Saturday, 31 December 2016 11:06

ባለቤቱን በስለት የገደለው፣ በ20 ዓመት እስራት ተቀጣ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

  “ሰድበኸኛል” በሚል ወጣቱን በጥይት የገደለው፣ 18 ዓመት ተፈርዶበታል

      የ22 ዓመት የትዳር ጓደኛውንና የ3 ልጆቹን እናት፣ በቅናት መንፈስ ተነሳስቶ በስለት አንገቷን ቀልቶ የገደለው ግለሰብ፤  የ20 ዓመት የእስራት ቅጣት ተወሰነበት፡፡
ተከሳሽ ጎሹ አካባት ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ገደማ፣ በድሬደዋ ከተማ ቀበሌ 02 ልዩ ቦታው ጎሮ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው፣ በቅናት ምክንያት የተፈጠረን ፀብ ተከትሎ፣ በቢላዋ የባለቤቱን እጅ ሁለት ጊዜ ሲወጋት፣ ሮጣ ለማምለጥ ስትሞክር የበሩ ደፍ አደናቅፏት ትወድቅና ጀርባዋ ላይ በመቀመጥ፣ በቢላዋ አንገቷን በመቅላት በዘግናኝ ሁኔታ ነፍሷን እንዳጠፋ ከድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ም/ኮማንደር ገመቹ ካቻ አስረድተዋል፡፡
ሟች በድሬደዋና በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ የንግድ ስራዎችን ለመስራት ጥረት በምታደርግበት ወቅት፣ ‹‹ከወንድ ጋር ቆመሽ አወራሽ፣ ለምን ትጋበዣለሽ›› በሚል በየጊዜው ፀብ ይፈጥር እንደነበር የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል በዚህም ተደጋጋሚ ፀብ ምክንያት ተከሳሹ ትዳሩን ትቶ፣ ወደ ትውልድ ሀገሩ ሰሜን ጎንደር በመሄድ፣ በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም ሌላ ሚስት ይዞ፣ ወደ ድሬደዋ በመመለስ፣ ከተማ ዝንጆሮ ገደል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አዲሷን ሚስቱን ቤት ተከራይቶ ያስቀመጣት ሲሆን ሟች ይህን ተግባሩን ስትሠማ፤ ‹‹አንድ አይደለም ሌላም ደግሞ ቢያገባ ግድ አይሰጠኝም›› ብላ በመናገሯ ፀቡ መክረሩን የፖሊስ ምርመራ  ይገልፃል፡፡
በመጨረሻም ተከሳሽ ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም፤ ሟች አሮጌ ልባሽ ጨርቆችን እምትሸጥበት ቦታ በመሄድ መቆፈሪያ፣ ሸራና ማዳበሪያ እንድትሠጠው ሲጠይቅ፤ እቃዎቹ የሌሉ መሆኑን ትነግረዋለች፡፡ ‹‹ከሰጠሸው ወንድ መልሰሽ ታመጫለሽ›› የሚል ዛቻ ከተናገረ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቷ ስትመለስ ጠብቆ ተከትሎ በመሄድ፣ የወንጀል ድርጊቱን እንደፈፀመ ም/ኮማንደር ገመቹ ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱ በእናቷ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስትጥር የነበረችውን የ20 ዓመቷን ልጃቸውን ገፍትሮ እንድትወጣ ማድረጉንና ልጅቷም የይድረሱልኝ ጥሪ በማሰማቷ፣ ወንጀል ፈፃሚው ወዲያውኑ በአካባቢው ህዝብ እጅ ከፍንጅ መያዙም ታውቋል፡፡ ፖሊስ ከአቃቤ ህግ ጋር በመተባበር የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን አሰባስበው በመሰረቱት ክስ ከትናንት በስቲያ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በተከሳሽ ላይ በ20 አመት እስር  እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በዚያው በድሬዳዋ ከተማ ‹‹ሰድቦኛል›› በማለት ወጣቱን በክላሽንኮቭ መሳሪያ ተኩሶ የገደለው ግለሰብ፤ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን ም/ኮማንደር ገመቹ ካቻ አስታውቀዋል፡፡
ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ.ም በድሬደዋ ከተማ መብራት ኃይል አካባቢ በሚገኝ የቀበሌ መዝናኛ ክበብ ውስጥ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታን ለመከታተል የታደመው የ20 ዓመቱ ወጣት ውብሸት ተስፋሁን “ሰድቦኛል” በሚል የማይረባ ምክንያት ህይወቱን በጥይት አጥፍቷል፡፡
ገዳይ ክላሺንኮቭ መሳሪያውን ታጥቆ ሟች ወደነበረበት መዝናኛ ክበብ በማምራት፣ ከክበቡ ሲወጣ ጠብቆት ተኩሶ በመግደል፣ ከአካባቢው ቢሰወርም፣ ከተሸሸገበት ደብረዘይት ከተማ በፖሊስ ክትትል መያዙ ተገልጿል፡፡
ፖሊስ ምርመራ ካጣራ በኋላ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ፣ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡  

Read 1702 times