Sunday, 25 June 2017 00:00

መንግስት ከሣኡዲ ለሚመለሡ ዜጎች ዋስትና እንዲሰጥ መኢአድ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

    መንግስት ከሣኡዲ አረቢያ ለሚመለሡ ዜጎች ህጋዊ ዋስትና እንዲሰጥና ከሣኡዲ መንግስት ጋር በመደራደርም የጊዜ ገደቡን ለማርዘም ጥረት እንዲያደርግ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጠይቋል፡፡
‹‹ከስደት ለሚመለሱም ሆነ ለስራ እጥ ወገኖቻችን መንግስታት አስተማማኝ የስራ ዋስትና ሊሰጥ ይገባል›› በሚል መኢአድ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ መኢአድ፤ በርካታ ዜጎች በተሠጠው የጊዜ ገደብ ተጠቃለው አለመውጣታቸው ከሶስት ዓመት በፊት ያጋጠመው አይነት የአደጋ ስጋት አስከትሏል ብሏል፡፡
ለዚህም ሲባል መንግስት በአፋጣኝ ከሣኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር የአዋጁ የጊዜ ገደብ በሚራዘምበት ሁኔታ ላይ እንዲደራደር ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ከተመላሾቹ መካከል አብዛኞቹ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሠበብ የተሠደዱ ናቸው ያለው መኢአድ፤ በሚመለሡበት ወቅት ምንም አይነት የበቀል እርምጃ እንዳይወሰድባቸው አስተማማኝ መንግስታዊ ዋስትና እንዲሰጣቸው አሳስቧል፡፡ የመኖሪያና የስራ ዋስትናም ከወዲሁ እንዲያገኙ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሣኡዲ ጋር በአግባቡ ተደራድሮ፣ ዜጎች ከ3 ዓመት በፊት ያጋጠመው ችግር ሳያጋጥማቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ፓርቲው ጠይቋል፡፡

Read 3231 times