Saturday, 25 February 2017 12:57

ሀዋሳ … ቆንጆዋ ግጥም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

ባለ ብዙ ቀለም አበባ፣ በአንድ ክር እንደታሰሩ ዥንጉርጉር ዶቃዎች መልክ፣ እንደ ፍንድቅድቅ ሸጋ እመቤት ናት፤ ሀዋሳ...! እንደ ግጥም ባለ ዜማ፣  እንደ እሸት ደማም ስንኝ፣… እንደ ረግረግ ልብ፣ እንደ ዳንሰኛ ስሜት!...እንደምታሸበሽብ ዘማሪ!!
ሀንት ግጥምን፤ ‹‹Passion for truth, beauty, and power!›› ይሉታል፡፡ …ሎረንስ ፔረኒ ደግሞ ለትልቁም ለትንሹም ለጄኔራሉም፣ ለተራ ወታደሩም፣ ለንጉሱም ለሎሌውም ጣፋጭ ጣዕም!... የነፍስ ዳንስ ---- እንደሆነች ይናገራሉ፡፡… ደግሞ እንደ ዝማሬ ወፍ ይቆጥራታል- ሼሊ!
እኔ ሀዋሳን ግጥም ልላት የዳዳኝ፣ ፅጌሬዳ መልኳ፣ ክርክም ስንኝ የመሰሉ ጎዳናዎችዋ፣ ሽቅብ እያቀኑ ያሉ ሕንፃዎችዋ አይደሉም፡፡… ይህን ያስታወሰኝ የመንግሥቱ ለማ፣ ግጥምን ከጥርሶች ድርድር ጋር ያዛመዱበት ሀሳብ ትዝታ ነው፡፡  ‹‹የላይና የታች ጥርሶች ሲጋጠሙ፤ የአፍን መግጠምና የመልክን ውበት መስተካከል እንደሚያስከትሉ፣ እንደዚሁም የላይና የታች ስንኞች ሲጋጠሙ የድርሰቱን መግጠምና መስተካከል ሊያስከትሉ ይችላሉ›› ብለዋል፡፡
ሀዋሳ እንዲህ ናት፤ ጥርሶችዋን በወጉ የደረደረች ብቻ ሳትሆን… ሳትታክት ፍቃ ያሳመረች ውብ!... ሀዋሳ ሸጋ እመቤት ብቻ አይደለችም፤ እንደ እናት ጡቶችዋን ለወደዳት ሁሉ የምታጠባ… ገላዋ በሽቶ ጣዕም የጣፈጠ፣ ዐይኖችዋ እንደ ኳስ እየተንከባለሉ፣ ከላይና  ከታች ኩልዋን ግጥም አድርጋ የተኳለች ሴት ወይዘሮ ናት፡፡… እንደ ኮረዳ አትቀብጥም፤ የሠከነ ቁመና፤ የሚጣፍጥ የተፈጥሮ ዜማ አላት፡፡… ጎንዋ ላይ ሻጥ ያለው ሀይቅ፤ በዳክዬ በዓሳና በሌሎች አዕዋፋት ዜማ ደምቋል፡፡
ጎዳናዎችዋ ካንዱ ጥግ ሆነው ሲያዩት፣ ሌላው ጥግ ድረስ ያለው መስመርና ንፅህና በእጅጉ ይማርካል፡፡ ሕንፃዎችዋ፤ እንደ አዲስ አበባዎቹ ከደመና ጋር ከንፈር ለከንፈር ባይሳሳሙም፣ በልከኛ ቁመና፤ በንፅህናና በዕፅዋት መጎናፀፊያ ድባብ ፈፅሞ ተመራጭ ናት፡፡ መንገዶችዋ አንድም ቦታ ወጣ ገባ አይደሉም፤… የትም ቦታ የውሃ ፍሣሽ መውረጃዎችዋ፣አፍንጫ የሚያሲይዝ ጠረን የላቸውም፡፡… የመንገዱ ስፋትና በመንገዱና በህንፃዎቹ መካከል ያለው ከፍት ቦታ፤በአትክልት መዋቡ ልዩ ጌጥና ሞገስዋ ነው፡፡
ለትራንስፖርት ባጃጆች፣ ታክሲዎችና የከተማ አውቶቡሶች አሏት፡፡ …ሌላው የተለየ ነገርዋ፤ በየመንገዱ የሚለምኑ ሰዎች፣ ሰካራሞች ዕብዶች ወይም በተለያዩ ሱሶች የፈዘዙ ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶቹ አይታዩም፡፡፡… ከረጂም ዓመት በፊት በጣት የሚቆጠሩ የጎዳና ልጆች አይቼ ሥጋቴን በጋዜጣ ላይ ገልጬ ነበር፤… ይሁንና ዛሬ የለም። ይህም ምናልባት፤ የአስተዳደሩ፣ የማህበረሰቡና የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ ሊጨበጨብለት የሚገባ ትልቅ ተግባር ነው፡፡
ብዙ ጊዜ እንደሚታየው ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች፣ ከከተሞች ጋር እንደ ጥፍር አድገው የሚቧጭሩ የልማትና የዕድገት እንቅፋቶች ናቸው። ለነዚህ ደግሞ መድሃኒቱ በትብብር፤ በማህበረሰብ ተሳትፎ ነገሮችን በእንጭጩ መቀየር ነው፡፡ ከዚያ ካለፉ ግን በየትኛውም ሁኔታ ህሊናን ቧጫሪና፣ የሠቀቀን ምንጮች፣ ትልልቅ ሰዎችን በለጋነት የሚቀጩ የህልም መጨንገፊያ ናቸው፡፡
አርስቶትል እንደሚለው፤ከተሞች ሰዎች ጥሩ ሕይወት ለመኖር የሚሰበሰቡባቸው አምባዎች ናቸው፡፡ እንደ ግጥም በምጣኔ የተደረደሩ፣ በዜማ የደመቁና፣ በዘይቤ ከፍ ያሉ ከተሞች፤ ለነዋሪዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ዕድገትና ለቱሪዝም መስህብ የሚኖራቸው ሚና ቀላል አይደለም፡፡
በየመንገዱ የውጭ ሀገር ዜጎችን እግር እየተከተሉ መለመን፣ ብዙ አይታይም፡፡… እንግዳ የሚሳደብ፣ ልጃገረድ የሚላከፍ፣ እጁን የሰው ኪስ ውስጥ የሚሰድ፣ በአይን አውጣነት እንግዶችን የሚያሳቅቅ -ወሮ በላ- አልገጠመኝም፡፡ ይልቅ መንገድ ሲጠይቋቸው በትህትና የሚያሳዩ፤… ዐይን ላይን ሲገጥሙ አፀፌታቸው ፈገግታ የሆኑ ብዙ ሰዎች አይቻለሁ፡፡… መንገድ ለሚያቋርጥ ሰው ቅድሚያ የሚሰጡ የሞተር ብስክሌትና የባጃጅ አሽከርካሪዎች ብዙ ናቸው፡፡… መቸም አንዱ የሀዋሳ ድንቅ ነገር ሴትና ወንዱ፣ አባወራውና እማወራው ሞተር ብስክሌት ማሽከርከራቸው ነው፡፡
ብቻ የዛሬዋ ይህቺ እሸት ከተማ ነገ፣ በአፍሪካ ደረጃ ‹‹ታላቅ›› መባልዋ ብዙም የሚያጠራጥር አይደለምና ለሃገሪቱ ቱሪዝም፤ ለህዝቡ ኑሮ መለወጥ ሕልም እንዳረገዘች ለማመን አያዳግትም፡፡ ከተሞች ካላደጉ ህብረተሰብ አያድግምና ሁሉም ጭንቅላቶች በዚህ ጉዳይ መስራት አለባቸው፡፡… የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሊንደን ቢ ጆንሰን እንዳሉት፤ ‹‹…our society will never be great until our cities are great!››
አንድ ህብረተሰብ ከፍ የሚለው ከተሞቹ ታላላቅ ሲሆኑ ነው፤ በዚያ ደግሞ በምጣኔ ሀብታዊ ስነልቡናዊ፣ በማህበራዊ ዘርፎችና በሌሎችም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ ታዲያ ለዚህ ጆንሰን የሚሉት፤ ‹‹It will be our task…” ነው፡፡ ለመጨመር፤ “Not only to live, but to live the good life››
ሀዋሳ በተፈጥሮ ዕጣ የወጣላት ናት፡፡… ምክንያቱም ጉያዋ ሥር ሀይቅ አለ፡፡ ሀይቅ ደግሞ መዝናኛ ነው፡፡ ውበት ነው ፡፡… የአዳም ልጆችን ሁሉ ያማልላል፤ በፉጨት ይጠራል! እነዚህን ሀይቆች እንደ ንብ የከበቡ አሉ፡፡ ሁለት ትልልቅ ሪዞርቶችና ሌሎች የመዝናኛ አገልግሎቶች፡፡… አንዱ የአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሪዞርት ሲሆን በሌላው ወገን ደግሞ ሌዊ ሪዞርት አለ፡፡… የአሞራ ገደልም አንዱ የሃይቁ ትሩፋት ነው፡፡ ዓሣ ማሥገር፤ ዓሳ መጥበስ፣ የዓሣ ሾርባ ማምረት አለና!
የኃይሌ ሪዞርት አንድ ትልቅ ህንፃ ያለው፣ በስተጀርባ ሃይቁ አጠገብ ደግሞ ትልቅ ዋርካ አለው። እዚያ ዋርካ ስር ምቹ ወንበሮች አሉ። ወረድ ሲል የተፈጥሮ፣ አሸዋ አለ፤… እዚያ ቋሚ ጃንጥላዎች ተተክለው፣ ወንበሮች ተደርድረዋል፡፡ ወደ ጎን እንዲሁ የተለቀቀ ሳር የለበሰ ምድር ይታያል።… ይሁንና ከዋርካው ሥር የረገፉት ቅጠሎች ያለመጽዳታቸው የሚፈጥረው ጥሩ ያልሆነ ስሜት አለ፡፡ ወረድ ብሎ ያለው አሸዋማ ሥፍራ ላይ ፈረሶች ባይሠማሩ፣ ለጤና ጥሩ ሲሆን ለደንበኛም ምቾት ይፈጥራል፡፡
ሌዊ ሪዞርት ከግቢው መግቢያ ጀምሮ በጥሬ አለቶችና በተፈጥሮ ቁሳቁሶች የተሰራ ነው፡፡ ወደ ግቢም ሲገባ፤ እጅግ የሚያምሩና በተለያዩ ዲዛይኖች የተሰሩ መዝናኛዎች፤ ቡቲኮች… አሉት፡፡ የደመቀ ህንፃም እንደዚሁ!... ከግቢው በር የሚጀምረው፣ የክብ ቤቶች ድርድር፤ ግራና ቀኙን አጅቦ ሃይቁ ዳር ያደርሳል፡፡ ውበቱ ብቻ ሳይሆን ንፅህናው ይገርማል!.... ሀይቁ ዳር… በመረባማው ሽቦ የታሠሩ ድንጋዮች፤ የሀይቁን ኩሩፈር ይዘውታል፡፡ ሀይቁ በእጅ የሚነካ ያህል ቅርብ ነው፡፡ በሁለቱም በሶስት ሜትር ቅርበት፣ የዳክዬዎችን ዋና ተመሥጦ ማየት ይቻላል፡፡ የሚዋልለው ሀይቅም  ዜማ፣ ማዶውን ካሉት አረንጓዴና ሰማያዊ መሠል ኮረብታዎች ጋር ተሸምኖ፣ አንዳች የውበት ምትሀት ይፈጥራል… ሁሉም ነገር ይዘምራል - ሰማዩ…መሬቱ… ደመናው… ዳክዬዎቹ… የሞተር ጅልባው ድምፅ ሙዚቃውን ያጅባል፤ ያዚያ ሁሉ ቅኝት ድምር ጥርቅም- ሃሌሉያ ለነፍስ!
ከዐመታት በፊት ባሣተምኩት መጽሐፍ ስለ አሞራ ገደል እንዲህ ሰፍሯል፡-  
የውሃው ድምፀት ቱማታ፤
በዐረፋ መዳፍ ጥፊ
የሀይቁን ከንፈር ሲመታ
ቄጠማው ባፍጢሙ ወድቆ
ከእግሮችሽ ስር ሲማፀን
ቃፊር የቆሙ ቋጥኞች
ተከበው በብርሃን ወጋገን…
ይህ ከዐመታት በፊት ለሀዋሳ ሀይቅ ውበት የተፃፈ ግጥም ነው፡፡ ዛሬ ይህንን የውበት ባንዲራ፣ ሌዊ ሪዞርት አድምቆ አውለብልቦታል፡፡
ክንፍ ይተክላል፡፡
ኦሶ- ሃዬ-ሃዬ
ኦሶ-ሃዬ-ሃዬ
ኦሶ - ዲገና
ኦሶ - ዲመና
እንደሚለው---- የሲዳሞኛ እሸሩሩ ዜማና ግጥም አይነት፣ ሌዊ ከሀዋሳ ከተማ ጀርባ ላይ በአንቀልባ የተቀመጥኩ ያህል ተመችቶኛል፡፡ ሀዋሳ አረንጓዴ የተጎናፀፈች፤ እፀዋት የተሸለመችና የተረጋጋ ድባብ ያላት፤ ሠላማዊ ከተማ ናት፡፡ ይህን ሳይ ምናልባትም ስለ አረንጓዴ ቀለም አንድ ያነበብኩት መፅሀፍ ትዝ ይለኛል፡፡ መጽሐፉ እንዳወጋኝ፤ ለራስ ምታትም መድህን ሳይሆን አይቀርም፡፡ “The Clam green light is an excellent remedy for headache” እንደሚሉት፡፡ … ታዲያ አረንጓዴ መብራት፣ አረንጓዴ አትክልት (ለምግብነት) አረንጓዴ ጨርቅ (ልብስ) አረንጓዴ ጌጣጌጥ ተጠቀሙ በሚል ባለሞያው ያሰመሩበትን ሀዋሳ በአረንጓዴ ዛጎል አሸብርቃ፣ በሀይቆች ዳንስ፣ …. በእናትነት ዝማሬዋ (እሹሩሩ) እያለች፣ አሶ - ሀዬ - ሀዬ -
ኦሶ - ዲገና
ኦሶ ዲመና ብላናለች፡፡ (“እሽሩሩ…ማሞ እሽሩሩ ዓይነት!...ልጅ አይመታም እያለች)
በመስተንግዶዋ፣ በውበትና ዜማ፣ በጣፋጭ ግጥምነትዋ የተጎናፀፍኩትን ኃያል መንፈስ፣ ሊበክሉ የሞከሩ ነገሮች እንዳሉ ግን ጠቆም ማድረግ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ያሞራ ገደል በሚለው የተከለለው ግቢ ብዙ ነገር ሊሰራበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ተፈጥሮ የቸረችው ውበት፣ የእነዚያ ግዙፍ ዛፎች ጥላ እንዳለ ሆኖ፣ በውስጡ በርካታ ነገሮች ሊገነቡ ይገባ ነበር፡፡ … ለምሳሌ የባህል ቤቶች፤ የልጃገረድ የሉጫ ፀጉር ክርክም የሚመስሉት እነዚያ ውብ ባህላዊ ጎጆዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ዳርና ዳሩ የተፈጥሮ ድንጋዮች ተደርድረው፣ በስነ ልቡና ምሁራን ምክር በተደገፈ ሁኔታ ቀለሞች ተነክረው፣ ጠርዝና ጠርዙን ቢያሳምሩ ደስ ይላል፡፡
ሀዋሳን ውስጡ ጣፋጭ ጮማ ያለው ሸንኮራ ሳይሆን ውጭው የሚያምር ሸንበቆ እንዳያደርጋት የፈራሁት ነገር አለ፡፡ … የሆቴሎች የመስተንግዶና የተግባቦት አቅም! … ይህ የሀዋሳ ትልቁ ክፍተት ነው። አብሮኝ ከነበረውና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ካለው ወዳጄ ጋር ባሳለፍናቸው ቀናት፣ መስተንግዶው በእጅጉ ቅር ብሎናል፡፡ ለኛ አይደለም፤ … ሀዋሳ የሀገራችን ውብ ከተማና የቀጣዩ ዘመን ፀሐይ ናትና … ሌሎች እንግዶች እንዳያዝኑ ሰጋን! … የሀገር ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ራቅ ካሉ አህጉራት የሚመጡ!
ትልልቅ የተባሉትን ሆቴሎች ሁሉ ዐይተን ነበር። ቅልጥፍናና መስተንግዶ በጣም በጣም ደካማ ነው። … ያንንን በመሰለ ውበት ውስጥ፣ … የዚህ ዓይነት ክፍተት ሊኖር አይገባም፡፡ … ሰራተኞች ለንቃት አንገታቸው ላይ ቃጭል ባይታሰርም፣ ተከታታይ… ስልጠና ሊሰጣቸውና የተሻለ አገልግሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል፡፡ … አሮስቶ ያለ ሹካና ቢላ ማቅረብ፣ … “ስቴኪኒ … ላገኝ አልቻልኩም ይቅርታ!” ብሎ መመለስ፣ እስከነ ጭራሹ ኮከብ ነን የሚል ስም ይዞ እንግዶችን ለመታዘዝ ብቅ ያለማለት፣ የግጥሙን ዜማ ይሰብራል፡፡ የወይዘሮዋን ውበት ያቃልላል፡፡…
የባጃጆቹ በኮንትራት ወደ ሪዞርቶች የመሄድ ፍቃድ ያለማግኘት የፈጠረውም ችግር አለ፡፡ ለኮንትራት ሥራ ሥምሪት መጠየቅ እንግዶችን አያጉላላምን?
… ቢሆንም ሂጌ ማ አስናÀ
ቄሴ ዲገናÀ - ነውና ነገሩ! … ሀዋሳዎችን - ብሩክ ሁኑ! … ሃዋሳም ሰላምሽም ይብዛ … እላለሁ፤ ሻሎም!

Read 6149 times