Sunday, 09 July 2017 00:00

ነጋዴውን ያስደነገጠና ግራ ያጋባ የቀን ገቢ ግምት

Written by 
Rate this item
(62 votes)

     የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን ሰሞኑን  በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ እየጣለ ያለው አዲሱ የግምት የገቢ ግብር ተመን ከፍተኛ መደናገጥን የፈጠረ ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ ከዚሁ የቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የተጣለባቸውን የቀን ገቢ ግምት ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮባቸው በድንገት ወድቀው ህይወታቸው ያለፈው አቶ አጎናፍር፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በሰፈር ውስጥ በከፈቷት የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፤ ሰሞኑን በተጀመረው የቀን ገቢ ግመታ፣ ሃምሳ ብር የማይሞላ የቀን ገቢ እንኳን በሌላት አነስተኛ ሱቃቸው ላይ የተጣለው የ5ሺ ብር የቀን ገቢ ግምት በፈጠረባቸው ድንጋጤ ራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ፤ በወቅቱ በሥፍራው የነበሩ ሰዎችም አቶ አጎናፍርን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ወደ አዲስ ህይወት ሆስፒታል የወሰዷቸው ቢሆንም ህይወታቸውን ለማትረፍ አልቻሉም፡፡ የሟች ባለቤት ደግሞ ሸንኮራ ዮሐንስ ለንግስ በዓል ሄደው ነበር ተብሏል፡፡  
የከተማዋ ገቢዎች ባለስልጣን በቁርጥ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ላይ ሰሞኑን የጀመረው የቀን ገቢ ግምት ፍትሃዊ ያልሆነና ጥናት ያልተደረገበት መሆኑን የሚገልጹት  ነጋዴዎች፤ የንግዱን ማህበረሰብ ለምሬት የሚዳርግና ተስፋ የሚያስቆርጥ አሰራር ነው ይላሉ፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሴራሚክ ሥራ ላይ የተሰማራ ረሻድ አወል የተባለ ግለሰብ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ በቀን ገቢ ግምቱ በቀን 10 ሺህ ብር ገቢ አለህ መባሉ በእጅጉ አስደንግጦታል። አምባሳደር አካባቢ የጀበና ቡና በመሸጥ ንግድ ላይ የተሰማራችው  ሌላዋ ወጣት ደግሞ የቀን ገቢሽ 3500 ብር ነው መባሏን ትናገራለች፡፡ “ከጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ በአንድ ቅፅበት ወደ መካከለኛ ግብር ከፋይ መዛወሬ አስደንጋጭም አስቂኝም ሆኖብኛል” ያለችው ወጣቷ፤” ለመሆኑ በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ካፒታል የሚባለው ነገር አይታይም? የእኔ ካፒታል እኮ 100 ብር እንኳን የማያወጣ ጀበና እና ስኒ ነው፡፡ ሰዎቹ ግን እንዴት ነው የሚያስቡት? ይህን ያህል የቀን ገቢ ቢኖረኝ ፀሐይ ላይ ምን እሰራለሁ?” ስትል ደጋግማ ትጠይቃለች፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሳሪስ አካባቢ በአነስተኛ የወንዶች ፀጉር ማስተካከል ሥራ ላይ የተሰማራው  ግብር ከፋይ፤የቀን ገቢ ግምቱ ሰሞኑን በደብዳቤ እንደደረሰው ጠቁሞ፤በቀን 5 ሺህ ብር ገቢ አለህ መባሉ ድንጋጤ እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡ ቀደም ሲል በዓመት ከ8ሺህ ብር በላይ ከፍሎ የማያውቅ መሆኑንና በወር 2ሺ ብር የማይደርስ ገቢ እያገኘ የቀን ገቢህ 5 ሺህ ብር ነው መባሉ ፍትሃዊ አለመሆኑን ገልጿል።
በዚሁ ክፍለ ከተማ በፎቶ ኮፒና ፅህፈት ሥራ ላይ የተሰማራ ሌላ ወጣት የቀን ገቢህ ነው ተብሎ 6 ሺ ብር ግምት የመጣበት መሆኑን ገልፆ፤ ይህን ያህል ገቢ እንኳንስ በቀን በወር አግኝቶ ማወቁን እንደሚጠራጠር ተናግሯል። ሁኔታው ሰርቶ ለመለወጥ ያለኝን ተስፋ በእጅጉ ያጨለመብኝ ነው ብሏል፡፡ የቀን ገቢ ግምቱን በሰማበት ወቅት የተሰማውን ሲገልፅም፤”ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፤ ለሁለት ቀናት ያህል ምግብ መብላት እንኳን አልቻልኩም” ብሏል፡፡ ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር አቤቱታ ለማቅረብ ጥረት ማድረጉን የሚገልፀው ወጣቱ፤ ‹‹ከ500 በላይ ቅሬታ አቅራቢዎች ተሰባስበን ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ፅ/ቤት ሄደን ጥያቄ ብናቀርብም፣ የሚያናግረን የመንግስት አካል እንኳን አጥተን ተመልሰናል” ይላል፡፡
በማግስቱም ከ2 ሺ በላይ አቤቱታ አቅራቢዎች ተሰባስበው ወደ ክፍለ ከተማው ፅ/ቤት በማምራት አቤቱታቸውን ለማሰማት ጥረት ቢያደርጉም ምላሽ በማጣታቸው ጩኸታቸውን እያሰሙ በጎዳና ላይ መጓዛቸውንና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መሞከራቸውን የተናገረው ወጣቱ፤ ”ድምፃችን  ይሰማ” ፣ ”መብታችን ይከበር” ለሚለው መፈክራችንና ጩኸታችን የተሰጠን ምላሽ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል፤ ህገወጥ ተቃውሞ እያደረጋችሁ ነው፤ መብታችሁን መጠየቅና ቅሬታ ማቅረብ ከፈለጋችሁ ኮሚቴ ምረጡና በኮሚቴ ጠይቁ” የሚል ነው ብሏል፡፡ “ኮሚቴ አንመርጥም፤ ለጥቃት ይዳረጉብናል” ብለን ለመከላከል ብንሞክርም፣” ይህ ካልሆነ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ተበተኑ” ተብለን ተበትነናል፤ አቤቱታችን ሰሚ አጥቶ እንዲሁ የሚመጣውን ለማየት ቁጭ ብለናል ብሏል - ወጣቱ፡፡
ወ/ሮ ሂክመት በቦሌ ክ/ከተማ በተለምዶ 17/17 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የልብስ መሸጫ ሱቅ አላቸው፡፡ ሰሞኑን በተጣለባቸው “የግብር እዳ” ጤናቸው መቃወሱን ይናገራሉ፡፡ “ቡቲክ ውስጥ የምውለው እቤት ከመዋል ይሻላል በሚል እንጂ እንኳን በቀን 3700 ብር ልሸጥ አንድም ቲ-ሸርትና አንድም ሱሪ ሳልሸጥ የምውልበት ቀን’ኮ ብዙ ነው” ይላሉ፤ተገምቶ የተነገራቸውን የቀን ገቢ አስመልክተው ሲያስረዱ፡፡  “በቀን 3700 ብር ከሸጥኩ በዓመት 1.4 ሚ. ብር እሸጣለሁ እንደ ማለት ነው፤ ይሄን ሁሉ የምሸጥና ገቢ የማገኝ ከሆነ ላለፉት አራት ዓመታት ባገኘሁት ገቢ እንደ ባለ ሀብቶቹ ፎቅ እገነባ ነበር” ብለዋል፤ ወ/ሮ ሂክመት፡፡
“የሱቅ ኪራይ መክፈል እያቃተኝ አንዳንዴ ባለቤቴን አስጨንቄ እከፍላለሁ” ያሉት ወይዘሮዋ፤ “እንዲህ ዓይነት እዳ ከመሸከምና በሽታ ላይ ከመውደቅ ለምን ከርችሜው ቤቴ ቁጭ ብዬ ልጆቼን አላሳድግም?” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር በመሆን ሲጨቃጨቁ መሰንበታቸውን ጠቁመው፤ በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ ለዛሬ ቀጥረውናል ብለዋል፡፡
የ32 ዓመቷ ፍቅርተ ገድሉ፤ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ ለ6 ዓመታት በኩዌት ስትሰራ ቆይታ ከተመለሰች አራት ዓመቷ ነው፡፡ የራሷን ስራ ለመስራት በማቀድ፣ ፀጉር ቤትና ሽሮ ቤት ከፍታ ስትሰራ እንደነበር ያወሳችው ፍቅርተ፤ ለኪሳራ በመዳረጓ የካፌ አስተናጋጅ ሆኗ መቀጠሯን ትናገራለች፡፡ ይህም የልቧን አላደርስ ስላላት፣ ቡና የምታፈላበትን በረንዳ በወር ሁለት ሺህ ብር ተከራይታ የጀበና ቡና እያፈላች መሸጥ መጀመሯን ትናገራለች፡፡ ምንም እንኳን የጀበና ቡና ሥራው ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በቀን 2500 ብር ገቢ ታገኛለች መባሏ አገሯ ላይ የመስራት ተስፋዋን እንደ ጉም እንዳተነነው ፍቅርተ በምሬት ትናገራለች። “እውነት የጀበና ቡና ሸጣ በቀን 2500 ብር ታገኛለች ብለው ሳይሆን ለመለወጥ ያለኝን ተስፋ ለማሟጠጥ ነው” የምትለው ወጣቷ፤ ”እዚህ ያለው እንደዚህ የሚማረር ከሆነ የተሰደደውስ ምን ተስፋ ኖሮት ይመለሳል?” በማለት ትጠይቃለች፡፡
 የጀበና ቡና ገበያዋን በተመለከተ ስታስረዳም፤”በቀን  መቶና 150 ብር ብሸጥም ስኳር፣ ከሰል፣ ቡና፣ የራሴ ጉልበት አለበት፤ ለዚያውም 150 ብር የሸጥኩበት ቀን በጣም በቁጥር ነው፤ በተለይ ክረምቱ ከገባ በኋላ በረንዳው ስለሚያፈስ ገበያ ቀዝቅዟል፤በዚህ የተነሳ ክረምቱ እስኪያልፍ ስራውን ለማቆም እያሰብኩ ነበር” ብላለች፡፡ “እንዴት የጀበና ቡና እየሸጥኩ በቀን 2500 ብር ትሸጫለሽ ትላላችሁ? ከየትስ አምጥቼ እከፍላለሁ?” ብዬ ብጠይቃቸው፣ ‹‹በቀን ከምትሸጭው ላይ ለምን እቁብ እየጣልሽ አጠራቅመሽ አትከፍይም” ሲሉ ተሳለቁብኝ ያለችው ፍቅርተ፤አሁን እንደገና  ልቤ ለስደት ተነሳስቷል ብላለች፡፡  
ወጣት ባልና ሚስት ናቸው፤ እሱ ታዋቂ የፀጉር ስታይሊስት ነው፡፡ ባለቤቱም በሹሩባና በፀጉር ስፌት የተካነች ናት፡፡  ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም በተለያየ የውበት ሳሎን ተቀጥረው ይሰሩ  እንደነበር ይናገራሉ። “የራሳችንን የውበት ሳሎን የመክፈት ሀሳብ ስለነበረን እቁብ እንጥል ነበር፤ከረጅም ጊዜ ትግል በኋላ እቁብ አሰባስበን አራዳ ክ/ከተማ በተለምዶ ገዳም ሰፈር በሚባለው አካባቢ አንዲት ጠባብ ቤት በወር 5 ሺህ ብር ተከራይተን፣ ግማሹን የውበት መሳሪያ ገዝተን፣ ግማሹን በኪራይ አሟልተን፣ የውበት ሳሎን ከፈትን” ይላሉ፤ጥንዶቹ፡፡  ‹‹እርግጥ ነው የራሳችንን የውበት ሳሎን ከከፈትን በኋላ ተቀጥረን እንሰራባቸው ከነበሩ የውበት ሳሎኖች ደንበኞቻችን ተከትለውን መጥተዋል፤ የማደግና የመለወጥ ተስፋ ነበረን›› የሚሉት ባልና ሚስቱ፤ሰሞኑን በቀን 2800 ብር ታስገባላችሁ ሲባሉ በድንጋጤ ክው ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ግን እኮ እዚህ እኛው አካባቢ በቀን 10 እና 25 ሺህ ብር ያስገባል የሚባለው ሬስቶራንት የተገመተለትን ብትሰሙ  በሳቅ ትሞታላችሁ፤በቀን 1800 ብር ነው” ያለው ወጣቱ የውበት ሳሎን ባለቤት፤”አሁን ከተማዋ ላይ ትንሽ አብዶ የማሳበድ ስራ እየተሰራ ይመስላል” ብሏል፤የተሰማውን ሲገልጽ፡፡
 በቀን ትሰራለህ የተባልኩት በዓመት ሲባዛ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ነው ያለው ወጣቱ፤ ግብሩ የዚህ 20 በመቶ ሲሆን ስንት ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ራሱ ያሳብዳል ይላል፡፡ “ለመሆኑ የሚገምቱት አካላት በምን መስፈርት እንደሚገምቱ፣ መነሻቸው ምን እንደሆነ፣ መንግስት ለነጋዴው ግልፅ አድርጓል ወይስ ስራው በአቦ ሰጡኝ ነው የሚሰራው?” ሲል ይጠይቃል፤ወጣቱ፡፡ ቀጣይ ዕቅዳቸውን በተመለከተ ጥንዶቹ ሲናገሩ፤”ለጉዳዩ መንግስት መፍትሄ ካልሰጠና እልባት ካልተገኘ ወደተቀጣሪነታችን እንመለሳለን” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ፤በግመታው ላይ የግንዛቤ ችግር መኖሩንና ህብረተሰቡን ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ተገቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ የታክስ ፕሮግራምና ልማት ሥራዎች ዘርፍ ም/ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የዕለት ገቢ ግምት መነሻ ግብር ከፋዩ ራሱ ያቀረበው መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ቅሬታ አለኝ የሚል አካል ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል በአግባቡ የማቅረብ መብት አለው ብለዋል፡፡ የንግድ ሥራው ባለበት አካባቢ ያለው የንግድ እንቅስቃሴና አማካይ የዕለት ገቢ ታሳቢ ተደርጎ ግምቱ መሰራቱንም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቅሬታዎች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን የጠቆሙት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች፤ ማንኛውም ግብር ከፋይ ቅሬታውን ከወረዳ ጀምሮ ላሉ ማዕከላት ማቅረብ እንደሚችልና ቅሬታውን ሲያቀርብ ግን በግል ብቻ መሆን እንዳለበት፣ በቡድን ተደራጅቶ  ቅሬታ ማቅረብ እንደማይቻልም አክለው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሰጥና የሚያስረዳ ኮሚቴ መቋቋሙንም  ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

Read 13367 times