Sunday, 02 July 2017 00:00

ምስጋና ከአሰፋ ጫቦ ቤተሰቦች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  እስካሁን ለምን ዝም እንዳልኩኝ የምትረዱ ይመስለኛል፡፡ ድንጋጤና ሐዘን በጣም ጎድተውኛል፤ በትክክል ሁሉ ማሰብ አልቻልኩም ነበር፡፡ አሴ ቢሆን ስንት ፅፎ ነበር፡፡
በመጀመሪያ ለአባቴ የደረሰችለት ዳላስ ቴክሳስ የምትኖረው ወ/ሮ አብነት ከነቤተሰቧ፤ ተመላልሳ በመጠየቅ ከአጠገቡ የተገኘች መልካም ሴት ናት፡፡ መቼም ቢሆን አልረሳሽም፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ መላው ቤተሰብ እንዲያውቅ አብነትንም ወደ አሴ እንድትሄድ ያደረጉ የአክስታችን የእትዬ ሽታ ልጆች ትዕግስትና ኤልሳ ምክሩ በጣም ኮርቼባችኋለሁ፣ የእትዬ ሽታ ምትክ ናችሁ።
አሴ አገሩ እንዲገባ ትልቁን ሚና የተጫወቱት በዳላስ ቴክሳስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቴ፤ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ገንዘብ አሰባስበው የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ፣ ከሆስፒታል ጀምሮ እስከ አሸኛኘቱ ድረስ ለፍተው ብዙ ጥረት በማድረጋቸው እንዲሁም በአሜሪካ በተለያዩ ስቴቶች እንዲሁም በተለያዩ ውጭ አገራት ያላችሁ የአሴ ወዳጆች፣ ጓደኞች ሁሉ ያደረጋችሁትን መረባረብ ታሪክ አይረሳውም፡፡
በዳላስ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል አስተዳዳሪና የቅዱስ ተቋም ዳይሬክተር፣ ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊ፣ እግዚአብሔር ብድራቱን ይክፈላችሁ እላለሁ፡፡
በድጋሚ በዳላስ ቴክሳስ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲና በሌላውም ስቴት ያላችሁ፣ በመላው አለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እሱ እንደወጣ እንዳይቀር ስላደረጋችሁ ደግሜ ደግሜ አመሰግናለሁኝ፡፡
ኢትዮጵያ ሲገባ ደግሞ ከመግባቱ ዜና ጀምሮ እስከ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ድረስ ህዝብ እንዲያውቀው በማድረግ ትልቁን ሚና የተጫወተው ሸገር 102.1 ሬዲዮ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እኛ ለአንድም ሰው ደውለን አልተናገርንም፤ ሁሉንም ያሰባሰባችሁት እናንተ ናችሁ። አባቴን እንዳከበራችሁት እግዚአብሔር ያክብርልኝ። በተለይ አቶ ደምሰውንና ሌሎችንም የሸገር አዘጋጆች በሙሉ፣ ወ/ሮ መዓዛንም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ሲገባ ከቦሌ ጀምሮ አቀባበል በማድረግና በሁለተኛው ቀንም የቀብር ስነ ስርአቱን በደማቅ ሁኔታ ያስከበሩትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡›
በሌላ በኩል በአርባ ምንጭና በጨንቻ የቀብር ሥነ ሥርአቱ ይፈፀማል ብለው በጣም ሰፊ ዝግጅትና ድካም ሲያደርጉ የቆዩትን የአርባ ምንጭ ህዝብና የክልሉን መንግስት ይቅርታ እጠይቃለሁኝ፡፡ ያም ሳያንሳችሁ እዚህ ድረስ በመምጣት የቀብር ሥነ ሥርአቱ በባህሉ መሰረት፣ እዚህ ካለው ህዝብ ጋር በደማቅ ሁኔታ ስለአከበራችሁ አመሰግናለሁ፡፡
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የምትልኩልን የሐዘን መግለጫ ደርሶናል፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለምሁራን፣ ለባለሥልጣናት፣ ለአምባሳደሮች፣ ለሚኒስትሮች፣ ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ ለአሴ የቅርብ ጓደኞችና ወዳጆች ከአጠገባችን ላልተለያችሁን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡
የአባቴ የቅርብ ጓደኛና (ወንድም) አቶ ፍቅረ ማርያም ይፍሩ፤ አባቴ አገሩ ሲገባ ከአቀባበል ጀምሮ የህይወት ታሪኩን ባመረ ሁኔታ ፅፎ ያቀረበው የቤተክርስቲያኑ ፕሮግራም እንዲያ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደ ሰርግ አምሮ ደምቆ እንዲደረግ የለፋ በመሆኑ እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጠው እላለሁ፡፡
የአክስቴ ባለቤት አቶ ባልቻ ሙሊሣ፤ የአክስት ባለቤት ሊባል አይቻልም፤ አይገባውም፡፡ ለኛ አባታችን መሰብሰቢያችን ነው፡፡ አሁንም የአሴን ማረፍ ከሰማ ቀን ጀምሮ ቤተሰቡን ከየአለበት እንዲሰባሰብ በማድረግ፣ ደከመኝ ሳይል ያንን ሁሉ ቀን ቤተሰባችንን በመሰብሰብ የቀብሩ ሥነ ስርዓት በጥሩ ሁኔታ ተፈፅሞ፣ እንግዶች በስርአት እንዲሸኙ በማድረግ ትልቅ ነገር ነው ያደረገው፡፡ እግዚአብሔር እድሜና፣ ጤና ይሰጥልን፡፡
ለቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ ለካቴድራሉ ቀሳውስት፣ ካህናት ለአገልጋዮች በአጠቃላይ፣ ለቀሲስ ፀጋዬ በክብር ስለሸኛችሁት በልዑል እግዚያብሄር ስም አመሰግናለሁ፡፡
እንደ ሃሳቡና ፍላጎቱ እንደ ዶርዜ ወንድሞቼ፣ እንደ ጋሞ ዘመዶቹ በዋፈራና በሆታ ሸኙኝ ባለው መሠረት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ በድምቀት ከጥዋት ጀምራችሁ እስከ ቀብር ሥነሥርአቱ ድረስ ላሳመራችሁለት የልቡን ስለፈፀማችሁ፣ ለአቶ ሞላ ዘገየ እንደ ቤተሰብ መሀላችን ገብተህ የኢትዮጵያዊነትህን፣ የወንድምነትህን፣ የጓደኝነትህን ከሌሎች ከውጭም ከአገር ውስጥም ካሉ ጋር በመተባበር እስከመጨረሻው ከአጠገባችን ባለመለየት የሰማነውን የህይወት ታሪክ ባማረ ሁኔታ አሰማሀን፡፡
ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጆች (የአሴ ወዳጆች)፣ ለነብይ መኮንንና ለአለማየሁ አንበሴ እንዲሁም ለሌሎቹ ጋዜጠኞች በሙሉ ከመጀመሪያ ካረፈበት ግዜ አንስታችሁ ሰፊ ሽፋን ነው የሰጣችሁት፤ አስቀድሜ እንዲያውም በጣም ፈርቼ ማዘኔን ነግሬአችሁ ነበር፡፡ ብቻችንን ነን ብዬም ነበር፤ ኋላ ሁሉም ደረሰልን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ለነባዳን የሚዲያ ማማከር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ለዳኒና ለነብይ) ለደራሲ እንዳለ ጌታና ለወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን፣ ለዘነበ ወላ … በአሜሪካን አገር ለሚኖሩ አባቴን እንደ አባት የሚጠብቁና የሚቆረቆሩለት ዳንኤል ካሣሁንና ዶክተር ግርማ አውግቸው ደመቀ እንዲሁም ለካሣሁን ሰቦቃ … ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
ለቤት አከራዮቼ (እንደ አባትና እናት) ለሚሆኑልኝ፣ በሐዘኔ በአጠገቤ ላልተለዩት ለአቶ ሲሳይ ወልተጂና ለወ/ሮ መለሰች ሁሪሳ ከነልጆቻቸው እንዲሁም ለጎረቤቶችና ለጓደኞቼ ለመላው ቤተሰብ ለሻምበል ሃ/ገብርኤል ጫቦና ቤተሰቡ፣ ለወ/ሮ ግንብነሽ ጫቦ ከነልጆቿ፣ ለወ/ሮ ቃልኪዳን መሸሻ፣  ለወ/ሮ ተቀባሽ አንጣልና ብርሃን አንጣል ከነልጆቻቸው፣ ለአቶ ሳምሶን አሰፋ ከነቤተሰቡ፣ ለአቶ አለማየሁ አሰፋ፣ ለአቶ ዋሴ አዛዥ ከነቤቴሰቡ ለአቶ የማነ ከነቤተሰቡ፣ ለአቶ ባንጃው ወዜ ከነቤተሰቡ፣ ለአቶ ፈለቀ በፀሎት ከነቤተሰቡ፣
ለውድ ባለቤቴ ለአቶ በላይ ይመርና ለልጆቼ እንዲሁም በስም ላልጠቀስኳቸው ብዙ ወዳጆቻችን … አመሰግናለሁ፡፡
ለድሬድዋ ነዋሪዎችና ለከተማዋ አስተዳደር ለወንድሜ የኤፍሬም አሰፋ ጫቦ ጓደኞችና ጎረቤቶች ሁሉንም… አመሰግናለሁ፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ የሬዲዮና ቴሌቪዥን አዘጋጆችና ጋዜጠኞች በሙሉ …
በኢትዮጵያም ሆነ፣ በውጭ አገር ለምትኖሩ ሁሉ … ላደረጋችሁልን፣ ለአባቴ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሁሉ እግዚአብሔር ይክፈላችሁ፤ አመሰግናለሁኝ፡፡
በመጨረሻ ለፍቶ እንዲያው እንዳይቀር በአገር ውስጥ አንድ የስሙ መጠሪያ እንዲደረግለትና “ቁጥር ሁለት የትዝታ ፈለግ” አባቴ ፅፎ ጨርሶ ነውና ያረፈው፤ ያንንም እቀጥላለሁኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአጠገቤ እንደማይለይ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እመቤት አሰፋ ጫቦና ቤተሰቦቿ

Read 1465 times