Saturday, 27 May 2017 13:57

ጋምቢያ የቀድሞው መሪዬ ከ50 ሚ. ዶላር በላይ ዘርፈውኛል አለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  88 የባንክ አካውንቶችና የ14 ኩባንያዎች ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ በፍ/ ቤት ታግደዋል

       በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣኔን አልለቅም ብለው ሲያንገራግሩ ከቆዩ በኋላ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና ባለፈው ጥር ወር አገር ጥለው የተሰደዱት የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜህ፤ ከመንግስት ካዘና ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈዋል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ያያ ጃሜህ ባለፉት አስር አመታት ብቻ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ገንዘብ ዘርፈው ከአገር ማስወጣታቸውን የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ በአገር ውስጥ ያሉ የጃሜህ ሃብቶችና ንብረቶች በሙሉ እንዳይንቀሳቀሱ በፍርድ ቤት መታገዳቸውንም ገልጧል፡፡ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ 14 ኩባንያዎች እና በስማቸው ወይም በወዳጆቻቸው ስም የተከፈቱ 88 የባንክ አካውንቶችም እንዳይንቀሳቀሱ በፍርድ ቤት መታገዳቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በርካታ መኪኖችን ጨምሮ በፕሬዚዳንቱ ስም የተመዘገቡ በርካታ ንብረቶችም መታገዳቸውን አብራርቷል፡፡
ጃሜህ ከመንግስት ካዝና የዘረፉት ገንዘብ 11 ሚሊዮን ዶላር ያህል ይሆናል ተብሎ ሲገመት የቆየ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ባደረገው ምርመራ ገንዘቡ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚደርስ ማረጋገጡን እንዳስታወቀ ቢቢሲ በዘገባው አስረድቷል፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር ለ22 አመታት የመሩትና ባለፈው ታህሳስ በተካሄደው ምርጫ በተቀናቃኛቸው አዳማ ባሮው መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣን አልለቅም በማለታቸው የጎረቤት አገራት ባሳደሩባቸው ከፍተኛ ጫና ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ የተሰደዱት ያያ ጃሜህ፣ በርካታ ውድ መኪኖችንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን ይዘው እንደሄዱ ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1581 times