Sunday, 02 July 2017 00:00

አምስት አርቲስቶች በወንጀልና በሽብርተኝነት ተከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

    ሁከትና አመፅን የሚያነሳሱ ዜናዎች፣ ግጭቶችና ሙዚቃ በማዘጋጀት፣ ከኦነግ ባንዲራና ወታደሮች ጋር በማቀናበርና ወደ ውጪ በመላክ በዩቲዮብ ላይ እንዲጫን አድርገዋል የተባሉ 5 የኦሮሞ አርቲስቶችን ጨምሮ 7 ግለሰቦች ትናንት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ የሽብርና የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በክስ መዝገቡ ስር የተካተቱት 7 ተከሳሾ አርቲስት መሆናቸው የተመለከተ ሲሆን አሊያድ በቀለ፣ ኢፋ ገመቹ፣ ሃይሉ ነጨ፣ ሴና ሰለሞን፣ ኤልያስ ክፍሉና በግል ስራ እንተዳደራለን ያሉት ሞይቡሊ ሞስጋኑና ቀነኒ ታምሩ ናቸው፡፡
በግለሰቦቹ ላይ ሁለት ክሶች የቀረቡ ሲሆን በአጠቃላይ የክሶቹ ጭብጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የወጣቶች “ሰገሌ ቄሮ” ድምፅ ዜና አዘጋጆችና ዜና አንባቢዎች በሚል ቡድን ራሳቸውን በማደራጀት፣ ዜና በማዘጋጀት ውጪ ላሉት የኦነግ አባሎችና አመራሮች በመላክ፣ በነሱ አማካኝነት ለተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች እንዲሰራጩ በማድረግ ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ስራ ላይ የቆዩ ሲሆኑ በፈፀሙት የሽብር ድርጅት ውስጥ በመሳተፍና የሽብር ተግባር በማሴር፣ በማዘጋጀትና በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸው ተመልክቷል፡፡
ተከሳሾቹ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ ሁከትና አመፅ የሚያነሳሱ ዜናዎችን በኦሮሚኛና በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅተው በድምፅ በመቅረፅ ማሰራጨታቸውም በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
ትናንት አርብ ሰኔ 23 በፍ/ቤቱ ክሳቸው በንባብ የተገለፀላቸው ተከሳሾቹ፣ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲቀርቡ ለሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

Read 8358 times