Monday, 06 March 2017 00:00

መፍትሄ አልባው የሞክሼ ሆሄያት ክርክር ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ ሠ፣ ሰ፣ አ፣ ዐ፣ ጸ፣ ፀ

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(14 votes)

  ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዳላት የፊደል ሀብት፣ የኪነጽሑፍ ቅርሷ የዳበረ እንዳልሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ልሂቃን በተደጋጋሚ ገልጸል፡፡ ምንም እንኳን ከፊደል ሀብታችን ጋር የሚተካከል የተጋነነ የጽሑፍ ቅርስ ባይኖረንም፣ ሊቃውንት ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው፣ የተጠበቡባቸው እፍኝ የማይሞሉ የኪነ-ጽሑፍ ቅርሶች፣ ገሚሶቹ በባዕድ ወራሪ ኃይል ተዘርፈው፣ የምዕራባዊያን ሙዚየም ማድመቂያ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ለምርምር አመቺ ባልሆነ መንገድ በየአድባራቱ ተሽሽገው ይገኛሉ። የእዚህ ጽሑፍ የትኩረት አቅጣጫ ማጠንጠኛ ከእዚሁ ማዕቀፍ ጋር ተያያዥነት ስላለው፣ የፊደል ቅርሳችን አንድ ሁለት ነጥቦችን መሰንዘር ይሆናል። መጣጥፉን ለመከወን በዋንኛነት ዋቢ ያደረግኩት ደግሞ የዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ “የአማርኛን ሞክሼ ሆሄያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ” የሚለው መጽሐፍን ነው፡፡
ሻማ ቡክስ ለህትመት ብርሃን ያበቃት ይህቺ ኩርማን የጥበብ ሥራ፤ ለዓይን የሚሞላ ቁመናን ባትላበስም የምታነሳቸው ቋጥኝ ፍሬ ሐሳቦች ግን ከአንጀት የሚጠጋ እንደሆነ ለመገምገም ጥቂት ገጾችን ብቻ መጎብኘት በቂ ይሆናል፡፡ መጽሐፏ በ139 ገጾች፣ በመዳፍ ልክ በተከረከመ ቁመና ለመያዝ አመቺ በሆነ መንገድ ነው የተሰናዳችው። ፊት ለፊት ባሉት ምዕራፎች ላይ የሞክሼ ሆሄያት ውዝግብን ሥረ መሠረት ለመገምገም ያመች ዘንድ ታሪካዊ ዳራውን በወፍ በረር ያስቃኘናል። ብዙም ሳያረፋፍድ ትክክለኛ የሆሄያት አሰካክን ተከትሎ ለመጻፍ የሚረዳ ማንዋል ማመሳከሪያን በማሳረጊያው አኑሮ ይደመድማል፡፡
በፊደል ገበታችን ላይ ከተሰለፉት ሆሄያት መካከል ጸሓፍትን የሚያጥበረብሩት ሞክሼ ሆሄያት፣ ሀሐኀ፣ ሠሰ፣አዐ፣ ጸፀ እንደሆኑ ይታወቃሉ። እያንዳንዱ ሆሄ የራሱ ስያሜ አለው። ሀ= ሃሌታው ሐ= ሐመሩ ኀ=ብዙኃን ሠ=ንጉሡ ሰ=እሳቱ አ=አዳም ዐ=በግዑ ጸ=ጻድቅ ፀ=ፀሐይ ተብሎ ይጠራል፡፡
የሞክሼ ሆሄያቱን ታሪካዊ ዳራ፣ በገጽ 11 ላይ በሚከተለው መልኩ ተብራርቷል፡፡
ግዕዝ የሳባውያንን ፊደል ሲወርስ በጅምላ ሁሉንም አልወረሰም፤ ለድምፅ ልሳኑ የሚያገለግሉትን ብቻ ነው የወሰደው። በሳብኛ ቋንቋ የነበሩ ግን ለግዕዝ ምንም አገልግሎት የማይሰጡትን 5 ፊደሎች ጥሏቸዋል፡፡ አማርኛ ግን የግዕዙን ፊደል ሲወስድ ለድምጽ ልሳኑ የሚያገለግሉትን ብቻ መርጦ በመወሰድ ፋንታ ሁሉንም በጅምላ ወስዷቸዋል፡፡ በአማርኛ ሞክሼ ሆሄያትን ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግር የተነሣው ከዚህ ጋር በመያያዙ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
ሞክሼ ሆሄያቱን በመጠቀም ዙሪያ ያለው አመለካከት፣በሁለት ጽንፍ ጎራ የተከፋፈለ ነው። አንደኛው ጎራ ሆሄያቱን በአጻጻፍ ስርዓት ጊዜ ከሚፈጥሩት ሳንካ አንጻር በመገምገም፣ ከፊደል ገበታ ላይ መሰረዝ እንደአለባቸው አጥብቆ ይሞግታል፡፡ ከዚህ ወገን ከሚደመሩት ምሁራን መካከል የአዲስ አበባ ዩነቨርስቲ የሥነ ልሳን ባለሙያው ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ይገኙበታል። ምሁሩ ከዚህ ቀደም በ2006 ዓ.ም ሚዩዚክ ሜይዴይ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያለው ጠንከር ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡
ፊደል መጣል፣ መጨመር በቋንቋ ስርዓት ውስጥ የተለመደ ክስተት ነው፡፡ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት በፊደል ገበታቸው ላይ አለምክንያት የተሰለፉትን ሆሄያት እንደየአስፈላጊነቱ በየጊዜው እያስወገዱ ቋንቋቸውን ለማዘመን ችለዋል፡፡ የእኛም ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ አውድ ውጭ ሊወድቅ አይችልም፡፡ ለአሠራር ሳንካ በሆኑት ሞክሼ ሆሄያት ላይ አፋጣኝ ውሳኔ ለማስተላለፍ የሚመለከታቸው አካላት በተገቢው ደረጃ ሊመክሩ ሊዘክሩ ይገባል፡፡ በዚህ መሰሉ ውሳኔ ወደ ተግባር መግባት ለቋንቋችን የሚያበረክተው ፋይዳ የላቀ እንደሚሆን፣ በጥናታዊ ጽሑፍ አጽንኦት ተሰጥቶት ተብራርቷል፡፡ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ በዝነኛው “ፍቅር እስከ መቃብር” ልብወለድ ላይ ሲጠበቡ፣ ከሞክሼ ሆሄያቱ መካከል አንደኛውን ብቻ በወጥነት ለመጠቀም የወሰኑት አለምክንያት አልነበረም፡፡ የሞክሼ ሆሄያቱ ያለበቂ አምክንዮ ለቁጥር ጨዋታ ብቻ በፊደል ገበታችን ላይ መደንቀር፣ ረብ እንደሌለው በመላ ማመላከታቸው እንደሆነ ከምሁሩ ማብራሪያ  ተደምጦ ነበር፡፡
ከዚህ በመለስ ለሞክሼ ሆሄያቱ ህልውና አጥብቀው ከሚከራከሩት ወገኖች የሚቀርብ ጠንካራ ጥናታዊ ሥራ እምብዛም አይስተዋልም። ውዝግቡ እስካሁን መቋጫ ሳይበጅለት በዝብርቅርቁ አጻጻፍ ባህል እንደተቀየድን  እንገኛለን፡፡
የዶ/ር አክሊሉ መጽሐፍ፤ ለዚህ ውዝግብ ማሳረጊያ ሊሆን ይችል ስለነበረ፣ ወሳኝ ታሪካዊ ኩርባን በገጽ 10 ላይ ያመላክተናል፤
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መርሐ ልሳን፤ በ1973 ዓ.ም ካወጣው የአጻጻፍ ሥርዓት ውሳኔ በስተቀር ሌላ ወሳኝ ጥናት ባለመደረጉ፣ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ መምህራንንም ስለዚህ ጉዳይ ሆን ብሎ ያስተማራቸው ሰው ባለመኖሩ እነሱ እራሳቸው በዘፈቀደ ስለሚጽፉ፣ ተማሪዎቻቸውም የነሱን ፈለግ በመከተል በዘፈቀደ ይጽፋሉ፡፡ እላይ ስሙን የጠቀስኩት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መርሐ ልሳን፣ ይህን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ረጅም ጊዜ የፈጀ ጥናት አካሂዶ ውሳኔም አስተላልፎ ነበር፡፡ ይህ ውሳኔ የተላለፈበትም ወቅት የደርግ የሥልጣን ዘመን ስለነበር ወሳኞቹ ደርግ ብዙ ቆራጥና ሥር ነቀል ውሳኔዎችን ያሳለፈ መንግሥት ስለሆነ፣ ይህንንም ውሳኔ ደግፎ ያወጣዋል የሚል እምነት ነበራቸው፤ ሆኖም ግን የመርሐ ልሳኑ ውሳኔ ለኢሠፓ ቢሮ ከሽኚ ደብዳቤ ጋር ቢላክለትም፣ እንደሰማነው፣ በአንዱ ጓድ ቢሮ የጠረጴዛ መሳቢያ ውስጥ ተቆልፎበት ቆይቷል፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ የት እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
ምናልባትም ይህ ውሳኔ ከመሬት ላይ ወርዶ ቢሆን ኖሮ እየተስተዋለ ያለው ወጥነት የጎደለው አጻጻፍ ስልት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ያገኝ ነበር፡፡ ነገሩን የበለጠ ወለፈንዲ የሚያደርገው በእዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሄ የሚያበጅ አካል ከ1983 መንግሥት ለውጥ በኋላ የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ ነው፡፡ የሞክሼ ሆሄያቱን ከፊደል ገበታ ላይ መፋቅ ከሀገራዊ ቅርስነቱ በዘለለ ሌላ ተጨባጭ ግልጋሎት እንዳለው የሚከራከሩት ወገኖች የሚደረድሯቸው የራሳቸው የሆነ አምክንዮ አላቸው። ከእዚህም ውስጥ አንደ መከራከሪያ የሚያነሱት ነጥብ፣ ሆሄያቱ ከሒሳባዊ ስሌትና ኮከብ ቆጠራ ጋር ያላቸው ቁርኝት ጥብቅ መሆኑን በማውሳት ነው፡፡
በእዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ ድርሳናት መካከል የይትባረክ ገሠሠ፣ በኪነጽሕፈት ጊዜ የፊደላት ሚና አንዱ ነው።
እያንዳንዱ ፊደል የራሱ የሆነ ቁጥር አለው፡፡ ለምሳሌ ፊደሉ ቁጥር ሲሆን እንደሚከተለው ይሆናል፡፡ ምሳሌውን ከእዚህ ቀጥሎ እንመልከት፡ ሀ(፩) ሐ(፫) ሠ(፬) ሰ(፯)ኅ(፳) አ(፵) ዐ(፰) ጸ(፮፻) ፀ(፯፻) እንደነዚህ ሁሉም ፊደላት ከ ሀ እስከ ፐ የየራሳቸው የተመደበላቸው መጠነ ቁጥር አላቸው።  ራሳቸው ፊደላቱ ቁጥር ናቸው። ታዲያ ይህ ቁጥር ዝም ብሎ ያለ ምክንያት ቁጥር አልተባለም። በሀገራችን በሁሉ ኅብረተሰብ ጎልቶ አይታወቅም ነበር እንጂ በምሁራኑ ዘንድ ሒሣብ  ይሠራበታል። እሱም ሐሣበ ቀመር፣ ሐሣበ ክዋክብትና ሌላም በመባል ይታወቃል።
የተለመዱ የአጻጻፍ  ግድፈቶች
ሞክሼ ሆሄያቱ በየአንዳንዱ ቃላት አጠቃቀም ውስጥ የራሳቸው የሆነ ድርሻ  አላቸው፡፡ ለምሳሌ ሕዝብ በማለት ፋንታ ህዝብ ፣ በመንግሥት ምትክ መንግስት፣ በኅብረት ፋንታ ሕብረት፣ባለሥልጣን በማለት ፋንታ ባለስልጣን ተብሎ ቢጻፍ ስህተት ነው፡፡ ይህ ለምን ስህተት ይሆናል ቢባል በአምክንዮ የተብራራ መልስ ሊኖር አይችልም፡፡ የቋንቋው ስታንዳርድ ነው ተብሎ ይታለፋል፡፡ ልክ ‘civil’ በ“sivil” ቢጻፍ ምኑ ላይ ነው ጉድለቱ ብሎ ከመጠየቅ ጋር ይመሳሰላል፡፡
 ገጽ 17
በአማርኛም ቢሆን በተለምዶ አንዳንድ ቃላትን የምንጽፍበት አንድ መንገድ ብቻ አለን፡፡ ለምሳሌ፣ ብዙ ሰው እግዚአብሔር የሚለውን ቃል የሚጽፈው በእዚህ መንገድ እንጂ እግዚአብሄር፣ እግዚአብኄር፣ ዕግዚአብኄር ወይም እግዚዐብሔር ብሎ ቢጽፍ፣ ለአንባቢው በቀላሉ እንደተለመደው እንደ እግዚአብሔር ቀና ሆኖ አይነበብለትም። ሲያነበውም ግራ ይጋባል፡፡
ናሙና ቅኝት
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ኅብረትን በብዙኃኑ “ኅ” ነው የሚገልጸው፡፡ በአንጻሩ ሕብረት ባንክ ደግሞ ሐመሩ “ሐ”ን ይጠቀማል። በአጻጻፉ ስታንዳርድ መሠረት ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ትክክለኛውን መንገድ ተከትሏል ማለት ነው፡፡
ለገሃር የሚገኘው የኢትዮጵያ ባሕር እና ትራንዚት ሎጀስቲክ ዋና መስሪያ ቤት፤ “መስሪያ” በሚለው ቃል ውስጥ እሳቱ “ሰ”ን ሲጠቀም፣ በተቃራኒው ትንሽ ከፍ ብሎ የሚገኘው የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ንጉሡን “ሠ” እናገኛለን፡፡ በአጻጻፉ ስታንዳርድ መሠረት የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ በትክክለኛው የአጻጻፍ ስርዓትን ተክትሏል፡፡
የአጻጸፍ ህጸጹ የሀገራችንን ትልቁ የትምህርት ተቋም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲንም ጎብኝቶታል፡፡ አራት ኪሎ ሳይንስ ፋክልቲ በሥላሴ ኮሌጅ በኩል ያለው መግቢያ፣ በቅርቡ ዕድሳት ተደርጎለት ነው የተጠናቀቀው፡፡ በዚህ በአዲስ መልኩ በተቀለሰው ሠፊ መዝጊያ ግንባር ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ የሚል ጽሑፍ በወርቃማ ቀለም በትልቁ ተከትቧል፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሣይንስ የሚለው ቃል፣ በእሳቱ “ሰ” ፋንታ ንጉሡን “ሠ” ነው የተጠቀመው፡፡ ማንኛውም ከአውሮጳውያን ቋንቋዎች የተዋስናቸው  ቃላት መጻፍ ያለባቸው በ “ሀ” በ”ሰ” በ”አ” እንደሆነ፣ የዶ/ር አክሊሉ መጽሐፍ በገጽ 26 ላይ በናሙና አስደግፎ ያብራራል፤
ከአውሮጳውያን ቋንቋዎች የተዋስናቸው ቃላት እንደ ዐረብኛ ዓይነት ያለ ችግር የለባቸውም፡፡
ስለዚህም በ“ሀ” በ”ሰ” በ”አ” ብቻ መጻፍ እንችላለን፣ ሊሆን የማይችለው ግን በሌሎች ሞክሼ ሆሄያት እነዚህን ቃላት መጻፍ ነው። ሳይንስ፣ ሶሻሊዝም.፣አርምስትሮንግ፣ሴኮንዶ ሚስቶ፣ ሆቴል፣ ሆስፒታል፣ ፓስታን፣ ለትክክለኛው አጻጻፍ መንገድ አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡
ለሞክሼ ሆሄያቱ ውዝግብ እስካሁን መፍትሄ መስጠት አልተቻለም፡፡ ለችግሩ መቋጫ ለማበጀት ሁለት አቅጣጫዎችን መከተል ይቻላል፡፡ የሆሄያቱ ተገቢ አጠቃቀም እንዲተገበር፣ ከታች የትምህርት ተቋም አንስቶ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድረስ በደንብ ታስቦበት መሄድ፡፡
ይህ አመክንዮ የደፋ መስሎ ካልታየ፣ ልክ የ1973 ዓይነት ውሳኔ ሰጪን ቡድን አቋቁሞ፣ መጠነ ሰፊ ሥራ ለመሥራት መንቀሳቀስ ተገቢ እርምጃ ይሆናል፡፡

Read 7550 times