Sunday, 19 February 2017 00:00

የአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች በትራምፕ ላይ ክስ መሰረቱ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

  የትራምፕ ጉብኝት እንዲሰረዝ በ1.8 ሚ እንግሊዛውያን የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

    ሃርቫርድ፣ የል እና ስታንፎርድን ጨምሮ 17 የተለያዩ የአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች፤ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ያስተላለፉትንና በፍርድ ቤት የተያዘውን የጉዞ ገደብ ትዕዛዝ በመቃወም ክስ መመስረታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ትራምፕ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያስተላለፉት ትዕዛዝ፣ ከመላው አለም የሚመጡ የነገዋ አለማችን መሪዎችን ተቀብለን እንዳናስተምር እክል የሚፈጥር ነው፤ በጽኑ እንቃወመዋለን ሲሉ ዩኒቨርሲቲዎቹ በጋራ በመሰረቱት ክስ መግለጻቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡ ክልከላው ሰዎች በነጻነት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡና እንዳይወጡ በማገድ በአለማቀፍ ተማሪዎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ ችግር ከመፍጠሩ ባለፈ፣ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በአለማቀፍ ደረጃ ብቁ የተማረ ሃይል ለመፍጠርና ነጻ የሃሳብ ልውውጥን እንዳያደርጉ የሚገድብ ነው ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ በኒውዮርክ በሚገኝ የፌዴራል ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መግለጻቸውንም አስረድቷል፡፡
ባለፈው አመት ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የአለማችን አገራት ተማሪዎች በአሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ የጠቆሙት ዩኒቨርሲቲዎቹ፤ 20 በመቶው ተማሪዎቹ የውጭ አገራት ዜጎች የሆኑትን የል ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ብዙዎቹ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የውጭ አገራት ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች እንዳሏቸው የጠቆመው ዘገባው፤ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፔንሲልቫኒያ እና ብራውን ክሱን ከመሰረቱት ሌሎች የአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ እንግሊዛውያን ፊርማቸውን በማሰባሰብ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በቅርቡ አገሪቱን ለመጎብኘት የያዙት እቅድ እንዲሰረዝ ያቀረቡት ጥያቄ በአገሪቱ መንግስት ውድቅ መደረጉ ተዘግቧል፡፡
“የትራምፕ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክር አስፈላጊ ሁነት በመሆኑ ጉብኝቱ እንዲሰረዝ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል፤ ጉብኝቱ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት ይከናወናል” ሲል የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባለፈው ማክሰኞ ባስተላለፈው መልዕክት፣ በይፋ ማስታወቁን ዋሽንግተን ታይምስ  ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የትራምፕን ጉብኝት በተያዘለት ዕቅድ ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም ቢሮው ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ትራምፕ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጉብኝቱን ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፤ ባለፈው ወር በአሜሪካ ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አገሪቱን እንዲጎበኙ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ትራምፕ ጥያቄውን መቀበላቸውን ተከትሎ፣ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተቃውሟቸውን በመግለጽ ጉብኝቱ እንዲሰረዝ መጠየቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ ፓርላማ በመጪው ሳምንት በጉዳዩ ላይ ተከራክሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ቀጠሮ ቢይዝም፣ ቢሮው ባወጣው መግለጫ ጥያቄው ውድቅ መደረጉን አስታውቋል፡፡

Read 4963 times