Sunday, 05 February 2017 00:00

“ጊዜ” ኮንሰርት በኢንተርኮንትኔንታል ይቀርባል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 የትዝታው ንጉስ ማህሙድ አህመድ፣ ዝነኛዋ ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደና ድምጻዊ ሳሚ ዳን የሚያቀነቅኑበት “ጊዜ” የሙዚቃ ኮንሰርት በመጪው የካቲት 11 ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ይካሄዳል፡፡ አንጋፋው ድምጻዊ ማህሙድ አህመድ ለዚሁ ኮንሰርት ሰሞኑን ከአሜሪካ እንደሚመጣም ታውቋል፡፡
እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ለሚዘልቀው ለዚህ ኮንሰርት፣ ሶስት ሺህ ቪአይፒ ቲኬቶች የተዘጋጁ ሲሆን ቀድመው ለሚገዙ 600 ታዳሚዎች፣ ቲኬቶቹ በ500 ብር ይሸጣሉ ተብሏል፡፡  ቀሪዎቹ በ900 ብር የሚሸጡ ሲሆን ወቅቱ “የፍቅረኞች ቀን” ሳምንት በመሆኑ ለጥንዶች በ1400 ብር ቲኬቶች መዘጋጀታቸውም ታውቋል፡፡  የቲኬት ሽያጭ ቀድሞ እንደሚያልቅና በኮንሰርቱ ዕለት ቲኬት እንደማይሸጥ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡
ኮንሰርቱ “ጊዜ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የቀድሞው፣ የመካከለኛውና የአሁኑ ዘመን ተወዳጅና ብርቅዬ አቀንቃኞች በጥምረት የሚጫወቱበት በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ከሙዚቃ ረዘም ላለ ጊዜ ጠፍታ የቆየችው ዘሪቱ፤በዕለቱ በአዲስ ሥራ እንደምትጠበቅና ሳሚ ዳንም ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ የአልበሙን ዘፈኖች እንደሚጫወት አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ኮንሰርቱን ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘርና ዳኒ ዳቪስ በመተባበር እንደሚያዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከአንድ ወር በፊት ከሀበሻ ቢራ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው “ኢትዮጵያዊ” ኮንሰርት ከገቢው 50 በመቶውን (ግማሽ ሚ. ብር) ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል መለገሱ የሚታወስ ነው፡፡

Read 850 times