Monday, 06 March 2017 00:00

የቀላል ባቡር አገልግሎት እስካሁን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ መግባት አልቻለም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   ባቡሮች በየፌርማታው በየ6 ደቂቃ ይደርሳሉ የተባለው የረጅም ጊዜ እቅድ ነው ተብሏል
                    አሁንም አገልግሎት የሚሰጡት ግማሽ ያህል ባቡሮች ናቸው
                  የባቡር ሹፍርናውን ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያውያን ተቆጣጥረውታል
     አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ የሆነው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፤ በእቅዱ መሰረት ሙሉ አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩ ተገልጋዮችን እያማረረ ሲሆን የባቡር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅቱ፤ የተለያዩ ተግዳሮቶች ስላጋጠሙኝ ነው አገልግሎቱን እስካሁን ያላሟላሁት ብሏል፡፡
አገልግሎቱ ሲጀመር ባቡሮች በየ6 ደቂቃው በየፌርማታው ይደርሳሉ፣ የኤሌክትሮኒክ ቲኬት አገልግሎት ላይ ይውላል፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች የሊፍት አገልግሎት ይቀርባል… የሚለው የት ገባ ስንል የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ሙሉ ምክንያቶችን አስረድተዋል፡፡
“ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች አገልግሎት እንዲሰጡ የተገነቡ ሊፍቶችን በተመለከተ ምላሽ መስጠት ያለበት የግንባታው ባለቤት ባቡር ኮርፖሬሽን መሆኑን የጠቀሱት አቶ አወቀ፤ “እኛም እንደተገልጋዩ ሊፍቶቹ አገልግሎት እንዲጀምሩ በጉጉት እየጠበቅን ነው” ብለዋል፡፡
የባቡር ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አንድ ሰው ፌርማታ ላይ ባቡር የሚጠብቀው 6 ደቂቃ ብቻ ነው የሚል እቅድ የተቀመጠ ሲሆን አቶ አወቀ ይህ እቅድ የረጅም ጊዜ ግባችን ነው፤ አሁን አገልግሎት እየሰጠን ያለነው ከ15-20 ደቂቃ ባለው ውስጥ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ተገልጋይ በሚበዛባቸው ሰዓት በ15 ደቂቃ ልዩነት፣ በማይበዛባቸው በሰዓት በ20 ደቂቃ ልዩነት ባቡሮች በየፌርማታው እንዲደርሱ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አወቀ፤ ቃል በተገባው መሰረት በየ6 ደቂቃ አሁን ላይ ማድረግ ያልተቻለው የከተማዋ የመኪና የትራፊክ ፍሰት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡ በከተማዋ የትራፊክ ደህንነት አስተማማኝ አለመሆኑን በምክንያትነት የጠቀሡት አቶ አወቀ፤ አሁን ባለው አገልግሎት እንኳ በተደጋጋሚ በባቡር መስመሩ ላይ መኪኖች አደጋ እያደረሱ ነው፤ ይሄ ባለበት የባቡሮች ፍጥነት ብንጨምር የበለጠ አደጋ ይፈጠራል የሚለ ስጋት አለን ብለዋል፡፡
የባቡር አገልግሎት ሲጀመር በ41 ባቡሮች እንደሚሰማሩ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን እስካሁን ግማሽ ያህሎቹ ብቻ አገልግሎት እየሠጡ እንዳሉም ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ቲኬት ይጀመራል የሚል ተደጋጋሚ መግለጫዎች ሲሰጡ ቢቆይም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ “በ24 ፌርማታዎች ላይ የሂሳብ መሙያ ማሽኖች ተተክለው፣ ባቡር ውስጥ ካለው ሲስተም ጋር የመናበባቸው ሁኔታ ሙከራ እየተደረገበት ነው፣ በቅርቡ አገልግሎቱ ይጀምራል” ያሉት አቶ አወቀ፤ የዘገየውም አሰራሩ ውስብስብነሳ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የትራንስፖርቱ አገልግሎት ፈላጊ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ቢሆንም የባቡር አገልግሎቱ አቅሙን ማሳደግ አለመቻሉም ታውቋል፡፡ ባቡሩ ሲጀምር በቀን እስከ 120 ሺህ ሰው እያጓጓዘ እስከ 400 ሺህ ብር ያስገባ የነበረ ሲሆን አሁንም በዚሁ ደረጃ ላይ መሆኑን አቶ አወቀ አስረድተዋል፡፡ የተገልጋዩ ቁጥር እንዲጨምር የባቡር ቁጥር መጨመርና የቲኬት ቁጥጥሩንም ማጥበቅ እንደሚያስፈልግም ሃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በከተማ የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያን ባለሙያዎች የሚሽከረከሩ ሲሆን ቻይናውያን የአሽከርካሪነቱን ቦታ መልቀቃቸውን ሃላፊው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን ያመለከታሉ የተባሉትን የስካሌተሮችና ሊፍቶች ስራ አለመጀመርና የብድር አመላለስን በተመለከተ፣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ደረጀ “የመስክ ስራ ላይ ነኝ፤ ወደ ቢሮ ስመለስ መረጃውን ማግኘት ትችላላችሁ” በማለታቸው ለዚህ ዕትም ሳይደርስልን ቀርቷል፡፡

Read 1876 times