Saturday, 11 February 2017 13:58

ርዕስ የሌለው ታሪክ

Written by  ድርሰት - አንቶን ቼክሆቭ ትርጉም - ተፈራ ተክሉ
Rate this item
(0 votes)

  መነኮሳቱ ይሰራሉ ይጸልያሉ፤ የገዳሙ አባት ደግሞ በኦርጋናቸው እየተጫወቱ፣ የላቲን ስንኞችን እየሰካኩ፣ መዝሙራቸውን ይጽፋሉ፡፡ አስደናቂው አዛውንት ልዩ ተሰጥኦ አላቸው፡፡ በትንሿ ክፍላቸው ውስጥ ሆነው ኦርጋኑን ሲጠበቡበት የሚወጣው ድምጽ፣ በዕድሜ የገፉና ጆሯቸው የሚያስቸግራቸው መነኮሳት እንኳን እንባቸውን ለመቆጣጠር ይቸገራሉ፡፡ ስለ ምንም ነገር ሲናገሩ፤በጣም ተራ ስለሆኑ ነገሮች እንኳን፣ ለምሳሌ ስለ ዛፎች፣ ስለ ዱር አውሬዎች፣ ወይም ስለ ባሕሩ፣ ልክ እንደ ኦርጋኑ የነፍሳቸው አውታሮችም የሚርገበገቡ ይመስላል፤ እናም ፈገግ ሳይሉ ወይም ሳያነቡ ሊያዳምጧቸው አይችሉም፡፡ በንዴት በሚጦፉበት ወይም በጥልቅ ደስታ በሚዋጡበት ወቅት ወይም ስለ አንድ መጥፎ ወይም ድንቅ ነገር ማውራት ሲጀምሩ፣ የማነቃቃት ጥልቅ ሥሜት ውስጥ ይገባሉ፣ የሚንቦገቦጉት ዐይኖቻቸው በእንባ ይሞላሉ፣ ፊታቸው ይቀላል፣ ድምጻቸውም እንደ ነጎድጓድ ያስተጋባል፡፡ የሚያዳምጧቸው መነኮሳትም በእሳቸው መነቃቃት፣ ነፍሶቻቸው እንደተመሰጡ ይሰማቸዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ድንቅ፣ ውብ ቅጽበቶች፣ በመነኮሳቱ ላይ ያላቸው ሐይል ገደብ የለውም፤ እናም እያንዳንዳቸው ወደ ባሕሩ ራሳቸውን እንዲወረውሩ ቢጠይቋቸው ሁሉም ትዕዛዛቸውን ለመፈጸም ይጣደፋሉ፡፡
እግዚአብሔርን፣ ሰማየ ሰማያቱንና ምድርን ከፍ ከፍ የሚያደርጉባቸው መዝሙራቸው፣ ድምጻቸውና ግጥሞቻቸው ለመነኮሳቱ የማያቋርጥ የደስታ ምንጭ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ሕይወታቸው ምንም የተለየ ነገር ባለማስተናገዱ በዛፎቹ፣ በአበባዎቹ፣ በፀደዩ፣ በበልጉ ተሰላችተዋል፤ ጆሮዎቻቸው የባሕሩን ድምጽ ሰልችተውታል፣ የወፎቹ መዝሙርም አሰልቺ ሆኖባቸዋል፣ የገዳሙ አባታቸው ተሰጥኦ ግን ልክ እንደ ዕለት ጉርሳቸው ያስፈልጋቸው ነበር፡፡
ብዙ ዓመታት አለፉ፣ እያንዳንዱ ቀንም ልክ እንደ ሌላው ቀን፡ እያንዳንዱ ምሽት ልክ እንደ ሌላው ምሽት ነበር፡፡ ከወፎቹና የዱር አውሬዎቹ በስተቀር አንድም ነፍስ ወደ ገዳሙ አቅራቢያ ብቅ አይልም፡፡ ከገዳሙ በቅርበት ወደሚገኘው መንደር ለመድረስ 112 ኪሎ ሜትር ያህል የሚሸፍነውን በረሀ አቆራርጦ መሄድ ግድ ይላል፡፡ የምድርን ሕይወት የናቁ፣ እርግፍ አድርገው የተውትና ወደ ገዳሙ መሄድን፣ ወደ መቃብር እንደመሄድ የቆጠሩት ሰዎች ብቻ ነበሩ፣ በረሀውን ለማቋረጥ የደፈሩት፡፡
ለዚህም ነበር በአንድ ምሽት ላይ አንድ ተራ ኀጢአተኛና ሕይወትን የሚወድ የከተማ ሰው፣ በራቸውን ሲያንኳኳ የተገረሙት፡፡ ይህ ሰው ጸሎት ከማድረሱም ሆነ የገዳሙ አባት እንዲባርኩት ከመጠየቁ በፊት ወይንና ምግብ ጠየቀ፡፡ ከከተማ ወደ በረሀው እንዴት እንደመጣ ሲጠየቅ፣ ረዘም ባለ የአደን ታሪክ መለሰ፤ ለአደን ወጥቶ፣ ከመጠን ያለፈ ጠጥቶም መንገድ ጠፋበት፡፡ ወደ ገዳሙ ገብቶ ነፍሱን እንዲያድን ለቀረበለት ሐሳብ፣ በፈገግታ እንዲህ ሲል መለሰ፡- “ለእናንተ የምገባ አጋራችሁ አይደለሁም!”
ከበላና ከጠጣ በኋላ ያስተናገዱትን መነኮሳት ቀና ብሎ ተመልክቶ፣ ጭንቅላቱን በግሳጼ እየነቀነቀ እንዲህ አለ፡-
“እናንተ መነኮሳት፤ ምንም የምታደርጉት ነገር የለም፡፡ ከመብላትና ከመጠጣት ውጭ ሌላ አታውቁም፡፡ አንድ ሰው ነፍሱን የሚያድንበት መንገድ ያ ነው? አስቡት እስኪ፤ እናንተ እዚህ በሰላም ቁጭ ብላችሁ፣ እየበላችሁ፣ እየጠጣችሁና ብፅእናን እያለማችሁ እያለ፣ ጎረቤቶቻችሁ እየጠፉና ወደ ሲዖል እየሄዱ ነው፡፡ በከተማው ምን እየተከናወነ እንደሆነ ማየት አለባችሁ! አንዳንዶች በረኀብ እየሞቱ ነው፣ ሌሎቹ ደግሞ ወርቃቸውን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ባለማወቃቸው፣ በአባካኝነት ሰጥመው፣ ልክ ማር ላይ እንደተጣበቁ ዝንቦች እየጠፉ ነው፡፡ በሰዎች ዘንድ እምነትም ሆነ እውነት የለም፡፡ እነሱን ማዳን የማን ሥራ ነው? ለእነሱ መስበክስ የማን ሥራ ነው? ከጥዋት እስከ ማታ እንዲህ ስክር የምለው፣ የእኔ ሊሆን አይችልም፡፡ የየዋህ መንፈስ፣ አፍቃሪ ልብና በእግዚአብሔር ማመን የተሰጣችሁ፣ በእነዚህ አራት ግድግዳዎች ውስጥ ቁጭ ብላችሁ ምንም ሳትሰሩ እንድትውሉ ሊሆን ይችላል?”
የከተማው ሰው የስካር ቃላቶች፣ ብልግና የተሞላባቸውና ተገቢ ያልሆኑ ነበሩ፤ ነገር ግን በገዳሙ አባት ላይ እንግዳ የሆነ ተጽዕኖ ነበራቸው፡፡ ሽማግሌው ከመነኮሳቶቻቸው ጋር በጨረፍታ ተያዩ፣ ፊታቸው ገረጣ፣ ከዚያም እንዲህ አሉ፡-
“ወንድሞቼ፡- እውነቱን ነው የሚናገረው፣ ታውቃላችሁ፡፡ በእርግጥ ድሃ ሰዎች በደካማነታቸውና የመገንዘብ ችሎታቸው ማነስ ምክንያት በምግባረ ብልሹነትና በቃል ኪዳን ማፍረስ እየጠፉ፣ እኛ ደግሞ ይህ እንደማይመለከተን ሁሉ የሆነ ነገር ለማድረግ እየሞከርን አይደለም፡፡ ስለረሱት ክርስቶስ ሄጄ ላስታውሳቸው የማይገባኝ ለምንድን ነው?”
የከተማው ሰው ቃላቶች ሽማግሌውን አነሳሷቸው። በሚቀጥለው ቀን ምርኩዛቸውን ይዘው፣ መነኮሳቶቹን ተሰናብተው ወደ ከተማው ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ፡፡ መነኮሳቶቹም መዝሙራቸውን፣ ንግግራቸውንና ግጥሞቻቸውን ተነፈጉ፡፡ አንድ፤ ከዚያም ሁለት አሰልቺ ወራትን አሳለፉ፤ ነገር ግን ሽማግሌው አልተመለሱም፡፡ በመጨረሻ፤ ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ በደምብ የሚያውቁት የምርኩዛቸው ድምጽ ተሰማ፡፡ መነኮሳቱ ሊቀበሏቸው ብር ብለው ሄዱ፡ በጥያቄም አጣደፏቸው፡ ነገር ግን ሽምግሌው ስላገኟቸው በመደሰት ፋንታ አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ምርር ብለው አነቡ፡፡ መነኮሳቱ አባታቸው በጣም እንዳረጁና ከሳ እንዳሉ አስተዋሉ፤ ፊታቸው ድካምና ጥልቅ ሐዘን ተላብሷል፡ ሲያለቅሱም የተበሳጨ ሰው ገጽታን ተላብሰው ነበር፡፡
መነኮሳቱም ማንባት ጀመሩ፡፡ በሐዘኔታም ለምን እንደሚያለቅሱና ለምን ፊታቸውን እንዳጨለሙት ይጠይቋቸው ጀመር፡፡ ነገር ግን ሽማግሌው አንዲትም ቃል ሳይተነፍሱ፣ ራሳቸውን በትንሿ ክፍላቸው ውስጥ ቆለፉ፡፡ ለሰባት ቀናት በክፍላቸው ውስጥ ሆነው፣ ምንም ሳይበሉና ሳይጠጡ፣ እያነቡና በኦርጋናቸው ሳይጫወቱ ቁጭ አሉ፡፡ በራቸውን በማንኳኳትና ወጥተው ሐዘናቸውን እንዲካፈሏቸው ለሚለማመጧቸው መነኮሳቶች በማይሰበር ዝምታ መለሱላቸው፡፡
በመጨረሻ ወጡ፡፡ ሁሉንም መነኮሳቶች በዙሪያቸው ሰብስበው፣ እንባ በተላበሰ ፊትና በሐዘንና የቁጣ ገጽታ በእነዚያ ሦስት ወራት ምን እንዳጋጠማቸው ይነግሯቸው ጀመር፡፡ ከገዳሙ ወደ ከተማው የነበረውን ጉዟቸውን ሲገልጹ፣ ድምጻቸው ረጋ እንዳለና ዐይኖቻቸው ፈገግታን ተላብሰው ነበር። መንገድ ላይ ወፎች እንደዘመሩላቸው፣ ጅረቶቹ እየተፍለቀለቁና ጣፋጭ የወጣትነት ተስፋ፣ ነፍሳቸውን እያነሰሳት እንደነበር ነገሯቸው፤ ገሰገሱ፡ ስሜታቸውም ወደ ጦር ግንባር እንደሚሄድና በሙሉ ልብ ድል እንደሚያደርግ ወታደር አይነት ነበር፤ በሕልም ውስጥ ሆነው እየተራመዱ፣ ግጥምና መንፈሳዊ መዝሙሮችን እየደረሱ፣ ሳያስቡት የጉዟቸው መጨረሻ ላይ ደረሱ፡፡
ስለ ከተማውና በውስጡ ስለሚኖሩት ሰዎች መናገር ሲጀምሩ ግን ድምጻቸው እየተንቀጠቀጠ፣ ዐይኖቻቸው እየተንቀለቀሉና በንዴት ተሞልተው ነበር፡፡ ወደ ከተማው ሄደው ያጋጠማቸውን ነገር በሕይወታቸው በፍጹም አይተውት ወይም ለማሰብ እንኳን ደፍረው አያውቁም፡፡ አሁን ብቻ ነው በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜና በስተርጅና ሰይጣን እንዴት ኀያል እንደሆነ፣ ክፋት እንዴት ተራ እንደሆነና ሰዎች ምን ያህል ደካማ፣ ፈሪና ዋጋ ቢሶች እንደሆኑ ያዩትና የተረዱት፡፡ ደስታ ቢስ በሆነ ዕድል ምክንያት መጀመሪያ የገቡት በመጥፎ ምግባር መኖሪያ ነበር። አንድ ኀምሳ የሚሆኑ ብዙ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ከተገቢው በላይ እየበሉና ወይን እየጠጡ ነበር። በወይኑ ተሳክረው አንድ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ከአፉ ሊያወጣቸው የማይችላቸውን ዘፈኖች እየዘፈኑና መጥፎና አስቀያሚ ቃላትን እየወረወሩ ነበር፤ ከልክ ባለፈ ነጻነት፣ በራስ መተማመናቸውና ደስተኝነት እግዚአብሄርንም፣ ሰይጣንንም ሆነ ሞትን ሳይፈሩ፣ ነገር ግን የወደዱትን በማለትና በማድረግ፣ መረን የለሽ ፍላጎታቸው ወደመራቸው ይነጉዱ ነበር፡፡ ጥርት ያለውና ጠብታዎቹ የወርቅ ፍንጣቂ የመሰለውን ወይን ጥዐሙንና መዐዛውን መቋቋም ከባድ የነበረ ይመስላል፤ ምክንያቱም የጠጡት ሁሉ በደስታ ፈገግ እያሉና ተጨማሪ ለመጠጣት እየፈለጉ ነበር፡፡ ለሰዎቹ ፈገግ ማለት ወይኑም በፈገግታ ይመልስና፣ ሲጠጡት በደስታ ያንጸባርቃል፤ በጥዐሙ ውስጥ ደብቆ የያዘው ሰይጣናዊ መስህብ እንዳለ ያወቀ ይመስል፡፡
ሽማግሌው ብስጭታቸው እየጨመረ ሄዶ በቁጣ እያነቡ ያዩትን መግለጻቸውን ቀጠሉ፡፡ በፈንጣዦቹ በተከበበ ጠረጴዛ ላይ አንዲት ግማሽ አካሏ የተራቆተ ኀጢአተኛ ቆማለች አሉ፡፡ ለማሰብ በጣም ይከብድ ነበር ወይም ተፈጥሮ ውስጥ ከዚህ የሚልቅ ደስ የሚልና የሚያስደንቅ ነገር ለማግኘት ይከብዳል፡፡ ይህቺ በደረቷ የምትሳብ፣ ወጣት፣ ባለ ረዥም ጸጉር፣ ጠቆር ያለ ቆዳ፣ ጥቁር ዐይኖችና ሙሉ ከንፈሮች፣ ኀፍረተ ቢስና ባለጌ፣ እንደ በረዶ የነጡ ጥርሶቿን እያሳየች ፈገግ ትላለች፡- “ተመልከቱ፤ ምን ያህል ኀፍረተ ቢስና ምን ያህል ቆንጆ እንደሆንኩ” ለማለት የፈለገች ይመስል፡፡ ትከሻዋ ላይ ጣል አድርጋው የነበረው ሀርና ወርቃማ ልብስ እየተጣጠፈ ወደቀ፤ነገር ግን ቁንጅናዋ በልብሶቿ የሚደበቅ አልነበረም፡፡ ይልቅ በተጣጠፉት በኩል በጉጉት አፈትልኮ ልክ በፀደዩ መሬት ላይ ማቆጥቆጥ እንደጀመረ ሳር ይወጣል፡፡ ኀፍረተ ቢሷ ሴት ወይን ትጠጣለች፣ ዘፈን ትዘፍናለች፣ እንዲሁም ራሷን ለፈለጓት ሁሉ አሳልፋ ትሰጣለች፡፡
ከዚያም ሽማግሌው ክንዳቸውን በቁጣ እያወዛወዙ የፈረስ ግልቢያዎቹን፣ የኮርማ ግጥሚያዎችን፣ ቲያትሮችን፣ ራቁታቸውን የሆኑ ሴቶች የሚሳሉበትንና በሸክላ የሚቀረጹበትን የአርቲስቶቹን ስቱዲዮዎች ገለጹ፡፡ በመነሳሳት መንፈስ ውስጥ ሆነው፣ በጎርናና ድምጽ ሲናገሩ የማይታዩ አውታሮችን የሚጫወቱ ይመስል ነበር፤ በተቃራኒው መነኮሳቱ በድንጋጤ ድርቅ ብለው፣ በስስት ቃላቶቻቸውን እየጠጡ በሀሴት ያቃትታሉ…
ሁሉንም የሰይጣን መስህቦች፣ የኀጢአትን ቁንጅናና አሰቃቂውን የሴትነት ቅርጽ አስደናቂ ሞገስ ከገለጹ በኋላ ሽማግሌው ሰይጣንን ረግመው፣ ዘወር ብለው ትንሿ ክፍላቸው ውስጥ ራሳቸውን ዘጉ…  
ጥዋት ከትንሿ ክፍላቸው ሲወጡ በገዳሙ አንድም መነኩሴ አልነበረም፤ ሁሉም ወደ ከተማው አምልጠዋል፡፡

Read 1273 times