Sunday, 26 February 2017 00:00

የ4 አገራት 20 ሚ. ዜጎች ለከፋ ርሃብ ሊጠቁ እንደሚችሉ ተመድ አስጠነቀቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   4.4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፣ የተገኘው 90 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው

      አለማቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ በተለያዩ አራት የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 20 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለርሃብ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ረቡዕ አስጠንቅቋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ሁለት ግዛቶች 100 ሺህ ሰዎች የርሃብ ተጠቂ መሆናቸውን ከቀናት በፊት በይፋ ያስታወቀው የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በሶማሊያ፣ የመንና ናይጀሪያ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የከፋ ርሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡ ከከፋ ድርቅና ከእርስ በእርስ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በተጠቀሱት አገራት ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀውን የርሃብ አደጋ ለመከላከል አለማቀፉ ማህበረሰብ በመጪዎቹ ሶስት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ርብርብ በማደረግ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ማሰባሰብ እንዳለበትም ዋና ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡
7.3 ሚሊዮን ያህል የመናውያን አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያለው ተመድ፣ በደቡብ ሱዳን 5 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚፈልጉ፤ በሰሜን ምስራቃዊ ናይጀሪያ 5.1 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ እጥረት ተጠቂ እንደሆነ፤ 2.9 ሚሊዮን ሶማሊያውያን አስቸኳይ የምግብ እና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ተመድ ለተጠቀሱት አራት አገራት የሚያስፈልገውን 4.4 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ያደረገው ጥረት ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማግኘቱንና እስካሁን ድረስ ማግኘት የቻለው 90 ሚሊዮን ዶላር ያህል ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ጸሃፊው፣ አለማቀፉ ማህበረስብ በአፋጣኝ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

Read 1145 times