Monday, 13 March 2017 00:00

አንድም ሦስትም ልቦና፡- (ግዮንአዊ ፍልስፍና)

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(12 votes)

 የግሪኩ አንጋፋ ፈላስፋ አፍላጦን /Plato/ ፍትህ ምን ማለት እንደሆነ በሚተነትንበት ድርሳኑ /The Republic/ ውስጥ ሁለት ዓለማት መኖራቸውን፣ እነርሱም ዓለመ አምሳያ እና ዓለመ ህላዌ መሆናቸውን ይገልፃል። ዓለመ ኅላዌ እውነት፣ ውበት፣ ፍትህ፣ እውቀት መገኛ እንደሆነና ዓለመ አምሳያ ደግሞ የዓለመ ኅላዌ ቅጅ፣ ጥላ፣ ግልባጭና አምሳያ መሆኑን የሚገልፀው ፕሌቶ፤ አንድ ሰው ፈላስፋ፣ ጥበበኛና ደቂቀ መለኮት የሚባለው ሁለቱንም ዓለማት ጠንቅቆ የመረመረ ሲሆን ነው ይላል፡፡
በዚህ ጽሑፍ የምናየው ጥበበኛው/ፈላስፋው ለምን እና እንዴት መሪ መሆን እንዳለበት አፍላጦን የሰውን ነፍስ መዋቅርና የአንድን ሃገር ሰዎች መዋቅር በንጽጽር ያስረዳበትን ነው፡፡ የነፍስን መዋቅር ሲመረምር ሦስት ዓይነት ነፍሳት አሉ ይለናል፡፡ አንደኛው ነፍስ ከወርቅ የተሰራ ነው፤ ሁለተኛው ነፍስ ከብር የተሰራ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ከብረት የተሰራ ነው፡፡
በኛ ማህበረሰብ ዘንድ ነፍስ ፍጹማዊ የሆነ አንድ ንጹህ ባህሪ ያላት ተደርጋ ስለምትቆጠር፤ የአፍላጦንን “ነፍስ” በእኛ ሃገር የ “ልቦና” እሳቤ እንተካው (ለነገሩ አፍላጦን ስለ ኢትዮጵያ አለማወቁ ነው እንጅ ነፍስ ተናጋሪ፣ አሳቢ እና ህያዊት ናት፤ አንደኛ ሁለተኛ ሦስተኛ ደረጃ የላትም)። ስለዚህ ሦስቱን ዓይነት የአፍላጦንን ነፍስ፤ ሦስት ዓይነት ልቦና እንበላቸው፡፡ አንዳንድ ልቦች ከወርቅ፣ አንዳንዶች ከብር፣ ሌሎች ደግሞ ከብረት/መዳብ የተሰሩ ናቸው እንበል - ሃሳቡን በቀላሉ እንድንጨብጠው። እነዚህ የተያዩና እርስ በእርስ የሚፎካከሩ ጠባዮች ያሏቸው ልቦናዎች ናቸው፡፡ እስኪ ሦስቱንም አንድ በአንድ እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡
ሀ/ ብረታዊ/መዳባዊ ልብ፡- ብረታዊ ባህሪ የሚያደላበት ልቦና ታታሪነት፣ መብል፣ መጠጥ፣ መዝናናት፣ ማምረት … ቅብጥብጥ ዓይነት እና ቀለል ያለ ስሜትን የሚወድ ዓይነት ልብ ነው። ይህ ልብ ዕለታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፣ ቀለል ያሉ ዘልማዳዊ ስራዎችን የሚያዘወትር፣ የሚታወቁና የተለመዱ ስራዎች ላይ መጠመድ የሚስማማውና ምቾት የሚሰጠው ነው፡፡ እንደ ጉንዳን ታታሪ ልቦና ነው ይህ ልቦና፡፡ ነገር ግን ፍላጎት/ስሜት ብቻ የሚመራው፤ ፍላጎቱን ማሸነፍ የማይችል ነው፤ ቅብጥብጥነት ያጠቃዋል፡፡
ግዮን መዳባዊ ነው፤ ጸባዩን የተረዱት ያርሱበታል፣ አምርተው ቀለባቸውን ይሰፍራሉ፡፡ ከታችና ከምንጩ ሥር ያሉት የሽንኩርት፣ የካሮት መደባቸውን ያጠጣሉ፤ ፍራፍሬ ያመርቱበታል፤ ከብቶቻቸውን ያጠግባሉ፡፡ ታላቁ ነብይ ሙሴ፤ ከግብጽ በተሰደደ ጊዜ የግዮንን ፈለግ መንገድ መሪ አድርጎ ወንዙን ተከትሎ ወደ መነሻው ወደ ምንጩ ነበር የመጣው እናም ውኃ የሚያጠጡ እረኞችን ያገኘው፡፡ በኋላም የነብይነት ጥሪውን እስኪጀምር ድረስ የካህኑ ዮቶር እረኛ ሆኖ የኖረው እዚሁ ነው። ግዮን እንዲህ ነው፤ እረኝነትንም ያስተምራል፡፡
ለ/ ብራዊ ልብ፡- ይህ ልብ ወኔያም ደፋር ነው፤ ጦረኝነት/ጀብዱ ይወዳል፣ ቁጡ ነው። እንደ ብር ጠንካራ ነው፣ በራስ መተማመኑ ከፍተኛ ነው፣ አዳዲስ ነገሮችን ይደፍራል፣ ልዩ መሆንን ይመርጣል፣ አሸናፊነት ባህሪው ነው፣ አይንበረከክም፡፡ ሃገር ጠባቂ መሆን፣ ህዝብን ማስከበር፣ ኃያልነትን፣ ግዛት ማስፋትን ይወዳል። እንደ አንበሳ ብርቱ ነው፡፡ ነገር ግን ኃይለኛነት የሚገዛው፤ ወኔውን መቆጣጠር የማይችል ነው፡፡
ግዮን ብራዊም ነው፤ ጀግንነትና ጀብዱ ባህሪው ነው። በአምስቱ አመት የአርበኝነት ዘመን ለኢትዮጵያ አርበኞች መሸሸጊያ ዋሻ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ጥላ፣ ጎጆ ሆኗቸዋል፤ ሲደክማቸው ብርታት፣ ሲጨንቃቸው ተስፋ ሆኗቸዋል፡፡ ከበላይ ዘለቀ ከተሰቀለው
ይሻላል ሽፈራው ሶማ የቀረው
የሚለው እንጉርጉሮ የአባይን እና አካባቢውን አርበኝነት፣ አልገዛም ባይነት የሚያስታውሰን ነው። ኃይለኝነቱን በጠባይ መያዝ ላወቀበት ግዮን የኃይል ምንጭ ነው፡፡ በአልገዛም ባይነቱና ባሸናፊነቱ የኢትዮጵያን ተራሮች አቋርጦ የሱዳን በረሃ ሳያመነምነው፣ የግብጽ አሸዋ ሳይመጠው ሁሉንም ድል አድርጎ ሜድትራኒያን ባህር ይቀላቀላል። ኃይለኝነት ባህሪው ነው፡፡ በፍቅር ሲጠጡት ነው ጤና የሚሰጥ እንጅ ክፋት ይዘው ቢጠጡት ጤና ይነሳል፤ እንደ ስካር አናት ላይ ወጥቶ ቋንቋ ይደበላልቃል፡፡
ሐ/ ወርቃማ ልብ፡- ይህ ልብ ተመራማሪ ነው፤ ሁለቱንም ዓይነቶች ልቦናዎች/ባህሪያት አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል፡፡ ከሁለቱ ልቦናዎች በተለየ መልኩ ተመራማሪ፣ ጥበበኛ፣ ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊ፣ የሰከነ፣ ጭምት፣ አስተዋይ፣ መንፈሰ ጠንካራ ነው፡፡ ይህ ልብ ሁሉንም ነገር በአመክንዮ ይመረምራል፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሃሳቦችን፤ ከመጥፎ እስከ መልካም ምግባሮችን በአመክንዮ በመመርመር ይበይናል፡፡ ያለ አመክንዮ አይንቀሳቀስም፤ ፍላጎቱን የሚቆጣጠር ወኔውን የሚያምቅ ወርቅ የሆነ ልብ ነው፡፡ ልክ እንደ ንቧ ማር ሰርቶ ብቻዬን ልጨርስ ሳይል፤ መርዛም እሾህ አለኝ ብሎ ሁሉንም የማይናደፍ አመዛዛኝ ነው ይህ ልቦና፡፡
ግዮን እንደ ወርቃማ ልብ ፍርድ አዋቂ ነው። ቋንቋውን ለሚችሉትና ለሚሰሙት ሰዎች ጥበብን ያስተምራል፡፡ አፈር ከሞላበት የኢትዮጵያ ምድር ተሸክሞ የአፈር ድርቅ ላመነመናት ግብጽ ልምላሜ ሆኗታል፡፡ በበረሃ ላለችው ምስር ፈውሱዋ ግዮን ነው። ለበረኧኞች፣ ለመናንያን የጥበብ መልእክተኛቸው ግዮን ነው፡፡ የግብጽ ጠቢባን ግዮንን ለመስኖ ለመጠቀም ባላቸው ታታሪነት የሒሳብ እውቀታቸው እንዳደገ፣ ፓይታጎረስ ቴረም የተባለውም የሒሳብ ቀመር በዚሁ ግድም እንደተገኘ ይነገራል፡፡ ግዮን ቀማሪ ጥበበኛ ነው፤ በጣና ሐይቅም ውስጥ አቋርጦ የሚሄድበት የራሱ የጥበብ መንገድ አለው። በውኃ ላይ የሚሄድ ብቸኛው ወንዝ ግዮን ይመስለኛል፡፡ በውኑ ይች ጥበብ ከምድር ናትን? እንዲህ ያለ ጥበብ ምን ይረቅቅ?
ግዮን ምንጩ ሥር ላሉ የሰከላ እና ጊሼ ሰዎች ዛሬም ድረስ ፈውሳቸው ነው፡፡ ስደተኛው ሙሴ የኦሪትን ሀሁ ለቅሞ የተማረው ከግዮን ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ የፍጥረት ምስጢራት አንድምታ ሲተረተርበት የኖረ፤ ቅኔ እንደ ውኃ ሲፈስበት የኖረ ነው የግዮን መንፈስ፡፡ ግዮን ውኃ አይደለም መንፈስ ነው፤ ግዮን ከተገደበ የሚገደበው ውኃም ብቻ አይደለም፤ ውጪ ውጪውን የሚያየው የኢትዮጵያዊያንን ልቦና ጭምር እንጅ፡፡ ግዮን አንድም ሦስትም ነው፡፡ እርጥብነት፣ ብርሃናዊነት እና ግዙፍ አካልነት የአንዱ የግዮን ሦስት ባህሪያት ናቸው፡፡
በአፍላጦን ፍልስፍና አንድ ልብ ፍትህአዊ ነው የሚባለው ወርቃማ ባህሪው ብሪታዊንና ብራዊውን አሸንፎ መቆጣጠር ሲችል ነው። ወርቃማ ባህሪው ገዥ የሆነለት ልብ ሰላማዊና ስምሙ ነው፤ ውስጣዊ ነውጥ/አለመስማማት የለውም፡፡ ሁለመናው ውብና ጠቢብ ነው። ብሪታዊው ባህሪ ገናና ሆኖ እራሱን ማስከበር የማይችል፣ ዕለታዊ ጉዳዮች የሚያሽከረክሩት ልቦና እንዳይሆን፤ አሊያም ብራዊው ባህሪ ገናና ሆኖ ጉልበተኛና አውዳሚ እንዳይሆን፤ ወርቃማው ባህሪ የሁሉም የበላይ ሆኖ ፍላጎታቸውንና ስሜታቸውን እያመጣጠነ ማስተዳደርና መምራት አለበት፡፡ እንደህ አይነት ልብ ጎባጣው የቀናለት፣ የተገራ፣ የታረቀ/ስምሙ/ውብ እና ፍትህአዊ ነው፡፡
አፍላጦን ፍትህ የሰፈነባት ሃገር እንዴት ነው ልትኖረን የምትችለው እያለ ሲመራመር ልክ ሦስት ዓይነት ልቦናዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ ይለናል፡፡ ሁላችንም እኩል አንድ አይነት ችሎታ የለንም ይለናል፡፡ አንዳንዶቻችን ጥሩ ሠራተኞች ነን /appetitic/ አንዳንዶቻችን ጠንካራ ወታደሮችን /auxiliary/ ሌሎቻችን ደግሞ መልካም ተመራማሪዎች ነን /Spirit/። ስለዚህ ፍትህ የሰፈነባትን ሃገር ለማግኘት ልጆቻችንን ይሄን ተረት እንንገራቸው ይላል አፍላጦን፡፡
አንዳንዶች ከወርቅ፣ አንዳንዶች ከብር፣ ሌሎች ደግሞ ከብረት ልብ መሰራታቸውን ለልጆቻችን ተረት እየነገርን እናሳድጋቸው፡፡ ሁሉም የተለያየ ችሎታ እንዳላቸውና አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው፡፡ ወርቃማ ልቦች ለገዢነት፣ ብርማ ልቦች ለጠባቂነት፣ ብረታማ ልቦች ደግሞ ላገልጋይነት መፈጠራቸውን እንንገራቸው። ይህ ክፍፍል በምንም አይነት ምክንያት ቢሆን ብሔርን፣ ጎጥን፣ መሰረት ማድረግ የለበትም፡፡
ትምህርትም እንደየአቅማቸውና እንደየልቦናቸው ጠባይ እየተመጠነ ይሰጣቸው፡፡ ምርታማነትን፣ ክህሎትን፣ ፍላጎት ማመጣጠንን፣ ገበያ መፍጠርን ወዘተ ለብረታዊ ልቦች እናሰልጥን፡፡ ዜጋንና ጠላትን መለየትን፣ ሃገርን ማስከበርን፣ ትእዛዝ ተቀባይነትን፣ ወኔን መቆጣጠርን ደግሞ ለብራዊ ልቦች እናስተምር። አለማዳላትን፣ ፍትህአዊነትን፣ ግለ ጥቅም አልባነትን፣ ምክንታዊነትን፣ አመራር ሰጭነትን፣ ተመራማሪነትን ደግሞ ለወርቃማ ልቦች ስልጠና መስጠት ይኖርብናል፡፡
ግለሰቡ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረው ስግብግብነቱን በወኔው ማክሸፍክ፤ ኃይለኝነቱን ደግሞ በምክንታዊነት /አመክንዮ/ ማሸነፍና ወርቃማ ልቡ የሁሉም የበላይና ያለ አድሎ ፈራጅ መሆን እንዳለባት ሁሉ አንድ ሃገር ሰላማዊና ፍትህ የሰፈነባት እንድትሆን ጠቢባን፣ እራሳቸውን የገዙ፣ ፈላስፎች ሊያስተዳድሯት ይገባል፡፡ የሰራተኞችና የጠባቂዎች የበላይ መሆን ያለባቸው ጠቢባን ናቸው። ጠቢብ ሰው፤ ልክ እንደ ወርቃማው ልብ ሰራተኞችና ጠባቂዎች የማያውቁትን ሁሉ የሚመራመር ፈላስፋ ስለሆነ፣ ሁለቱንም ያለ አድሎ የሚያስፈልጋቸውን ልክ እንደየ ልቦናቸው ጠባይ ይመግባቸዋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ሃገሪቱ ፍትህ የሰፈነባት ትሆናለች፡፡
ግብረ ጉንዳን እንደ አፍላጦን የብረት ነፍሳት ያሉ ናቸው፡፡ ታታሪዎች፣ ለፍቶ አደሮች፣ ሁሌም የሚጎትቱት የሚሸከሙት ነገር አያጡም ጉንዳኖች፤ እናም ታታሪውን፣ አራሹን፣ አምራቹን፣ ሰራተኛውን ኢትዮጵያዊ ልቦና ቀደም ብለን የብረት ልብ ያልነውን ግብረ ጉንዳን ብንለው የሚወክለው ይመስለኛል፡፡ አንበሳ ደግሞ ደፋር፣ ኃይለኛ፣ ጠንካራ ነው እና የብር ልብ ያልነውን ኢትዮጵያዊ አንበሳ ይወክልልን ይመስለኛል፡፡ ንብ ሁሉንም ቀሳሚ፣ ቀማሚ፣ ወለላ ጠማቂ ነው፤ በመድሃኒትነቱ፣ ጥም አርኪነቱ/ጠጅ/፣ ፈዋሽነቱ የተመሰከረለትን ማርን የሚጠበብበት ንብ ነው፡፡ የወርቅ ልብ ያልነውን ኢትዮጵያዊ ንብ፣ በደንብ ይወክልለናል (አደራ የኢህአዴግ ንብ እንዳትሰማን)፡፡
መደምደሚያ፡- /የኢትዮጵያዊ አንድም ሦስትም ልቦና/ የኢትዮጵያዊ ልቡ እንደ ግብረ ጉንዳን ታታሪ፤ እንደ አንበሳ ደፋሪና እንደ ንብ ተመራማሪ ነው። እርሻን ቀድመው ከጀመሩት የጥንት ስልጡኖች አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ምግብ አብስሎ መመገብ፤ እንስሳትን ማላመድና ማርባት፤ ልብሱን ከእጽዋት/ጥጥ/ አዘጋጅቶ መልበስ ከጀመሩት ሁሉ ቀዳሚ ነው ኢትዮጵያዊ፡፡ እነዚህን ሁሉ የኑሮ ዘዬዎች በአንክሮ ብንመረምራቸው፣ የኢትዮጵያዊን ህያው ታታሪ ልቦናን ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡ በጉልበቱና በክህሎቱ ለዘላለም ምስክርነት የተከላቸው ውቅርና ትክል ድንጋዮች የታታሪነቱ ምስክር ናቸው (አክሱም፤ ላሊበላ፤ ጢያ ወዘተን ያስታውሳሉ)፡፡
ኢትዮጵያዊ ከጥንትም ጀምሮ አሁንም ድረስ ዳር ድንበሩን ማስከበር፤ አልገዛም ባይነት፤ ጀግንነት ባህሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊን በዚህ የሚጠረጥረው ማንም የለም፡- ካለም የእጁን ያገኛል፡፡ ዛሬም ድረስ የአካባቢውን ሰላምና የአለምን ደህንነት ለማስከበር ደፋ ቀና ከማለት አልቦዘነም፤ ኢትዮጵያዊ፡፡ ኃይለኝነትና ጀብዱ እንደ ባህሪ ተዋህደውታል። ጦሩን ሰብቆ ጋሻውን ነጥቆ አፈር ከድሜ ያበላቸው ጠላቶቹ፣ ለኢትዮጵያዊ ደፋር ልቦና ምስክር ናቸው (ግብጾችና ጣልያንን ያስታውሱ)
የፍትህ አዋቂነቱን፣ ተመራማሪነቱን፣ የጽድቅ ፍቅሩን ለማስረገጥ ደግሞ ቤተ አምልኳችን ለዘመናት ሲመሰክሩለት የኖሩት የምርምር፣ የጠቢባን ልቦና የሚያፈልቀውን እውቀት መመርመር ነው፡፡ የባህላዊ ተቋማቱ እንደ ሽምግልና፣ የገዳ ሥርዓት፣ እድር፣ እቁብ፣ የቡና ማህበራቱ፣ የዝክር ማህበራቱ፣ የባህላዊ ትምህርት ቤቶች የኢትዮጵያዊውን ፈላስፋነቱን የሚመሰክሩ ናቸው። መንግስታት በውስጥ ሽኩቻና ጦርነት ወቅት አቅማቸው ተዳክሞ መዋቅራቸው ሲላላ፣ ማህበራዊ አንድነቱን ያለ መንግስት ማስቀጠል የሚችል እንደ ወርቅ የነጠረ፤ እንደ ንብ የተመራመረ ልብ ያለው ህዝብ ነው ኢትዮጵያዊ፡፡
በግዮን መንፈስ የተቃኘን ኢትዮጵያዊን ህዝብ ለመምራት፣ በጊዜያዊነት በመነዳት ሳይሆን እንደ ግዮን ዘመን የማይሽረው ህዝባዊና ሃገራዊ የጉዞ ራዕይ መሰነቅ ግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ ታማኝነት ሳይሆን አገር የመምራት ሙያ ባለቤትነት ያስፈልገናል፡፡ በዘመድ በመሰባሰብ ሳይሆን በጥበብ ማበብ ነው አገር የሚመራው፡፡
ከዘመቻ ባሻገር ማሰብ፤ ዛሬን መስሎ ከመታየት መራቅን፡፡ ፍትህን፣ ጥበብን፣ መልካምነትን ስንቅ ማድረግ ግድ ነው የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን፡፡ ለአለቃ መታመንን ሳይሆን ለህዝብ ማገልገልን ማስቀደም ይጠይቃል፡፡ ለዛሬ አሸናፊ ሆኖ ለመታየት ሳይሆን የህሊና ፍርድን ለማሸነፍ መስራት፡፡ የግል ጥቅም በረሃ (ሱዳን) ሳያመነምነን፤ የቂም በቀልና የበታችነት አሸዋ (ግብፅ) መጥጦ ሳያደርቀን፤ ሃገራዊነትንና ህዝባዊነትን ታጥቀን ከባህሩ (ሜድትራኒያን) እንደ ግዮን በታላቅነት፣ ባሸናፊነት መቀላቀል ያስፈልገናል። እንደ ታላቁ ፈላስፋ አፍላጦን ፍልስፍና ከሆነ፣ ይህንን ኢትዮጵያዊ ለማስተዳደር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልቦና አብጠርጥሮ የሚያውቅ፣ ጠቢብ ልቦና ባለቤት መሆን ያስፈልጋል፡፡ እንደ ንቧ መድሃኒት የሚሆን ማር መቀመም የሚችል መሪ፤ እንደ ንቧ ሰፈፍ ቅርጹ ያልተዛነፈ/የተስተካከለ የማር እንጀራ/ አይነተኛ የሆነ እንቁላል መጣያ የሚሆን ሰፈፍ መጋገር የሚችል ቀማሪ መሪ፤ እንደ ንቧ ከሁሉም አበባ ጣፋጩን ቀስሞ፣ ከውኃ ጋር አስማምቶ ዱቄቱ ሳይበዛ ማሩ እንዳይደርቅ፤ ውኃውም ሳይበዛ ማሩ እንዳይንቦጫረቅ ውብና ስምሙ የሆነ፣ የተስተካከለ፣ ለሁሉም ጣፋጭ ለሁሉም መድሃኒት የሆነ ማር ማዘጋጀት የሚችል ፈላስፋ/ጠቢብ መሪ ያስፈልጋታል፤ ኢትዮጵያ፡፡ የዚህ ወርቅ ህዝብ መሪ ለመሆን፣ የወርቆች ሁሉ ወርቅ መሆንን ይጠይቃል። የዚህ ፈላስፋ ህዝብ መሪ ለመሆን፣ የፈላስፎች ፈላስፋ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ሰንቆ፣ በዚህ ምድር አንገቱን ቀና አድርጎ መኖር ይገባዋል፡፡
(ከሴፕቴምበር 28፣ 2013 እትም
በድጋሚ የወጣ)

Read 1931 times