Sunday, 05 February 2017 00:00

“የደራሲያን ድንኳኖች!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

    ስለ ደራሲያን በሰማናቸው ጨዋታዎች አንዳንዴም ወጎች፣ ሌላም ጊዜ የህይወት ዳናዎች ተገርመን አናበቃም፡፡ የተለዩ ባህሪዎቻቸው አንዳንዴ ከሥጋ ለባሹ ተርታ ፈቅ አድርገን እንድንገምታቸው ሁሉ ያደርገናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ወፈፌዎች ናቸው እንዴ? የምንልበት ጊዜም አይጠፋም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ዶስተየቭስኪ እንደሚያስበው፤ከፍልስፍና ጋር እናጎራብታቸዋለን፡፡ … ለምሳሌ ቶልስቶይ ታሞ ሆስፒታል ተኝቶ፣ መድኃኒት አልወስድም ባለ ጊዜ፣ የልቡን ማንም አላወቀለትም! ታዲያ ጓደኛ ነኝ ባዩ፤ “አንተ ሰው መድኃኒቱን ውሰድ! … አለዚያ … ችግር ውስጥ ትገባለህ!” ቢለው፣ ቶልስቶይ ምርር ብሎ፤ “አንተ ነህ ያስጠላኸኝ፣ አንተ ካልወጣህ መድኃኒቱን አልወስድም!” ማለቱንና የምርም ጓደኛው ሲወጣ፣ በተገላገልኩ መንፈስ መድኃኒቱን መውሰዱን ስንሰማ፣ “የምን ጉድ ነው!” ያሰኘናል፡፡ …
ይህ ዓይነቱ ዝብርቅርቅ ስሜት፣ ደራሲያኑን ብቻ ሳይሆን ገጣሚያኑንም ይጨምራል፡፡ ታዲያ ዳንቴ ጋብሬል ሮሴቲ የተባለ ገጣሚ፣ የሆነውን ነገር ስናስብ ይብስ እንደነቅ ይመስለኛል፡፡  ሚስቱን በቅናት ድብን አድርጎ፣ ከልክ ያለፈ መድኃኒት ወስዳ እንድትሞት ያደረጋት ራሱ ገጣሚው ነው፣አውቆ ግን አይደለም፡፡ የሳምባ በሽታ ስለነበረባት ለርሱ የምትወስደውን መድኃኒት አብዝታ ቃመችውና ለዘላለም ተሰናበተች፡፡ ይሄኔ ገጣሚው ጨርቁን ጣለ፤ ፀሐፍት እንደሚሉት፣ በርግጥም ይወዳት ነበር፡፡ … እናም በፍቅር ሳሉ የፃፋቸውን ግጥሞች ሁሉ አብሯት ካልተቀበረ ብሎ፣ አብሯት እንዲቀበር አደረገ፡፡ … ይህ የጤነኛ ሰው ስራ ነው ባንልም፣ የፍቅር ከፍታ ውጤት ነውና ይሁን! … ግን እንደ ህፃን ልጅ አደረገው፡፡ በሰባተኛው ዓመት፣ ቤተሰቦችዋን ሄዶ አንድ ነገር ጠየቀ፡፡ … ግጥሞቹን ከመቃብር አስቆፍሮ ለማውጣት! … የፈረንጅ ቤተሰብ ደግ ነው፡፡ “ምናባቱ … ልጃቸውን የበላ አፈር … ለምን የገጣሚውን ግጥም ይብላ!” ብለው ፈቀዱለት፡፡ አውጥቶ አሳተመው! … አሁን ከዚህ በላይ ዕብደት አለ!? ኧረ ብዙ ነገር አለ፡፡ ኢቫን ቱርጌኔቭ ... የምሽቱን የተፈጥሮ መልክ ለማየት ብሎ በሌሊት ይቆዝም የለ እንዴ፤ ያለ እንቅልፍ! … ጨረቃና ክዋክብቱን አገላብጦ ሊስም ይሆናላ! … ወይ ከያኒ!
በዚህ ከቀጠልኩ ማቆምያ የለውም፡፡ ስለዚህ በጊዜ መለስ ልበልና፣ የደራሲያንን የድርሰት ምንጭ አብረን እንፈትሽ፡፡ መምህሮቻችን፤ “ድርሰት የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው!” እያሉ አስተምረውናል፣ ደግ ነው፡፡ ግን ከዚህም ትንሽ ቀረብ ይላል፡፡ በተለይ እውነታዊነት ላይ ያተኮሩ ድርሰቶች፣ በቀጥታ የደራሲውን የህይወት ገጠመኝ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፣ የስነ ጽሑፋዊ ሂስ ምሁራን፤ ”ህይወት ታሪካዊ ኂስን አስፈላጊ ነው” ብለው ወደ ጎራው የቀላቀሉት፡፡ የደራሲው ስራ ውስጥ ያሉ መቸቶችንና ገጠመኞችን፣ ገፀ ባህርያት፤ ከእውኑ ዓለም ጋር በማነፃፀር፣ የደራሲው የህይወት አንጓዎችን መለካት መሞከራቸው ለዚሁ ነው፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በፃፉት፤ “የሥነ ጽሑፍ መሰረታዊያን” ውስጥ የደራሲው ስራዎች ከእውነተኛ ገጠመኞች ጋር ቁርኝት ሊኖራቸው እንደሚችል ደጋግመው ያነሳሉ። ለዚህም ምሳሌ አድርገው በተለይ በአጫጭር ልቦለዶቿ፣ የምናውቃትን ዩዶራ ዌልቲን፣ ዋቢ አድርገው እንዲህ ጽፈዋል፡-    
“…የትም ይሁን የት፣በኖርኩበት ቦታ በዙሪያዬ የተመለከትኩትን ሁሉ መሠረት በማድረግ አንድ ዐይነት መድረክ እፈጥራለሁ፡፡ ይህን የማደርገው በፈጠራ ድርሰትና በእውኑ ዐለም የጠበቀ ትስስር አለ ብዬ ስለማምን ነው፡፡ በምናብ ዐለም የቱንም ያህል ርቆ ቢኬድም የተፈጠረው ሕይወት በዙሪያው ካለው እውን ህይወት ጋር የተቆራኘ ሆኖ ነው እሚሰማኝ፡፡… ስለዚህ በተቻለኝ መጠን እውኑን ዓለም መሰረት አደርጋለሁ፡፡”
እንግዲህ ይዶራ ዊልቲ-ይህን እማኝነትነት ሰጠች እንጂ ሌሎችም በዚሁ ተርታ የሚሰለፍ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ደራሲያን አሉ። ለምሳሌ አሜሪካዊው የኖቤል ተሸላሚ ደራሲ ኸርነስት ሔሚንግዌይን ተጨማሪ አደርገን መጥቀስ እንችላለን፡፡
ይህ ደራሲ በተለይ በእኛ ሀገር ተነብቦ ተወዳጅነት ያገኘለትን፣ “ሽማግሌውና ባህሩ”ን እንዴት እንደፃፈውና መነሻ ሀሳቡን ሲጠየቅ፤የሰው መልስ ከላይ ይዤ ከተሳሁት ሃሳብ ጋር የሚመሳሰል ነበር፡፡ ‹‹I know about a man in the situation with a fish. I knew what happened in a boat, in a sea, fighting a fish. So I took a man I knew for twenty years and imagined him under those circumstances.››
አዎ ሄሚንግዌይ፤ ኩባ ደሴት ላይ ለሃያ ዓመት የሚያውቃቸውና ዓሣ የሚያሠግሩ ሽማግሌ ነበሩ። በዚያ የሽማግሌና የዓሣ ፍልሚያ የሚያውቃቸውን ሽማግሌ ወደ ልቡ አምጥቶ፣ በምናብ አማሠላቸው፤ ቅመም ጨመረባቸውና ሽማግሌውና ባህሩን ፈጠረ።… ከሚያውቀው ሰው፤ የማይታወቅ ውበት ጨምሮ ዓለምን አሥደመመ፡፡
በዚሁ ተመሳሳይ ከፍ ያለ የጥበብ ማሳ ላይ ያለው የሩሲያው ታላቅ ደራሲ ሌዎ ቶልስቶይ ሥራዎች ውስጥ እጅግ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ገብተው፣ ቁመናና ባህሪያቸው ሳይቀር ተወስዶ፤ ጥበብ እየተነሰነሰ፤ ግጭት እያንባረቀበት፣ ድንቅ ድርሰቶችን ወልደዋል። ዶሪክ አሌክሳንደር እንደፃፈው፣ ቶልስቶይ እህቱን፤ ‹‹Childhood”, “Boyhood”, and “youth”  በሚሉት መጻህፍቱ ገፀ-ባህሪ እንዳደረጋት ይገልፃል። ለምሳሌ በ“Boyhood” ውስጥ እንዴት እንደሳላት እንዲህ ይናገራል፡-
…Describing his sister in his earlier novel ‹‹boyhood›› as the little girl lyubochka, Tolstoy tells as she is ‹‹small›› and because she has rickets her legs are still crooked and her figure is very ugly. ቶልስቶይ እህቱን በቫይታሚን ዲ እጥረት የተፈጠረባትን ደጋን እግርነት ብቻ አይደለም የሚያወራው፡፡ ስለ ፊቷ ሲተርክ ከዋክብት ዐይኖቿን አይረሳም፡፡ እንዲህ ይላታል፡- ‹‹…Really very beautiful- large and dark…›› እያለ ያደንቃታል፡፡ በርግጥም እህቱ ይህቺ ናት፡፡… ግን ድርሰቱ ውስጥ አለች፡፡ ረጃጅም ቀሚሶች እንደምትለብስም ይናገራል፣ ይህም እግሮቿን ለመሸፈን እንደሆነ አንባቢው ያውቃል፡፡… ግና ደግሞ ርግብ ናት!... ምስኪን!
ቶልስቶይ ባለቤቱንም፤ “War and peace” በተሠኘ ድርሰቱ ቦታ ሰጥቷታል፡፡ ባለቤቱ እጅግ ቀጥተኛ ሴት እንደሆነች በርካታ ፀሀፍት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲፅፉ ያነስዋታል፡፡ አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ፊሊና ያንሲን ጨምሮ፡፡ ታዲያ ይህቺን ቀናተኛ ሚስቱን በሌላ ገፀ ባህሪ ውስጥ አሣልፎ ይኖራታል፡፡ ዶሪስ አሌክሳንደር እንዲህ ይገልጸል፡-
“Tolstoy’s sarya has all his wife’s jealousy at the start of war and peace” ይህ ብቻ አይደለም፤ የቶልስቶይ በርካታ ገፀባህሪያት በአካባቢው ያሉትን ቤተ ዘመዶች ይጨምራል፤… ይሁን እንጂ ሰዎቹን ሙሉ ለሙሉ ወስዶ በጥሬው አይጠቀምም፤ ከባህሪያቸው ጋር ተያያዥ በሆኑ ገጠመኞች፣ በመንሥኤና ውጤት አጅቦ፤ በቋንቋ ውበት እያጫወተ ታሪኩን በስኬት ይደመድመዋል። በርግጥ የቱም ደራሲ፣ እውነተኛ ሰዎችን እንደ ገጸ ባኅሪ በጥቂቱ ይውሰድ እንጂ ከአካላዊ አሳሳላቸው ባለፈ ሥነ ልቡናዊና ማህበራዊ መልካቸውን እንደ ሁኔታው ሊቀይረው ይችላል፡፡
የኛ አገሮቹ ደራሲያን በዚህ ረገድ እንዴት ይሰለፋሉ ብለን፣ መስኩ ላይ እንደርድራቸው ብዬ አሰብኩ፡፡ ከእውነተኛ የሕይወት ገጠመኝና በቅርቡ የሚያውቃቸውን ሰዎች ገፀ ባህርያት አድርጎ በመጠቀም የበዐሉ ግርማን ያህል የተወራለት የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፤ ‹‹ስብሀት፡ ሕይወትና ክህሎት››፤ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፤ ‹‹በዐሉ ግርማና ስራዎቹ›› እንዲሁም ዶ/ር ታዬ አሰፋ፤ ‹‹ብሌን›› የተሠኘው መጽሔት ላይ ጠቅሰውታል፡፡
በተለይ ደራሲ ስብሀት ገብረ እግዚአብሔር ስለ በዐሉ በተነሳ ቁጥር፤ ‹‹ደራሲው›› የተሰኘው መጽሀፍ ውስጥ ያለው ሲራክ የተባለ ገፀባህሪ፣ ጋሽ ስብሀት እንደሆነና፤ ሠፈሩም ተረት ሰፈር እንደነበረ ብዙ ተነግሯል፡፡ እንዳለጌታ ከበደ በፃፈው የበዐሉ ግርማ ‹‹የቀይ ኮከብ ጥሪ›› ላይ ያሉት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰራተኞች፤ ‹‹ይህ እገሌ ነው!›› እስኪባል ድረስ ያስታውቁ ነበር በሚል ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ ጥበባዊ ሥራዎች ብዙ ቅመሞች እንዳሉት ፀሐፊው ገልጿል፡፡
የ“ሕያው ፍቅር” ደራሲ ደረጀ በቀለ እንዳወጋኝ፤ በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት ገፀ ባህርያት ናፖሊዮን፤ የመሳሰሉት ልጅ ሆኖ በሠፈር፣ አንዳንዶቹንም ካደገ በኋላ የሚያውቃቸው እንደሆኑና ታሪኩ ውስጥ ከተፈፀሙት ሁነቶችም ጋር ቁርኝት እንዳለው ጠቅሶልኛል፡፡
እንደዚሁ ወዳጄ ደራሲ ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይም፣ በመጽሐፍቱ ይበልጡንም “አጥቢያ” እና “የብርሃን ፈለጎች” ውስጥ የራሱ ሕይወት ገጠመኝ እንዲሁም አሳዳጊ አያቱና በሠፈር ውስጥ የሚያውቃቸው ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሶልኛል። ይህም ማለት የደራሲው መጽሐፍ ሲገለጥ፤ የደራሲውን  የቅርብ ጓደኞች፣ የሥራ ባልደረቦችና የሕይወቱ ተካፋይ የሆኑ ቤተሰቦች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ በርግጥስ ደራሲው ከተቆረሰበት ሠፈር፤ ዳቦና ሻይ ከተሻማቸው አሊያም ገጠር  እረኛነት ከዋለባቸው መስኮች-----ቀድሞ በፊቱና በልቡ ምን ሊነበበው ይችላል?...ምንስ ሊያስነብብ ነፍሱ ትበርበታለች? ክንፎቹስ ከዚያ አደባባይ አልፈው ወዴት ሊበርሩ ይችላሉ?...አዎ ምናባዊነት አለ... ያልታየ ሕይወትም ቢሆን ጥንስሱ፤…ያለና የነበረ ነውና ወዴት ይኬዳል?... ወደ ቀድሞው ድንኳን አይደል!... ደራሲያን ያሳዩን ይህንኑ ነው - በዚህ መሥመር!

Read 2472 times