፡
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ ከአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ሩስያና ጀርመን ጋር በ2015 ስምምነት መፈጸሟ ይታወሳል፡፡

Read 1948 times