Monday, 19 June 2017 09:22

“ቃና” ባይኖር ምን እሆን ነበር?

Written by  በተአምር ተክለብርሃን
Rate this item
(3 votes)

 ብዙ የአማርኛ ፊልሞች ላይ ስመለከት፣ ሰፊው የፍቅረኛሞች የህብረተሰብ ክፍል፣ ለተፈቃሪዎቻቸው ፍቅራቸውን አጋነው ለመግለፅ ሲፈልጉ እንደተኮራረጁ ሁላ… “እድሜዬን መቁጠር የጀመርኩት አንተን/ቺን ካገኘው ጊዜ ጀምሮ ነው” ከዛ በፊት አልኖርኩም እንደማለት… (“ፍቅረኛን የማማለያ 20ዎቹ ዘዴዎች” ምናምን የሚለውን የሳይኮሎጂ መፅሐፍ፣ ከፊልሙ በፊት ሸምድደውታል መሰለኝ)
ብቻ “እድሜዬን መቁጠር የጀመርኩት ቃናን ማየት ከጀመርኩ ነው” ብዬ ለቃና ቲቪ እስክናገር (የሳይኮሎጂ መጽሐፍ የማንበቢያ ጊዜ በቃና ምክንያት የለኝም) ይገርማችኋል --- ከአንዳንድ ሱሶች ተላቀቅሁ ስል፣ በቃና የቱርክ ፊልም ሱስ ተጠምጄ አረፍኩት፡፡
አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ደስታ ሊሰጠኝ የቻለው ቃና ይመስለኛል፡፡ በአኗኗር ዘይቤዬ ላይ እራሱ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ከስራ ወደ ቤት እንደገባሁ፣ ከ12 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ቃና አያለሁ፤ ከዛ እተኛለሁ (ስለሚደክመኝ እንጂ ከዛም በላይ ብቀጥል ደስታዬ ነው)
ሌሊት በህልሜ  የየፊልሙን ቀጣይ ክፍል በሌላ ደራሲ አማካኝነት አያለሁ፡፡ ሲነጋ ሰዓቴን ጠብቄ ስራ እገባና፣ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር “እገሊት ምን ሆና ነው? እገሌ ምን ሆኖ ነው?” እያልኩ አራቱንም ፊልም እገርባለሁ፡፡ የዕለት ተዕለት ኑሮዬ --- እንዲህ ባዲስ መልክ ተጀምሯል፡፡
ምን እሱ ብቻ --- ስደነግጥ የአውራ ጣቴን ጫፍ በጥርሴ ነከስ አድርጌ፣ እራሴን ወደ ላይ ገፋ ማድረግ ጀምሬያለሁ፡፡ የቱርክ ባህል ተፅእኖ አድርጎብኝ። ጥሩ ያልሆነ ወሬ ስሰማ፣ የጆሮዬን ጫፍ ጎተት አድርጌ፣ መልሼ እጄን ለኩርኩም በሚሆን መልክ እጨብጠውና፣ አጠገቤ ያለውን ነገር አንኳኳለሁ (“የሴጣን ጆሮ ይደፈን” ከሚለው ሀገርኛ  አባባል ወጥቼ፣ በቱርክኛ ሳንኳኳ ነው የምውለው)
በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሴጣን ጆሮ እንዲደፈን በቱርክኛ ለማንኳኳት የሚጋብዙ ነገሮች በመብዛታቸው ስራ መሄጃ ሰአትም አይኖረኝም ነበር፤ ግን እድሜ ለቃና ከዚህ ሀሳብም  ገላግሎኛል። እንዴት አትሉም …… ስለ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች የማሰቢያም የመስሚያም ጊዜ የለኝም እንጂ እንቅልፍ አጥቼ ሳንኳኳ ልኖር ነበር፡፡ ምን ሳንኳኳ ብቻ--- የሚስደነግጡ ነገሮች በተከሰቱ ቁጥር ውሃ ልትውጥ ወደ ላይ እንዳንጋጠጠች ዶሮ፤ አውራ ጣቴን ጥርሴ መሀል ከትቼ፣ እራሴን ወደ ኋላ ስገፋ መዋሌ ነበር፡፡
ብቻ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ  ጉዳዮች ላይ እድሜ ለቃና የለሁበትም፡፡ እኔም መንግስትም ከብዙ ሀሳብ የተገላገልን ይመስለኛል። እናንተዬ --- ያለሁት ቱርክ እስኪመስለኝ ድረስ ከኢትዮጵያ መረጃ  እርቄያለሁ፡፡ የሀገራችን እድገት ባለ ሁለት ዲጂት እንደነበር አውቃለሁ፤ እስቲ ወቅታዊ መረጃ ጀባ በሉኝ፡፡ ስለ ሀገሬ እቺን ታህል ካወኩም ጥሩ ነው፡፡ “ስለ ሀገር  እድገት ለመስማትማ  አንዳንዴ ኢቢሲን ተመልከቺ” እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ (ግን ጊዜ የለኝም፤ በቃና ተጠምጃለሁ!)
ኢቢሲ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ… ከነዳጅ መወደድ ጋር ተያይዞ ባለፈው የተደረገው የታክሲ ታሪፍ ማስተካከያ? ወደዚች ወሬዬ ከመግባቴ በፊት ግን… ትክክለኛውን የታክሲ ጭማሪ ታውቁታላችሁ? እኔ ግራ ግብት ነው የሚለኝ፤ ከ3 ብር እና ከ4 ብር ላይ ረዳቶች የሚመልሱልኝ ያወዛግበኛል፡፡ የሚሰጠኝ መልስ ከ15 ሳንቲም እስከ 30 ሳንቲም ይዋዥቃል፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ መልስ አይኖርም፡፡
ለማንኛውም ወደ ተነሳሁበት ወሬ ልመለስና----በጭማሪው ምክንያት ታክሲ ውስጥ ትንሽ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ረዳት፤  አንዷን ተሳፋሪ  ሂሳብ እንደሚያስጨምራት ይነግራታል፡፡ ተሳፋሪዋም፤ “መንግስት የሌለበት ሀገር ይመስል” እደግመዋለሁ “መንግስት የሌለበት ሀገር ይመስል፤ እንደፈለጋችሁ ታስከፍላላችሁ” አለች (እችን ሀረግ ስታነቡ ወገኖቼ፤ ወገባችሁን ብትይዙ ደስ ይለናል)። ማን? ተሳፋሪዋ። ብቻ “አልጨምርም” በሚል ብዙ ተናገረች፡፡ ረዳቱ ታሪፍ መሆኑን ለማስረዳት የተቻለውን ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ያየ ተሳፋሪ፤ ለሀገሬ አንድ ጠጠር ጣል ላድርግ ብሎ፣ ታሪፍ መሆኑን ሰፊው ህዝብም መንግስትም እንደሚያውቅ ሲነግራት፤ ረዳቱ የሷን ምላሽ ሳይጠብቅ፤ “እባክህ ተዋት” ብሎ ወደ እሷ ዞር አለና፤ “ቃና ላይ ተተክለሽ ከምትውይ፣ ለምን ኢቢሲን ለዜና እንኳን አታይም?! “ የሷን መልስ አልሰማሁም፤ ግን “ኢቢሲ ለዜና?” የምትል ይመስለኛል፡፡
ወደ እኔና የቃና ግንኙነት ከመመለሴ በፊት፣ አሉ አሉን ልጨምርላችሁ፡፡ አንድ ለቅሶ ቤት ተከሰተ የተባልኩት ነው… ለቅሶ ቤት ውስጥ ቤተሰብ የቀብር ሰዓት ከመድረሱ በፊት በለቅሶና በጩኸት አካባቢውን ቅውጥ እያደረገው፣ ጎረቤትና እድርተኛ ግን ወፍ የለም፡፡
ለቀብር ጥሩንባ ቢነፋም ዝር የሚል ሰው ጠፋ፤ እንደሰማሁት ከሆነ “ጥሩንባ ነፊው የተሰጠህን ሀላፊነት በአግባቡ አልተወጣህም” እንዳይባል፣ ደጋግሞ ከህጉ ውጪ ሁላ ነፍቷል አሉ፡፡ ብቻ ማስተዛዘኑ፣ ጉርብትናው ይቅር የእድር ቅጣት ሁላ መፍራት ቀረ? ሰው ሊመጣ አልቻለም አሉ፤ ሀዘንተኛዋ ከመጨነቃቸው የተነሳ ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው? መብራት ሀይል ደውለው …
“እባካችሁ ለቀብር የሚመጣ እድርተኛ አጣሁ… ሁሉም ቃና ላይ ተተክሏል“
“እና ምን እንርዳዎት እመቤት?”
“የቀብር ሰዓቱ 6፡30 ነው፤ የቀብር ሰዓቱ እስኪያልፍ የሰፈሩን መብራት ታጠፋልን? “
የለቅሶውን በዚህ እንለፍና ወደ ሸማቾች ማህበር እናምራ፡፡ መንደርተኛው የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ከሸማቾች ማህበር መገብየት ከጀመረ ቆይቷል። ታዲያ ሰፈርተኛው የለመደውን ሊገዛ ሲሄድ  ሸማቾች ሆዬ፤ “ለሱቅ ሰጥተናል፤ ከዛ ግዙ” የሚል መልስ መስጠት፤ እዛው ክርክር ይነሳና፣ የሰፈሩ እናቶች ወሬውን ሰምተው፣ አንድ አንድ እያሉ ማከፋፈያው በር ላይ ይሰበሰባሉ፡፡ ሌላ ምላሽ ሊሰጧቸው አልቻሉም፡፡ ማህበሩ “ከሱቅ ግዙ” በሚል አቋሙ ፀና፡፡
ከተሰበሰቡት እናቶች መሀል አንዷ፤ “ምነው...ይሄንንማ ለቀበሌ እከሳለሁ” ብላ ወደ ቀበሌ ስታመራ… መንደርተኛው፤ “ፋቱማ ጉል ብቻሽን አይደለሽም፣ ፋቱማ ጉል ብቻሽን አይደለሽም፣ ፋቱማ ጉል ብቻሽን አይደለሽም…” እያለ እስከ ቀበሌ ተከተላት አሉ፡፡ መንግስት እንዴት ዝም እንዳላቸው አላውቅም፤ ያልተፈቀደ ሰልፍ እኮ ነው እሚመስለው። ለነገሩ የዳቦ ወይ የታክሲ ሰልፍ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይሆናል፡፡
የፍርድ ቤት ጉዳይ ያለባት የእናቴ ጓደኛ ቢጨንቃት፣ “እሳት የላሰ ጠበቃ” ካወቀች  እንድትጠቁማት እናቴን ታማክራታለች፡፡ እናቴ ሆዬ፤ አሰብ ታደርግና ፊቷ “በአገኘሁት” መንፈስ እየበራ “አለ እንጂ”
“ጎሽ ገላገልሽኝ፤ ማነው?“ ጉጉት ብላ
“ሙኒር”
“ሙኒር ማነው? “
“እነ ፋቱማ ጉልን ቁም ስቅል የሚያሳያቸው፣ ያሳሪኖች ጠበቃ ነዋ… ከሱ የተሻለ አታገኝም” ብላት እርፍ፡፡
ብቻ --- ያለነው ቱርክ ነው፡፡ ቱርክን ጠልቻት እንዳይመስላችሁ፤ ወድጃታለሁ፡፡ ከቱርክ ያልተመቸኝ ግሊንቺክ ሰፈር ብቻ ነው፡፡ ከድህነት ጠለል በታች ያለች ሀገሬን ነው የሚያስታውሰኝ። ውይ ግሊንቺክ! ከድህነት ጠለል በታች ያሉ ሰዎች የሚኖሩባት ሰፈር፡፡ እኛ ግን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ስንሰለፍ፤ የድህነት ጠለል ላይ ነው እምንደርሰው ወይስ ከድህነት ጠለል በላይ እንገባለን? እንደነ መህመት ኤሚር፤ ሀብታም እንሆናለን ብዬ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡
ስለ ቃና አውርቼ ሙቃዲስን ባላነሳ ማን ይቅር ይለኛል? ማንም! እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ኢትዮጵያውያን እንጀራ ስለምንበላ ነው ምቀኛ ሆነን የቀረነው ሲባል እሰማለሁ፡፡ ስለ ምቀኝነታችን ምንም ጥርጥር የለኝም፤ እንጀራው ሊሆን እንደሚችልም የሰፊውን ህዝብ መላምት አምኜ ተቀብዬ ነበር፤ ታዲያ ሙቃዲስ ምን ሆና ነው? እንጀራችንን ከየት አገኘችው? ብቻ ከኛ አገር ለየት የሚያደርጋቸው፣ መተት አለማወቃቸው እንጂ ይሄን ቱርካዊ ያስለፈልፉት ነበር፡፡ (ስለ መተታቸው ደብቀውን ይሁን አይሁን ሳላጣራ ስለደመደምኩ ቂም እንዳትይዙብኝ)
አስቡት ፋቱማጉል “ሙቃዲስ ናት በምግብ ሰጥታኝ፣ የምቀባው ቅባት ውስጥ ነው የደረገችብኝ” እያለች “ቅጣት” ላይ ስትለፈልፍ… ምን መለፍልፍ ብቻ--- ሰዉ እሚለውን አስቡትማ “ራህሚን እኮ እንዲህ ጅል አድርጋ ያስቀመጠችው ሙቃዲስ ናት--- ምናምኗን ተብትባበት-- ሃሃ” ተብሎ ቡና መጠጫ ነበር ምትሆነው፡፡
“ኤፍሱንና ኑራን ናቸው ከልጅነቴ ጀምሮ በሚጠጣውም በሚበላውም ቀላቅለው ሲሰጡኝ እንዲህ ዘገምተኛ ሆኜ የቀረሁት” እያለች ባህር “የተቀማ ህይወት” ላይ ስትለፈልፍ፣ ቱርክ ብቻ አይደለም ቃና ቲቪ እራሱ በመተት የተሞላ ትእይንት ያስተናግድ ነበር፡፡ 
ብቻ ባህላቸውን ከማሳደግ አንፃር ለቱርኮች መስጠት የምፈልገው አስተያየት፤ ይሄ ውሃ የሚያባክኑት ነገር ላይ ነው፡፡ መልካም ተመኘን ብለው የሀገሪቱን ውሃ ደፍተው ጨረሱት እኮ! ይሄን ከኛ ቢማሩ ጥሩ ነው፡፡ እንደኛ “ይቅናህ” ብለው ማለፍ በቂ ይመስለኛል፡፡  ያላቸውን የውሃ አቅም አላውቀውም፡፡  
ግን ግፍ ነው፤ በር ላይ የሚደፉት ውሃም ጡር አለው፡፡ ነገሩ ውሃ ሬሳ ማጠቢያ ነው ብለው ሊሆን ይችላል፡፡  ቢሆንም ቢሆንም ጡር ነው፡፡ እኛ እንኳን --- የሚፈስ ውሃ በምንገድብበት ሰዓት እነሱ በባልዲ እያወጡ መድፋታቸው ምን ይባላል? ከኛ ጋር የልምድ ልውውጥ ቢያደርጉ ይመከራል፡፡ አባይን መገደብ ሳንጀምር በፊት ሳናውቀው በቱርክኛ፣ ለግብፅ መልካም ምኞታችንን እየገለፅንላት ነበር ማለት ነው?
እንደ ኤፍሱን ያለማቋረጥ አወራሁ አይደል፡፡ ልጅ ሆኜ እናቴ ሙዚቃ ስሰማ፣ ”ነገ ፈተና ላይ እሱ ነው አይደል የሚመጣው? በደንብ ትመልሻለሽ” ትልኝ ነበር፡፡ የዘንድሮው ተማሪ6ዎች እንዴት ሆነው ይሆን? ብዙ ግዜ ተማሪዎች መንገድ ላይ ሲያጋጥሙኝ፤ የኤፍሱን ትምህርት መጀመር ገርሟቸው ሲያወሩ እንጂ ስለ ትምህርት ሲያወሩ ሰምቼ አላውቅም፤ እና አሳስቦኛል፡፡ የማትሪክ ሰሞንም አይደል፤ መቼም የማትሪክ ውጤት የዳሰሳ ጥናት ባላደርግም፤ ኑራንን እንኳ እየረዳ ያለ አምላክ፣ እነሱንም እንዲረዳቸው እመኛለሁ፡፡
አረ ኤፍሱን በቃሽ? ነገሩ እኔም ላበቃ ነው …  «የሕይወቴ ቃና ለውጥ የጀመረው ቃናን ማየት ከጀመርኩ ነው” በፊት ስለ ኑሮዬ አስብ ነበር፤ አሁን ግን የሚያሳስበኝ የእነ ኤፍሱን አዳርና የቱርክ ነገር ሆኗል፡፡

Read 3908 times