Sunday, 05 February 2017 00:00

ሻይ ቡና

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

  (እረኛው ቃልዲ / ‹‹ሻይ ቅጠል ሕዝብ!››@)
     አቦል ቶና በረካ
(ስንቴ፤ ለምን፤ ምክንያት)
፩ - አቦል
(ስንቴ?)
ከመንጋው መሀከል ቅብጥብጧን ፍየል ስንት ጊዜ  አጣሃት
ጥቅጥቁ ጫካ ውስጥ ብቻዋን ስትገባ እየተከተልሃት
ሱስ ካስያዛት ተክል ከቡና ዛፉ ስር ድብን! ፍርፍር! ብላ ስትስቅ አገኘሃት?
ፍሬዋን ቀጥፈህ ወስደህ ከቤተሰብህ ጋር ስንት ጊዜ ጠጣሃት
ሽታው ላወዳቸው ለአዛውንቱ ሼካ ስንት እፍኝ ዘየርሀት  
ጠይቧ ሸክለኛ በእንባዋ አቡክታ ጀበና እስክትሰራልህ ስንት አርብ ጠበቅሀት?
ኋላም ገድሏን ሰምተው ማንኪራ ምድር ላይ በዱአ ያስቆሏት
ፍንጃሉን ደርድረው በሀላል ሲያስፈሏት
ቤተ መንግስት እልፍኝ ንጉሡንም ጋብዘው  ስን - ስንቴ ፉት አሏት?
ፌርማታው ፊት ለፊት፤ የጀበና ቡና መሸጫ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ፤ ‹‹ባክህ ተወው፤ ይኼን ሻይ ቅጠል ሕዝብ!” አለና የቡና ሲኒውን በአንድ ትንፋሽ ፉት አድርጎ ሲያስቀምጥ አየሁት፡፡ ‹የቡና ስባቱ መፋጀቱ›ን እንጂ ‹ቃል ያድን ቃል ይገድል›ን ገድፏል ይኸ ሰው፤ አልኩ በልቤ፡፡ዓለሙን ሁሉ ‹‹ይሁን›› ብሎ በቃሉ የፈጠረው፣ ቃል በእለት ተእለት ኑሯችን ውስጥም የመርገምትና በረከቱ ፋይዳ፣ ‹‹የአፍህን ፍሬ ትበላለህ›› ሆኖ ሳለ፡፡ ሰውየው የሚያጣጥመው ቡናችንን ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ›› ብለን ውዳሴ ባዜምንለት አንደበታችን መልሰን ደግሞ ‹‹ሲኦል በራፍ ላይ የተኮደኮደ የዲያቢሎስ ሰንጋ ፈረስ ገመድ በጥሶ ወደ ምድር ሲወርድ፤ ይግጠው ከነበረው አፉ/ጥርሱ ላይ ከቀረ መሬት የወደቀ ችግኝ ቡን በቀለ!›› የማለታችን የመርገምት ድርሣን ትሩፋት በዘመናት የታየው አጉል ኩነት ምስክር ነው፡፡ በአንድም በሌላም፡፡ ለዚህም ይሆናል ከአመታት በፊት ለእረኛው ቃልዲ መጠይቅ እንደወረደ ከተሰደረው Free Verse ስንኝ - አቦልን (ስንቴ?) አስታውሼ በውስጤ ያነበነብኩት፡፡ በሳድስ ፊደላት ቤት እየመታ የሚዘልቀው ተራኪ ግጥሙ (Narrative Poetry) በጠጣር ቅኔ ባያጌጥም፣ በእምቅ ሀረጋት ባይለበጥም፤ በቃልዲ ስም ይከተብ እንጂ በወል የሚያጠይቅ ላህይ አለው፡፡ ለጣቂው የግጥሙ አንጓም - ቶና (ለምን?) ይህንኑ ‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ...› ወይም ‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›ን አመላካች ይዘት አለው . . .
፪ - ቶና
(ለምን?)
ፍሬዋን በቅድሚያ ስሟን ‹‹ቡና›› ብለህ  ለምን ነው የጠራሃት
በጉዲፈቻ ሥም አረቢካ-ስ-ትባል ከቶ ለምን ዝም አልሃት
ከአረብ ሀገር አልፋ ለክፍለ ዘመናት
በአውሮጳ ምድር ገቢ ማጋበሻ ስትሆን ለምን ተውሀት?
እጅ እግር ሲቆረጥ ችግኟን በመንካት
በሴራ ተሰርቃ ብራዚል እስክትደርስ በአሣር አስመለክካት
በመአዛዋ ስስት በረከቦቷ ማዕድ ሰው ዘር ሲተቃቀፍ በሌት ተቀን መአልት
ምድርና ሞላዋ ‹‹ድንኳኗን›› ሲተክሉ ‹‹ኮፊ›› ‹‹ካፌ›› እያሏት
ግልገልክን ታቅፈህ ለምን በፀ - ጥታ በሩ - ቁ አስተዋልሀት?
ብላቴናው ቃልዲ፤ ነጋ ጠባ ያቺን ታክቲከኛ - ወገኛ-ተአምረኛ፣ አስቸጋሪ ወጠጤ ፍየል ፍለጋ በየጥሻና ስርጓጉጡ ሲኳትን፤ እሾህና ቆንጥር የበጣው የውስጥ እግሩ፤ ውሎ ሲያድር ውሃ ቋጥሮ ሲያዥ ሰንብቶ፤ አጥንት ድረስ እሚመዘምዝ ህመሙን የታወቀለት፣ ቁስሉ ትኩረት አግኝቶ ምናልባት ረመጥ በተነከረ እራፊ ጨርቅ ተተኮሰለትና እፎይ ያለባት ቀን፤ ያቺ የቡና ፍሬን አግኝቶ የመጣባት ምሽት ሳትሆን አትቀርም፡፡ የቃልዲ የእግር ቁስል ቢያገግምም የቡና ፍሬ ባለቤትነት ቁጭት ግን መገረኑ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ወደ ሀበሻ ዘመዶቻቸው በእንግድነት ብቅ ብለው በተስተናገዱ እንግዶች ጓዝ ወደ አረቡ አለም ያቀናችው የቡና ተክል፣ መንገዷን ቀጥላ አውሮጳ ምድር ስትደርስ ፈረንሳዊያን በተራቸው ከቡና የሚገኘው ገቢ ብቸኛ ተጠቃሚ በመሆን ለ200 አመታት ትርፍ ሲያጋብስቧት ኖሩ፡፡ በየጉዞ መነሻና መዳረሻ (ወደብ) ስፍራዎችና በነባርና አዲስ በሚቆረቆሩ ከተሞች ዙሪያ ሁሉ ከኢትዮጵያ ከፋ Kaffa የተገኘችውን ቡናን Coffee በየቀኑ ለማግኘት በሚሰባሰቡ ታዳሚዎቿ ሰበብ የተከፈቱ የቡና መሸጫ ቤቶች - Cafe ናቸው ቀስ በቀስ እየተስፋፉ ለሆቴሎች መፈጠር ምክንያት የሆኑት ተብሎም ይታመናል፡፡ ፈረንሳዊያን ከቡና የሚገኘውን ገቢ በብቸኝነት መቆጣጠር ያስችላቸው ዘንድ ያወጡት መመሪያ አስከፊ ነበር፡፡ ከተፈቀደለት የመንግስት አካል በስተቀር ማንም የቡና ችግኝ ይዞ ቢገኝ፤ ለዚሁ ተብለው በሰለጠኑ አነፍናፊ ውሾች ስለሚደረስበትም፤ ያላንዳች ማወላወል እጁን እስከ መቆረጥ የሚደርስ ቅጣትን ይከናነባታል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ይህን ግጥም ያነበቡ ቀናኢ ኢትዮጵያዊ ፤ ፈረንሳዊያኑም ያነብቡት ዘንድ ሙሉውን ግጥም የተረጎሙት ሲሆን፤ በተለይ ይህቺኑ የቡናን በባእዳን መጠሪያ ስያሜ፣ ከፍተኛ ገቢንና አስከፊ ቅጣቱን የምትተርከውን የቶና አንጓ  ብቻ ለአይነት ቆንጥረን እንያት...
2 – Tona
(Pourquoi?)
Mais au tout début,Pourquoi donnas-tu
Le nom « café » à ce grain?
Pourquoi permis-tu Que l’on lui collât
Le nom « Arabica »,Un nom adoptif ?
Et tu permis pourquoi Qu’il se répande loin
Au-delà des pays arabes
Pour, durant de longues années,
Servir de source De profit financier? Pourquoi ?
Malgré l’interdiction D’y toucher
Au risque de se faire coffrer,
Pourquoi laissas-tu la bande
La passer en contrebande
Jusqu’au Brésil ?Pourquoi en fis-tuUn fétiche?
L’entière humanité,Par son arôme ensorcelée,
Autour de sa rekebote de majesté,
De jour comme de nuit se rassemblait;
Lorsque la Terre entière Et ses habitants
Le fameux arbuste ils vénéraient,
Répétant «Coffee!» «Café!»
Toi, tu es resté Avec ton chevron excité
Contemplant de loin Sans ne rien faire,
Sans ne rien dire, Pourquoi
እና ታዲያ እንዲህ ባለ ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ የነበረውን የቡና ችግኝ፣ ብራዚላዊያን በምን ተአምር እጃቸው አስገቡት? ምስጢር ነው!...(ከአፍታ ቆይታ በኋላ....)
‹‹ኑ ቡና ጠጡ›› በሚል መርሀ ግብር የኤችአይቪ ኤድስን መስፋፋት ለመግታት በሀገራችን የተደረገው ዘመቻ ውጤቱ ጥሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ይህን የማህበራዊ መስተጋብራችንን ልምድ በመፍትኼነት ለመጠቀም ሀሳቡን ያመነጨውን ሰው ሳናደንቅ አናልፍም፡፡ የቡና ማእዳችን በተለይ የኑሯችን ምሰሶዎች የሆኑት እናቶቻችንና እህቶቻችን የመርዶና ብስራታቸው ማወጃ፣የእለት ተእለት ኑሯችን እንከኖች መንቀሻ፣ በእራፊ ቀሚሳቸው ጫፍ ቁስሎቻችንን የሚተኩሱበት፤ የህመሞቻችን እንባ ማበሻ. . . ወዘተ አድርገውት መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ ‹‹ተወው ባክህ ይህን ሻይ ቅጠል ሕዝብ!›› ካለው ወንድማችን በተለየ፡፡
በነገራችን ላይ ሻይ ቅጠልም እንደ ቡናችንና አብዛኛው በርካታ ግኝቶች የአጋጣሚ ግኝት ነበረ፡፡ የቻይና ገበሬዎች ውሀ በሸክላ ድስት ጥደው፣ መስክ ላይ አረፍ ብለው ሲነቁ፤ የፈላው ውሃ መልኩን ቀይሮ ቀልቷል፡፡ ጠጡት፡፡ ያለወትሮው ተነቃቁ፡፡ ወዲያውም ነፋስ አምጥቶ በድስቱ ውስጥ የሞጀረውን ቅጠል በአካባቢው አገኙትና፤ሻይ ቅጠል የሰው ልጅ የኑሮ አጋር ሆነ፡፡ እንዴትና በየት በኩል ወደ ጃፓን እንደገባ እንጃዪ፤ ከቻይናዎቹ በላይ ጃፓናዊያን፣ ለሻይ ማእድ የተከበረ ስርአት አላቸው፡፡ የሻይ መጠጫ ብቻ የሆነ ክፍልም አላቸው፡፡ በእኛም ሀገር የቡና መጠጫ ብቻ ክፍል ያላቸው ቢኖሩም አሉታዊ ትርጓሜው ያይላል፡፡ ለዚህም ይሆናል የጀበና ቡናን ለመጀመርም መዘግየታችን፡፡ ጀበና ሰሪዋን ጠይቧን ሸክለኛን ለማክበርም እንዲሁ፡፡ በቡና ስም ስፖርት ክለብና ባንክ የመሰየሙ፤ በቃልዲ ስም ቡናችን በስፋት የመተዋወቁ ነገር ቢዘገይም ቁጭትን የሚክስ አይነት ስሜት የሚያሳድር ይመስላል፡፡ እናም በትህትናቸው ከኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይነት መልክ ጋር የሚነጻጸሩት ጃፓናዊያኑ፣ የሻይ ግብዣ የሚያቀርቡለትና ወደ ሻይ ክፍላቸው የሚያስገቡት በክብር የሚጋብዙትን እንግዳቸውን ብቻ ነው፡፡እግራቸውን አጥፈው በተመስጦ ተቀምጠው፣ በጥሞና የሚያጣጥሙት የሻይ ማእድ ስርአታቸው ሂደትም ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ዙር የሚከናወን ነው፡፡ የኛ ቡና ሶስት ጊዜ የሚጠጣበትን ምክንያት በማሳረጊያችን ላይ ያንኑ የፈረደበትን ቃልዲን ጠይቀን እንሰነባበታለን፡፡ ላሁኑ ግን ከላይ የጀመርነውን የቡናን ከፈረንሳይ እስከ ብራዚል መድረስ ድንቅ ገድል እንቋጭ፡፡
ብራዚላዊያኑ አንድ መልከ መልካም ወታደራቸውን በልዩ ሁኔታ አሰልጥነው ወደ ፈረንሳይ ግዛት ድንበር በጀልባ አደረሱት፡፡ የጦር መኮንኑ የጉዋና ግዛት ሀገረ ገዢን ሚስት በፍቅር አነሁልሎ ጨርቋን አስጣላት፡፡ከዚያስ... የቡና ችግኙ መአዛ እንዳይነቃ በትኩስ አበቦች መካከል አድርጋ በጀልባው ላይ ጫነችለታ፡፡ ወቴ ሆዬ፤ እንኳንስ አነፍናፊ ሶሎግ ውሻ፣ አውራ ዶሮም ሳይጮህበት፣ የቡና ችግኙን ይዞ ከአውሮጳ ወደ ላቲን እብስ! እናስ ዛሬ በአለም ላይ ግንባር ቀደሟ የቡና ምርት ገቢ ተጠቃሚ ማን ሆነች - ብራዚል!
በቻይና ገበሬዎች የቀን ሽልብታ መሀል የተገኘው የሻይ ቅጠልም እንዲሁ በግዛታቸው ጸሐይ አትጠልቅም የሚባሉት እንግሊዛዊያን ብቸኛ ገቢ ማጋበሻ ሆኖ ቆይቶ፤ አንድ ምሽት በ1773 እ.ኤ.አ የሻይ ቅጠል ቀረጥ ያንገፈገፋቸው የቦስተን ነዋሪዎች ሰብሰብ ብለው፤ በመርከብ የተጫነ ሻይ ቅጠል እያፈናጠሩ ወደ ባህር ከተቱ፡፡ አንድ የእንግሊዝ ወኪል በነበረ ቀረጥ ሰብሳቢ ህንዳዊ ጉሮሮ የተንተከተከ ሻይ ቅጠል አንቆረቆሩበት፡፡ በዚህ መልኩ የተጀመረው የቦስተን የሻይ ቅጠል ቀረጥ አመጽ (Boston tea party) ንቅናቄ ወደ ታሪካዊው የአሜሪካ አብዮት አደገና በመጨረሻ አሜሪካዊያኑን ከእንግሊዝ መዳፍ ነጻ ሊያወጣቸው ቻለ፡፡ እናም ታዲያ የጀበና ቡና መሸጫ በራፍ ላይ ቁጭ ብሎ፤ ‹‹ተወው ባክህ ይኼን ሻይ ቅጠል ሕዝብ!›› ላለው ምስኪኑ ወንድሜ፤ ሻይ ቅጠል አሜሪካን ነጻ እንዳወጣ ማን በነገረው አልኩ በልቤ፡፡  
፫-በረካ
(ምክንያት)
እረኛው ቃልዲ ሆይ፤አረንጓዴዋን ወርቅ ነክተህ እንደባረክሃት
ከማንኪራ ጫካ ከኢትዮጵያ ለአለም  ቀምሰህ እንደላክሃት
ያቺን ተዓምር ፍሬ ብቻህን አውቀሀት ቀድመህ አፍልተሃት
ሁለት ወይ አራቴ አምስት ስድስት ሰባቴ ከቶ ያልጠጣሃት
ምክንያትህ ምን ይሆን ቡና ማዕዳችንን በሦስት የከፈልሃት?
‹‹አቦል፣ ቶና፣ በረካ›› ብለህ የጠራሃት፤ ወይም ያስጠራሃት?
ልክ እንደ መወለድ፤ ማደግ፤ እና መሞት የኑሮ ዑደት ግብዓት
የአልፋ ወ ኦሜጋ ክስተትና ጉዳይ የአለም ወ ፍጥረታት
ጅምሩ፤ መሃሉ፤ እናም መጨረሻ፤ ንዑስ ክፍል እንዳላት
የሦስትነትን፤ የህይወትን ምስጢር ለልጅነት ልብህ ምን ሀይል ሹክ አላት?!

Read 2593 times