Sunday, 30 April 2017 00:00

“ጋሼ አሰፋ፤ ደራሲ ሁን!”

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(2 votes)

   “አንድ አፍሪቃዊ መንደር ውስጥ የሚኖር ሽማግሌ ሞተ ማለት፣ አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ተቃጠለ               ማለት ነው” - እዎቦዋ
        ጋሼ አሰፋ ጫቦ አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ነበር። እናም ወደማይቀረው ዓለም መጓዙን ስሰማ፣ አንዱ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ተቃጠለብን ስል ቆዘምኩ፡፡ ሞት ሰሞኑን ተደራርቦብኛል፡፡ ወላጅ እናቴ ወ/ሮ ወርቅነሽ ባላ፣ የፋሲካ እለት ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ፣ ልክ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ መሪር ሀዘን ላይ እያለሁ ለዳግማይ ትንሳኤ፣ ጋሽ አሰፋ ጫቦ ከዚህ ዓለም በሞት የመለየቱን መራር ዜና፣ የቅርብ ጓደኛዬ ሻምበል ፀጋዬ ኃይሉ፣ ሌሊት ደውሎ አረዳኝ። ፀጋዬ መረጃውን ከማህበራዊ ሚዲያ ማግኘቱን ነግሮኛል። ስልኩን እንደዘጋሁ እንደ ገና ስልኬ ጮኸ። የውጪ ጥሪ ነው፣ አነሳሁት፡፡ ቀይ ባህር ላይ 201 ስኳድሮን አብረን የቀዘፍነው፣ በርካታ የባህር ላይ ትዝታ የነበረን የቅርብ ጓደኛዬ፣ ፒቲ ኦፊሰር ተዘራ ብርሃኔ ነበር፡፡ ቁጥሩ እንጂ ስሙ ስልኩ ስክሪን ላይ ስላልተነበበኝ “ጤና ይስጥልኝ፤ ማን ልበል?›› አልኩ።
“ጃት ነኝ!” አለ፡፡ ጃት፤ የተዘራ ብርሃኔ የቅፅል ስም ነው፡፡ የቀይ ባህርን ማዕበል አብረን ስንጋተር ቆይተን፣ እንደ ምንም እግሩ መሬት ከረገጠ፣ ዳግም ወደ ጀልባው ሳይመለስ፣ ለእለታት ብርር ብሎ ስለሚጠፋ ነው ይህንን ቅፅል ስም ያወጣንለት፡፡
ወደ ጉዳያችን ስንመለስ፣ በእናቴ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልፆልኝ፣ የጋሼ አሰፋ ጫቦ ማረፍ ቁርጥ መሆኑን አረዳኝ፡፡ ይሄኔ ጨለመብኝ፤ በአያሌው ቆዘምኩ፤ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩኝ፡፡ በትንሽ በትልቁ የምነፋረቅ ሰው አይደለሁም፡፡ ቀይ ባህር ላይ በ1982 የካቲት ወር በተካሄደው መራራ ጦርነት ተሳትፌ፣ አያሌ ጓደኞቼ እዚያ አውደ ውጊያ ላይ ወድቀዋል፡፡ ለዘር ተርፌ አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ ሰዎች ሲሞቱ አዝን እንደሆን እንጂ አልቅሼ አላውቅም፡፡ የአዲስ አድማሱ ወዳጄ አሰፋ ጎሳዬ ድንገተኛ ሞት ግን የእንባ ከረጢቴን ፈታው፡፡ ከልቤ አለቀስኩኝ፡፡ የዓመታት ዝምታዬን አካካስኩ፤ በጣም አነባሁ፡፡ የጋሼ ስብሐት ለአብ ሞትም፣ ይህንኑ አልቃሻነቴን በአያሌው ቆስቁሶታል፡፡ ከለል ያለ ቦታ ብቻዬን አነባሁ፡፡ በቀብሩ ቀን ደንዝዤ ነበር። የእናቴ ረፍትና የጋሼ አሰፋ ሞት ደግሞ በአያሌው ደቋቆሰኝ። እንደተለመደው ብቻዬን አነባሁ፡፡፡
በቅርቡ ምን አልባትም ከዓመታት ከመንፈቅ በኋላ ስልሴ ጮኾ አነሳሁት፡፡ “ሰሮ!” አለኝ ከማዶ። “ሰሮ” ስል መለስኩ (ሰሮ በጋሞ ቋንቋ ሰላም ማለት ነው፡፡) “አሰፋ ነኝ!” ሲለኝ፤ “አሰፋ ጫቦ!” ብዬ ጮህኩኝ፡፡ እራሱ ነው፡፡ ስልኩን ያገኘው ከጋራ ጓደኛችን ወ/ሮ ሮማን ተወልደ ብርሃን ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ እንደምታገኘው ነግራኝ ነበር፡፡
ሽፋኑን “ቫይበር” ላይ የለጠፍኩት፣ “መልህቅ” የተሰኘ መጽሐፍ ታትሞ እንደሆነ እንድልክለት ጠየቀኝ፡፡ አለመታተሙን ገልጬ፣ ‹‹ልጅነት›› ደርሶት እንደሆን ጠየኩት፡፡ ለንደን በሚገኘው ታናሽ ወንድሙ እሸቱ ጫቦ  እንዲሁም ወደ አሜሪካ መዝለቃቸውን ባወሱኝ ወዳጆቼም በኩል አንድ ሁለቴ ልኬለት ነበር፤ ግን አልደረሰውም፡፡ “ መፅሃፉን አለመላካቸው ወንጀል ነው” ሲል ወቀሳቸው፡፡ እንደገና ልልክለት ወስኜ፣ ‹‹ማስታወሻም›› የቀድሞው የጋሼ ስብሐት ለአብን ህይወት የሚያወሳው እስከ 67 ዓመቱ ድረስ  መሆኑን አጫውቼው፣ አሁን ግን ከልደት እስከ ህልፈት የሰራሁትን ‹‹ማስታወሻ›› አክዬ ላኩለት፡፡
ከዚህ በኋላም አጭር መልዕክት ተለዋውጠናል። የገረመኝ ፈጣን አንባቢነቱ ነበር፡፡ 10 ቀን ለእኔ አንድ መጽሐፍ ለማንበብ፣ ከስራዬ ጋር ከተጣመረ አይበቃኝም፡፡ የእኔ አነባበብ ስልት መስመር በመስመር ስለሆነ፣ ለአንድ መፅሃፍ 15 ቀናት ያስፈልገኛል፡፡ እሱ እዚያ ምራቅ ለመዋጥ እንኳን ጊዜ በሚያጥርበት አገር ተቀምጦ፣ ከስራው በተጨማሪም ከድረ ገፅ ወዳጆቹ ጋር እየተገናኘ፣ በአስር ቀን ሁለት መጽሐፍት እምሽክ ማድረግ ይችላል፡፡
መጻህፍቶቼን ስልክለት ከሰላምታ ጋር የላኩለት መልዕክት ባጭሩ እንዲህ ነው፡-
‹‹ጋሼ አሰፋ፤ አንተ እድለኛ ነህ፤በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከልጅነት እስከ እውቀት ኖረህበታል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ግን መቆም አለበት፡፡ ተተኪው ትውልድ ከቆምክበት እንዲቀጥል ማድረግ ይኖርብሃል፡፡ አንተ ግን በግልፅ ከፖለቲካው ዓለም መለየትህን መግለጫ ሰጥተህ ደራሲ መሆን ይኖርብሃል፡፡ ህይወትህን ሙሉ አንብበሀል፤ ንባብህ ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ ስለዚህ ደራሲ ብትሆን በኢትዮጵያ ታሪክና ሥነ ፅሁፍ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖርሃል፤ ከኋላ ለምንከተልህ ወጣት ፀሐፍትም ድንቅ አምድ ልታኖርልን ትችላለህ፡፡
‹‹ጋሼ፤ ልብ በል፤ አንድ እዚህ አገራችን ውስጥ በፖለቲካው ዘርፍ ተሰማርተው፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው የሰሩ፣ በኋላም የህይወት ታሪካቸው በመፅሃፍ የታተመላቸው አቶ ተመስገን ዘውዴ የተባሉ ፖለቲከኛ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ወደ ፖለቲካ የሚገቡት በስተ እርጅና ነው” ያሉትን አባባል አሁን ላስታውስህ፡፡ አንተ ግን ከልጅነትህ ጀምሮ ባመንክበት ተጫውተሃል፡፡ አሁን ስላንተ ሳስብ ባንተ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ራሴን ጠርቼ ስቆዝም፣ ከዚህ በኋላ ፖለቲካውን እርግፍ አድርገህ ትተህ፣ ደራሲ መሆን አለብህ ብያለሁ፡፡ ደራሲ የሚያደርግህ አያሌ ስንቆች እንዳሉህ አሳምሬ አውቃለሁ”
ለዚህ ነው በእንግልጣ አፍ ስላበረታታኸኝ አመሰግንሀለሁ ያለኝ፡፡
ይህንን ጥብስቅ ያለ እውቀቱን፣ ይህንን ይበል የተሰኘለትን ንባቡን ለጥራዝ ሳያበቃ፣ በረከቱን፣ እምነቱን ሳያጋራን በማለፉ ነው ያለቀስቀኩት፡፡ ሞት ብሽቅ እውነት ነው፡፡ አሰፋ ጫቦም የዚህ እውነት አካል ሆነ እንጂ እንዳልኩት ሆኖ የፖለቲካውን ዓለም በይፋ ተሰናብቶት ቢሆን ኖሮ፣ ህልምና ትልሜ እውነት በሆነ ነበር፡፡ በእኔ ምኞት ቢሆን ኖሮ፣ በቀጥታ ጨንቻ ወርጄ የሚያርፍበትን ውብ የጋሞ ጎጆ ቤት ማሰራት አላማዬ ነበር፡፡ ምርጫው የዘር ማንዘሩ መፍለቂያ በሆነችው ‹ደራ› ከሆነም፣ ደራ ላይ ለእርሱ ጎጆ ቤት መስራት ለእኔ ቀላል ነበር፡፡ ምክንያቱም የአባቴ ትውልድ ስም ‹ኤሌ› ከጋሽ አሰፋ ዘመዶች ጋር ድንበርተኛ ነበሩ፡፡ አምላክ ይህንን ውጥኔን አልፈቀደም እናም ጋሼ አሰፋ ሞተ፡፡
ጋሽ አሰፋ ብቻውን ሺውን ገጥሞ ይታየኝ ነበር። ‹‹አያገባኝም!” ብሎ የሚተወው ጉዳይ የለም፡፡ አያሌ ርዕሰ ጉዳዮችን ይተነትን፣ ይፅፍ ይናገር ነበር። ለዚህ ያበቃው ደግሞ ማወቁ፣ ማንበቡ፣ መጓዙ፣ ከምንም በላይ ያመነበትን ፊት ለፊት መናገሩ ነው፡፡ የፊት ለፊት ተናጋሪነቱ፣ ምስጢር ከጋሞነቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድ የጋሞ ተወላጅ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ‹‹ወርዶ አሳኦፓ!›› እየተባለ ነው የሚያድገው፡፡ (ውሸት አትናገሩ ማለት ነው፡፡) ለአንድ ጋሞ ‹‹ኢ ዚ ወርዮ!›› መባል የሞት ሞቱ ነው፡፡ (እሱ ሐሰተኛ ነው ማለት ነው) ግምገማን ከልጅነት ጀምሮ ከእናቱ ጡት ጋር ይያያዛታል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጋሞ ዝቅ ባለ፣ በማንሾካሾክ ድምፅ የማያወራው፡፡ እንደዚያም ማውራት አይችልም፡፡ ልሞክር ቢል ‹‹ደቅ ኢስታ ሀሳአ!›› ይባላል፡፡ (ጮክ ብለህ ተናገር ማለት ነው፡፡)
ይህንን አንብባችሁ ስትጨርሱ ወደ እንጦጦ ወጣ ብትሉ፤ የጠጅ ቤት ጫጫታ ትሰማላችሁ፡፡ ጠጅ ቤቱ ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላ ይመስላችኋል፡፡ ጎራ ብትሉ ሶስት ጋሞዎች እያወሩ ነው፡፡ ስለ ጋሞ ሲያወሳ፤ ‹‹ጋሞ እውነቱን እንዲናገር የእምነት፣ የባህል ግዴታ አለበት፤ ግዴታውን ካልተወጣ የሚከፍለው ዋጋ አለ፤ ጎሜ ነው፡፡ ጎሜ ደግሞ መቅሰፍት ያመጣል፡፡ (ጎሜ ሀጢያት እንደ ማለት ነው) እንደ እምነቱ፤ ስንሞት ገሀነም ገብተን ሳይሆን ዋጋውን እዚሁ መሬት ላይ ነው የምንከፍለው። ‹‹መቅሰፍቱ in one form or another በራሱ፣ በቤተሰብ፣ በንብረት ---- አልፎ አልፎ በደሬ (አገር) ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡
ጋሽ አሰፋ ይቅር ባይ ልብ አለው፡፡ በእንዳለ ጌታ ከበደና ጓደኞቹ ጥረት ተሰባስቦ ለህትመት የበቃው ‹‹የትዝታ ፈለግ›› የተባለ መፅሐፉ መግቢያ ላይ፤ ‹‹ጠላት የለኝም›› ሲል ታላቅነቱን እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ የእርሱን ሥራና ፅሁፍ ልብ ብለን የተከታተልን፣ ከጠላትም ግዙፍ ጠላት ሊኖረው እንደሚችል  እንገነዘባለን፡፡
ጋሽ አሰፋ በጋሞ ‹‹ቦዛ›› ነው (ቦዛ፣ ግልፅ የሚል ፍቺ አለው) በፃፋቸው ፅሁፎች ሁሉ ቦዛነቱን በአያሌው አይቼበታለሁ፡፡ ነገን በእርግጠኝነት ያምናል፡፡ ስለዚህም ‹‹ይሄንን ጉዳይ አንድ ቀን እመለስበታለሁ›› ይለንና ወደ ፈለገበት፣ ወይም አሁን ወደሚያወጋበት ጉዳይ ያዘግማል፡፡ ይህ ቦዛ ‹‹ኢትዮጵያ ዞሮ መግቢያ ቤታችን›› ሲል ሊፅፈው ያሰበውን ፅሁፍ ጨርሶልን ይሆን ወይስ ነገን አምኖ እንዲሁ ጉድ ሰርቶን ይሆን? በተመሳሳይ “ቆይ ነገ” ሲል፣ ወይ ስሜቱ ሳይመጣለት ቀርቶ አያሌ ሀሳቦቹን ሳይቋጭልን ተላለፍን፡፡
‹‹የትዝታ ፈለግ›› ተከታይ ወይም ሌላ ድርሰት በአገር ውስጥ እንዲታተም ትልም ነበረው፡፡ ይሄንን ከወ/ሮ እመቤት አሰፋ ጫቦ ጋር እየተመካከረ ነበር፡፡ ይህስ የት ደርሶ ይሆን? ልጁ ከተጽናናች ኋላ አናግራታለሁ፡፡ የራሱን ማስታወሻ መጻፉን አጫውቶኝ ነበር፡፡ ይህስ የት ደርሶ ይሆን? እልፍ አዕላፍ ጥያቄዎች አሉን፡፡
የጋሼ አሰፋን ረፍት ሰምታችሁ በመደወል የሃዘኔ ተካፋይ ለሆናችሁ ወንድምና እህቶቼ፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ፣ ለአድናቂዎቹ መጽናናቱን እመኛለሁ፡፡ ‹‹ጋሽ ኔሸንፓ ፆሲ ማሮ!›› የጋሼን ነብስ አምላክ ይማረው እያልኩ ነው፡፡ አሜን!! እንበል፡፡

Read 1899 times