Wednesday, 25 January 2017 07:45

ሰውኛ ባሕሪያት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(3 votes)

 የዚህ ዓምድ ትኩረት ሥነ-ጥበብ፡ በዋነኝነትም የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ነው። በተለይም ዘመንኛው (Contemporary) የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ላይ አጽንኦት በመስጠት ወቅታዊና በመታየት ላይ ያሉ ትርዒቶችን ይዳስሳል፡ ገለጻ ያቀርባል፡ ያትታል፡ ይመረምራል፡ ሂስ ያቀ ርባል። ግለሰቡን ሳይሆን ስራውን በመተቸት የሂስ ባሕልን ለማዳበር ይጥራል፡፡ የዓምደኛውን እይታ መሬት በያዙና ሚዛን በሚደፉ አመክንዮች በማስደገፍ፣ ግለሰብ አንባቢ ስለ ሥነ-ጥበብና ስለ ኢትዮጵያ ሥነ- ጥበብ ግንዛቤ እንዲጨብጥ፡ የዕይታ ባሕሉ(Visual Culture) እንዲዳብር፡ የሥነ-ጥበብ አድናቆቱ ከፍ እንዲል፡ ሥነ-ጥበብን የሕይወት ዘዬው (Life Style) አድርጎ እንዲወስደው መንገድ ለመክፈት ይጥራል። በማኅበረሰብና በሃገር ደረጃም ልክ እንደ ኤኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊ፡ ማኅበራዊ፡ ባሕላዊና ትውፊታዊ እንዲሁም ታሪካዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሥነ-ጥበብን የሰፊው የሕይወት መር(Mainstream) አካል እንዲሆን ይተጋል።

                   ሰውኛ ባሕሪያት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ
                               በሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)

        ላለፉት አምስት ወራት የጠፋሁት ስለ ሃገራችን ሥነ-ጥበብ በጋዜጣ እንድጽፍ የሚኮረኩረኝ ርዕሰ-ነገር አጥቼም ብቻ አይደለም፡፡ ከግንቦት 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ጋዜጣ የዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ላይ ትኩረት አድርገው በተከታታይነት ሳቀርባቸው የነበሩ ጽሁፎችን አስፈላጊነት ውድቅ የሚያደርግ ክስተት በመላው ሃገሪቱ ሲከሰት፤ አይደለም ጽሑፍ ማቅረብ ማቆም፣ ጽሑፍ አቀርብ እንደነበረም የሚያስት ዝንጋኤ ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ ባቀረብኳቸው ጽሑፎችና ዳሰሳዎች ውስጥ በሚሰሩት ስራ ላይ በዝርዝር ሂሳዊ ትችት ያቀረብኩባቸው አካላት ፍጹም ስርዓት በጎደለው መልኩ የሰነዘሩብኝን ጸያፍ ዝልፊያ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ የምታውቁ አንዳንድ አንባቢዎቼ፣ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮብኝ ጭልጥ ብዬ እንድጠፋ ያደረገኝ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ለመጥፋቴ ምክንያቱ ሁለት መሆኑን እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አንደኛው ሥነ-ጥበብ ሰላም በሌለበት መገኘት የማትችል በመሆኑ፣ የሃገራችን ጸጥታና ሰላም በደፈረሰበት ወቅት የጀመረኝ የዝንጋኤ መንፈስ ገና ከሰሞኑ ብቻ ይለቀኝ መጀመሩ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ እንደ ማንኛውም ተመስጦ የሚያሻው ስራ፣ ስለ ሥነ-ጥበብ እንድጽፍ የሚያነሳሳኝ ዋንጫ ጎዶሎ ብቻ ሳይሆን ባዶ ሆኖብኝ፣ ጽዋዬ እስኪሞላ መጠበቅ ስለነበረብኝ ነው፡፡ እነሆ ለመነቃቂያ እውነቱንና ሃቅ ሃቁን በመነጋገር ብንጀምርስ? ብያለሁ፡፡
የሃቅ ትርጉም እውነት ብቻ ሳይሆን እውነታው እውን እንዲሆን ያስቻሉ ምክንያቶችን ንጽሕና በሚያላብስ መንፈስ የሚገልጥ እሳቤ ያዘለ ቃል ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ሰው የኔ የሚለው፣ ሌላው ሊጋራው የሚችለውም ሆነ የማይችለው እውነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሃቅ ግን የኔ፣ ያንተ፣ የሱ.... ወዘተ ብሎ ነገር የለውም፡ ሃቅ ‘ሃቅ’ ነውና። ዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እያስተናገደ ያለው የእውነታ ስፋትና ጥልቀት በግልጽ ተመርምሮ ካልታወቀለት፣ የእውነታው ሃቅ መሃል ሲንገዋለልና ሲንከራተት፣ በጊዜና በድግግሞሽ ሂደት ያዳበራቸው ሰውኛ ባሕሪያት ቁልጭ ብለው፣ ዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እንደ የአንድ ሃገር ወሳኝ ዘርፍ ሳይሆን እንደ ሰው እየታየና እየተኖረ ይመስለኛል፡፡ እኔ ያየኋቸው የወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ሰውኛ ባሕሪያትን ስለ እውነታውና ስለ ሃቁ እየነካካሁ እጠቃቅሳለሁ፡፡ እውነታውን ከሃቁ በመለየት የመመራመሩን ሚና ግን ለናንተው ትቸዋለሁ፡፡
1. ዓይን-አፋርነት፡ በሰውኛ ባሕሪ ዓይን-አፋርነት እጅግ የሚወደድ ውስጣዊ ውበትን ለመደበቅ ከመሞከር የሚመጣ ባሕሪ ይመስለኛል። ዓይን-አፋርነት ያለንን አስደሳችና ጠቃሚ ነገር ይፋ ለማውጣት የሚያስችሉ መንገዶችን ካለማወቅ የሚመነጭም ይሆናል፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ዓይን-አፋርነትም በዚሁ መንገድ የመጣ ሆኖ፣ ትንሽ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ‘ያጨቅኩትን ሁሉ ብዘረግፍ ይህ ያገሬ ሰው ምን ይለኝ ይሆን? ከቶስ ይረዳኝ ይሆን?’ የሚል ይሉኝታ ይዞት ቁጭ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ ደፈር ያሉ ሠዓሊያን ስራቸውን ለሕዝብ ባቀረቡ ቁጥር የተሰራውን ስራ ለመረዳት ጥረት የማድረግ የቤት ስራውን የማይወጣ ተመልካች፣ ‘ሥዕል አይገባኝም’ እያለ ለመመራመርና ለመጠየቅ ራሱን ሳያዘጋጅ፣ ትርዒቱን ተመልክቶ ሳይሆን የዓይን ሻወር ወስዶ እልም የሚል ተመልካች በተደጋጋሚ ካሰለቸው በኋላ በሚፈጠር ዓይን-አፋርነት የተወለደ አፋርነት ነው የሚመስለው። ሆኖም የወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ አይን-አፋርነት፣ ወደ ዓይን-አውጣነት የሚቀየርባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡ ገንዘባቸውን፣ የሚወዱትን የሥነ-ጥበብ ስራ ለመግዛትና ፍላጎታቸውን ለማርካት ሳይሆን የገዢነታቸውን አቅም ለማሳየት ብቻ ውድ ለተባለ ሥዕል ገንዘብ እያፈሰሱ ለሚመጻደቁ ደካሞች፣ አይን-አውጣ ሆኖም ገንዘብ የሚያጭድ ባሕሪም አዳብሯል - የወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ፡፡ እኒህ አይነቶቹ ‘ገዢዎች’፣ ሥነ-ጥበብን ለመገንዘብ ያዳበሩት እውቀት አነስተኛ በመሆኑ፣ ውሳኔያቸው በገንዘባቸው አቅም ላይ ይመሰረታል፡፡ ሆኖም ግን ሥነ-ጥበብን የመገንዘብ አቅማቸው እየዳበረ የመምጣት እድል ሲኖራቸው፣ ባለማወቅ ያፈሰሱት ንዋይ የራሳቸው ውሳኔ መሆኑን ዘንግተው፣ ሥነ-ጥበብን በመደገፍ ፈንታ ቁርሾ እንዲያተርፉ የማድረግ አደጋ ማስከትል መቻሉ ሌላኛው የወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ዓይን-አፋርነት እያፈራ ያለው ጽንፍ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ሃቅና እውነቱን የመለየት ፋንታ፣ የእርስዎ የውድና ነቄ አንባቢ ድርሻ መሆኑን አይዘንጉ!
2. ስሱነት፡ የሥነ-ጥበብን ፋይዳ የመረዳትም ሆነ የኑሮ አቅማችን ከልከኛው በታች የወረደ  በተለይ  እንደ ሃገራችን ባሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ በሥነ-ጥበብ ሙያ ማለፍ በራሱ እሳት በወርቅ እንደሚፈተነው አይነት ክብደት አለው፡፡ ይህም የአብዛኛውን የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ጉዞ አስቸጋሪና በውጣ ውረድ የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በስኬት ጎዳና የሚጓዝ ማንኛውም ሰው፤ ፈተናዎችን ማለፍ የግድ ቢሆንበትም በተለይ በሃገራችን ሥነ-ጥበብ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ሠዓልያንም ሆኑ ባለሙያዎች ፈተናዎቻቸው ጠንካራ፣ ታጋሽና ቻይ እንዲሆኑ ሳይሆን ይበልጡኑ ስስ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ነው የሚመስለው፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት የሚመስለኝ ደግሞ ለራስና ለሚሰሩት ስራ የተጋነነ ፍቅር (EGO) ማዳበር ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ለራስም ሆነ ለሚሰራው ስራ ፍቅር የሌለው ከያኒ፣ ለሙያው ፍቅር ይኖረዋል ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም የEGO መዳበር፣ የአትንኩኝነት ባሕሪን እየፈጠረ፣ በወቅታዊው ሥነ-ጥበባችን ላይ እያመላከተ ያለውን የስሱነት ሰውኛ ባሕሪ አስከትሏል ባይ ነኝ፡፡ ይህ በበኩሉ ደግሞ ለሥነ-ጥበባዊ ትችት፣ ሂስና ውይይት ጆሮን ዳባ የማልበስ አሳዛኝ ባሕሪ በሥነ-ጥበብ ማኅበረሰባችን ውስጥ እንደ ካንሰር እንዲሰራጭ አድርጓል፡፡ ስለ መፍትሄው ለመነጋገር በቅድሚያ ይህ ባሕሪ መገራት ያለበት ስለሚመስለኝ፣ ወደ ቀጣዩ ነጥብ ብሻገር እመርጣለሁ፡፡
3. ጥገኝነትና ጥግ-ገኝነት፡ ዘመናዊውና ዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ  የተጓዘባቸውንና እየተጓዘባቸው ያሉ መንገዶች መዋቅር ሲጤን ከመሰረቱ እስከ ምሰሶው፣ ግድግዳና ወጋግራው ጭምር ተናባቢነት የሌለው የተውገረገረ መዋቅር ነው የሚያሳየው፡፡ ብቸኛው ጠንካራ መሰረት የሠዓልያን ሙያዊ ክሂሎት ነው፡፡ በስተቀር ከመንግስት እስከ አቅም ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ድረስ ሥነ-ጥበብን በመዋቅር ደረጃ የማካተት ክፍተት በግልጽ ይታያል፡፡ ሥነ-ጥበብን በመደበኛ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተትም ሆነ በከፍተኛ ትምህርት ስርዓት ውስጥ የማስፋፋት ስራ ባለመሰራቱ፣ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተለይም ሠዓልያን ጫናው እንዲያርፍባቸው ግድ ሆኗል፡፡ በዚህም ሊረዳና ድጋፍ ሊያደርግ ወደሚችል አካል ዘንበል ማለትና ጥገኝነት የመጠየቅ ግዴታ ውስጥ የገባ ሥነ-ጥበብ እንዲኖረን ሆኗል፡፡ ጥገኝነቱ ደግሞ በከተማችን የሚኖሩ ፈረንጆችና የሚያስተዳድሯቸው ተቋማት ላይ ሲሆን የጥግ-ገኝነቱ አይነት ግን የተለያየ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ከዚህም አንጻር የአመለካከት ጥግ-ገኝነት፣ ምንም ያክል የተድበሰበሰና መንግስት ራሱ ጥገኝነቱን የማይፈልገው ቢመስልም የመንግስት ጥግ-ገኝነት፣ የኤኮኖሚያዊ ጥቅማ ጥቅሞች ጥገኝነት፣ የርዕዮተ-ዓለም ወይም ideology ጥግ-ገኝነት የተወሰኑት ናቸው፡፡ በኒህ ሁሉ ጥገኝነቶችና ጥግ-ገኝነቶች ለተዘፈቀው ሥነ-ጥበባችን መፍትሄ ለመሻት በቅድሚያ ሁሉም ኃላፊነት ያለበት ራሱን መፈተሽ፣ ባደባባይ በግልጽ መነጋገር፣ የራስን አቋምና አካሄድ ማጥራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ (ሃቅና እውነቱን ከመመርመር እንዳልቦዘናችሁ አምናለሁ)
4. ብቸኝነት ወይም በይነ-ዲስፕሊኒያዊ አልባነት፡- ማንኛውም ሙያ ከሌሎች ሙያዎች ጋር ያለውን ዝምድና አካታች ሲሆን ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ከሃገራችን ታሪክ፣ ማኅበረሰቦች፣ ቋንቋ፣ ትውፊት፣ አኗኗርና...... ወዘተ መለያዎቹን የሚወርስ ሲሆን ከሙያ አንጻር ከሌሎች ዲሲፕሊኖች ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ባሕል ባለማዳበሩ በይነ-ዲስፕሊኒያዊ አልባነትን በማስተናገድ ብቸኛ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡ ምናልባት ከዚህ ብቸኝነት ነጻ ሊወጣ የሚችለው ከቅርብ አመታት ወዲህ እየዳበረ በመጣው ግጥምና ሙዚቃን በማቀናጀት በሚቀርቡ የ’ግጥምን በጃዝ’ መድረኮች ሠዓልያንን በማሳተፍ በተጀመሩ ጥረቶች ነው፡፡ ይህ በበኩሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት የሚያስፈልገው ቢሆንም ሥነ-ጥበባችንን ከብቸኝነት የመገላገያ ብቸኛው መንገድ ሆኖ መቀጠል እንደሌለበትም ግልጽ ነው፡፡
5. አዲስ አበቤነት፡ ሠዓሊዎቻችን ከመላው ሃገሪቱ የተሰባሰቡ ቢሆኑም የሚኖሩትና የሚሰሩት አዲስ አበባ በመሆኑና ሥነ-ጥበብ በመላው ሃገራችን ታዋቂና ተወዳጅ ሙያ እንዲሆን ጥረቶች ባለመደረጋቸው፣ ሥነ-ጥበባችን አዲስ አበቤነት እንዲላበስ አስገድዶታል፡፡ አዲስ አበቤነቱ በሃገር ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በዓለም-አቀፍ መድረኮችም እንቅስቃሴያችን የተገደበ እንዲሆን አስገድዷል፡፡  
6. የዕድገት ውስንነት፡ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች አያሌ ምክንያቶች የወቅቱ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እድገት የተወሰነ እንዲሆን ያደረጉ ሲሆን ይህ የዕድገት ውስንነት ገንዘብን ወይም ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንደማያካትት የሚሟገቱ አካላት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ጤነኛ ባልሆነ መልኩ የሚመጣ ኤኮኖሚያዊ ጥቅም ራሱ እንደ እድገት ሊቆጠር መቻሉንም ጨምረን ልንነጋገርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን እያስታወስኩ እሰናበታለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!!!

Read 2749 times