Sunday, 04 June 2017 00:00

‹‹ብሪጂንግ ካልቸርስ›› የሙዚቃ ኮንሰርት ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በታዋቂው የፒያኖ ሊቅ ግርማ ይፍራ ሸዋና ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት በሚመጡ ሙዚቀኞች የሚቀመረውና ‹‹ብሪጂንግ ካልቸርስ›› (ባህሎችን ማገናኘት) የተሰኘው የሙዚቃ ኮንሰርት ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ይቀርባል፡፡
በዚህ ኮንሰርት ላይ ግርማ ይፍራ ሸዋ ብቻውን፣ ከአውሮፓ ከሚመጡት ሙዚቀኞች ጋር በጋራና ከጣሊያን ከምትመጣ የኦፔራ አቀንቃኝን በማጀብ ከ1፡30 እስከ 2፡00 የሚቆይ ሙዚቃ እንደሚያቀርብ ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ በማሪዮት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስፖንሰርነት በብሉ ሚዲያ አስተባባሪነት የሚዘጋጀው ይሄው ኮንሰርት፤ በጉጉትና በናፍቆት የሚጠበቀውን ተወዳጁን የረቂቅ ሙዚቃ አቀናባሪ ግርማ ይፍራሸዋን ከአድናቂዎቹ ጋር በቀጥታ ያገናኘዋል ተብሏል፡፡
በዕለቱ በኮንሰርቱ ላይ የሚታደሙ በተቻለ መጠን ለኮንሰርቱ በሚመጥን አለባበስ እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ የኮንሰርቱ መግቢያ መደበኛው 1 ሺህ ብር ሲሆን ቪአይፒ 1300 ብር ሲሆን ለቪአይፒ የእራት ግብዣን ይጨምራል ተብሏል፡፡
በእለቱ ለሚታደሙ ሁሉ የግርማ ይፍራሸዋ 3ቱም የረቂቅ ሙዚቃ አልበሞች በነፃ እንደሚበረከቱ የተገለፀ ሲሆን ማክሰኞ ሰኔ 13 ደግሞ መግቢያው ነፃ የሆነ ለሙዚቃ ተማሪዎች የተዘጋጀ የግርማ ኮንሰርት እንደሚካሄድ በእለቱ ተገልጿል፡፡ የመግቢያ ትኬቶቹ በራማዳ፣ በሒልተን፣ በካፒታልና በጎልደን ቱሊፕ ሆቴሎች ይሸጣሉ፡፡

Read 1020 times