Saturday, 26 August 2017 12:21

የመምህር የሻው ተሰማና የደራሲው ፍጥጫ

Written by  ቀለሙ ዘለቀ
Rate this item
(0 votes)

  ደራሲ ይባቤ አዳነ፣ ለአንባቢያን እነሆ ካላቸው አራት መጻሕፍቱ አንዱ የሆነውና በሳል ብዕር ያረፈበት የተባለለት ዘሩባቤል (አክሳሳፎስ) መጽሐፍ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም.  በዋቢሸበሌ ሆቴል ሲመረቅ ታድሜ ነበር፡፡ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ከሌሎች የመጽሐፍት ምረቃ መርሐ ግብሮች ለየት የሚያደርጉ ክስተቶች ታይተዋል፡፡  
ከነዚህም መካከል፡-   
* የቅኔ ዘረፋ (በሦስት እጹብ ድንቅ የተባለላቸው የቅኔ መምህራን) የሙልሙል ዳቦ ዕደላ (ዕለቱ ቡሔ መሆኑን ልብ ይሏል)
የቡሔ ጭፈራ…
የእምዬ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ በዓለ ልደትም ሻማ ተለኩሶና አስደናቂ ታሪካቸው በፕሮግራም መሪው በጋዜጠኛ በፈቃዱ ዓባይ አማካኝነት ተደምጦ በክብር ተዘክሯል፡፡ ‹‹ከአለፉት ድንቅ መሪዎቻችን መልካም ነገሮቻቸውን እንጂ መጥፎ መጥፎውን ብናነፈንፍ ምን ሊጠቅመን?›› የሚል መልዕክትም አስተላልፏል፤ የፕሮግራም መሪው፡፡
ይህ ሁሉ በታየበት ሁኔታ ነው እንግዲህ የመጽሐፍ ዳሠሣ ሰዓት ደርሶ፣ የመጀመሪያ አቅራቢ የሆነው ሃያሲና መምህር የሻው ተሰማ፣ ወደ መድረክ እንዲወጣ የተጋበዘው፡፡ የሻው ተሰማ ግን ወደ መድረክ ብቻውን መውጣት የፈለገ አይመስልም፣ የደራሲውን እጅ ጨብጦ ይዞት ወጣና፣ የተዘጋጀላቸው ወንበር ላይ ተሠየሙ። የሻው፣ ክርኖቹን ጠረጴዛው ላይ አስመርኩዞ፣ የድምፅ ማጉያውን በሁለት እጆቹ ጨበጠ፡፡ በቀጥታ ወደ ሙግቱ ከማምራቱ በፊት የልጅነት ትዝታ ያጫረበትን የቡሔ ዜማውን በኦሮምኛና በአማርኛ አቀለጠውና ታዳሚውን አስደመመው፡፡ አዚሞ እንደ ጨረሰ፣ ደራሲው አብሮት እንዲሆን ያደረገበት ምክንያት የመጽሐፍ ዳሠሣውን ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ ማቅረብ በመፈለጉ እንደሆነ ጠቁሞ፣ ወደ ደራሲው ፊቱን ቀልበስ አድርጎ፤ ‹‹እንደዚህ ቢሆን ጥሩ ይመስለኛል፤ አይመስልህም ይባቤ?›› አለ የሻው፡፡ ይባቤም ‹‹ይቻላል›› አለ በልበ ሙሉነት፡፡ የሻውም ጉሮሮውን ሞርዶ፣ የመጀመሪያ ጥያቄውን ሰነዘረና ፍጥጫው ተጀመረ፡፡
የሻው፡- በዚህ መጽሐፍ ልታስተላልፍልን የፈለግኸው ምንድነው?
ይባቤ፡- ጥበብንና ኃያልነቱን፡፡
የሻው፡- ይህ መጽሐፍ ሁለት ተፋላሚ ሐሳቦችን ይዞ በሚጓዝ ስልት ነው የተጻፈው፡፡ ለምን በዚህ ስልት መጻፍ ፈለግኽ?
ይባቤ፡-  አዎ፤ እኔ በየትኛውም ጉዳይ ከሌሎች መለየትን እፈልጋለሁ፡፡ አረማመዴ  ሳይቀር…
የሻው፡- በአጭሩ፤ በአጭሩ ለምን…?
ይባቤ፡- ሁለት ተፋላሚ (ተቃርኖ) ሐሳቦችን ይዞ እንዲጓዝ ያደረግሁበት አንዱ፡- በዓለም ላይ ያለውን ተቃርኖ ለመወከል ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እኩዩን በሠናዩ   እንዲሸነፍ የማስቻል ጥበብን ለማስካን ስል በዚህ ስልት ከተብኩት፡፡
የሻው፡- የፈጠርካቸውን ገፀ ባሕርያት ታውቃቸዋለህ? ለምሳሌ እግዚአብሔር ፍጡሮቹን        አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል፡፡ ጨጓራህ የሚሠራውን እንዴት እንደሚሠራ፤ ኩላሊትህ ማጽዳቱን ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚያፀዳ ወዘተ አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ አንተና እኔ ግን ኩላሊታችን ማጽዳቱን እንጂ እንዴት እንደሚያጸዳ፤ በአሁኑ ሰዓት ራሱ ምን እያደረገ እንደሆነ፤ በአጠቃላይ የተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ተግባሮቻቸውን እናውቅ ይሆናል እንጂ እንዴት እንደሚያከናውኑ አናውቅም። ፈጣሪያቸው ግን ያውቃቸዋል፡፡ አንተ የፈጠርካቸውን ገፀ ባሕርያት፣ የዚህን ያክል ታውቃቸዋለህ?
ይባቤ፡- እግዚአብሔር ፍጡሮቹን በሚያውቃቸው ደረጃ የኔን ፍጡሮች አውቃቸዋለሁ ካልኩ፣ ከእርሱ ጋር መተካከል ስለሚሆን አውቃቸዋለሁ አልልም፡፡
የሻው፡- ስለዚህ አታውቃቸውም?
ይባቤ፡- አውቃቸዋለሁ፡፡
የሻው፡- በጭራሽ አታውቃቸውም፡፡
ይባቤ፡- በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡
የሻው፡- ካወቅሃቸው፣ ከፈጠርካቸው ገፀ ባሕርያት መካከል ልዕለ ሰብእ (super humanity)     ያላቸው አሉ፡፡ ልክ ነኝ?
ይባቤ፡- አዎ አሉ፡፡
የሻው፡- ታዲያ እነዚህ ልዕለ ሰብእ ባሕርያት ከተጓናጸፉት ገፀ ባሕርያት መካከል አንዱ ማናት ያች እንግሊዛዊቷ… ማን ነበረች?
ይባቤ፡- ዩክሊና፡፡
የሻው፡- አዎ፤ ዩክሊና፡፡ ከእርሷ ጋር የነበረው እንደዚያ ያለ የቀነዘረ ወሲብ አግባብ ነው? … እርሷ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው የቶኒ ብሌር ደንገጡር ወይም ፕሮቶኮሊስት ናት፡፡ እንደዚያ ያለ ልዕለ ሰብእ ያለው ዘሩባቤል፣ ዩክሊናን በወሲብ አቀንዝሮ የሚፈልገውን ነገር ከሚያገኝ በሌላ መንገድ አይቻልም ነበር?
ይባቤ፡- እርሷ የጎደለባት ወሲብ ብቻ ነው፡፡ ሌላ የጎደለባት ነገር ስለሌለ፣ ሌላ ደካማ ጎን የላትም፡፡
የሻው፡- ታዲያ እንዲያ ያለ ልዕለ ሰብእ ያለው ሰው፣ እንደዚያ ያለ ወሲብ ነውር አይሆንም? ለኔ በጣም ነውር ሆኖ ነው የተሰማኝ፡፡
ይባቤ፡- እንደዚህ ያለ ወሲብ ነውር ነው የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ ነውርም አይደለም፡፡ ወሲቡ ስሜት ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን ለዓላማ እስከሆነ ድረስ በፍጹም ነውር ሊሆን አይችልም፡፡
የሻው፡- እንዴ! ነውር ነው እንጂ፡፡ (ኮስተር እያለ የመጣ ይመስላል የሻው፡፡)
ይባቤ፡- አይደለም፡፡ ምናልባት አንድ ታሪክ ነቅሰን ብናመሳክር የሚያስታርቀን ይመስለኛል። ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ድረስ ሄዳ፣ ከጠቢቡ ሰሎሞን ጋር ወሲብ ፈጸመች፡፡ የመጀመሪያውን ምኒልክን አስገኘች፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ታቦተ ጽዮንን አናገኝም ነበር፡፡ ስለዚህ ለእንዲህ ዓይነት ዓላማ ተኮር ወሲብ ክብር አለኝ፡፡ ነውር መባል የለበትም። (እንደዚህ ያለውን ወሲብ ነውር ነው ማለት ራሱ ነውር ነው ለማለት የፈለገ መሰለኝ፡፡)
የሻው፡- (በአግራሞትና በጥያቄ አተያይ ታዳሚውን ቃኘት አደረገና) እሺ፡፡ ሤራው ወይም ፕሎቱ ላይ ፈረንጆችን እንቅልፋም አደረግሃቸው፡፡ ፈረንጆቹ ምንም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም። እንዲያው ዝም ብለው ዶርማንት አደረግሃቸው ይባቤ፡፡ ዘሩባቤል ያን ሁሉ ሲያደርግባቸው፣ ፈረንጅን ያህል ፍጡር እንዴት ዝም ይላል?
ይባቤ፡- ዘሩባቤል የጥበብ ሰው ስለሆነ በግርማ ሞገሱ ፀጥ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡ (ይባቤ በደፈናው የመመለሱ ነገር የበዛ መሰለኝ፡፡ የራሱ ምክንያት ኖሮት ሸፋፍኖት አልፎ ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያውያኑን ለመያዝ ፈረንጆቹ ያላደረጉት ፖለቲካዊና የስለላ ጉዞ ያለ አይመስለኝም፡፡ የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር፣ የአውሮፕላን በረራን እስከ ማገድና በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ነፍሳት ሁሉ እንዲገደሉ የሚል አስቸኳይ አዋጅ እስከ ማወጅ መድረሳቸውን መጽሐፉ ላይ አንብቤያለሁ። ለሰላዮቹ አባላትም ኦርብዌር ከተሰኙ የሸረሪት ዝርያዎች ድር የተሰሩ የጥይት መከላከያ ሰደርያ እንዲለብሱ የተደረገው ኢትዮጵያውያኑን አሰነካክሎ ለማስቀረት የሸረቡት እንደሆነ አንብቤያለሁ፡፡ ይባቤ ግን ይሄን ዝርዝር ከመናገር ተቆጥቦ ድፍን ያለ መልስ ሰጥቶ ነው ያለፈው፡፡)
የሻው፡- ከገፀ ባሕርያቶችህ መካከል ብዙዎቹ አንዴ ፖለቲከኛ ይሆናሉ፤ ሌላ ጊዜ ፈላስፋ፤ እንደገና…
ይባቤ፡- (አቋረጠውና) ኑሮው ነው እንደዚያ የሚያደርጋቸው፡፡ (አሁንም አጭርና ድፍን ያለ መልስ ነው የሰጠው፡፡)
የሻው፡- መጽሐፉ የትኛው የልብ ወለድ ዓይነት ነው? ትውፊታዊ ወይስ ዘመናዊ?
ይባቤ፡- ትውፊታዊ…
የሻው፡- (ፈጠን አለ የሻው) ትውፊታዊ ነው ለማለት ማሳያህ ምንድነው?
ይባቤ፡- ዘመናዊም ነው፡፡
የሻው፡- ካንተ እኔ አላውቅም ይባቤ፡፡ ዘመናዊ ሊያስብለው የሚችል ነገር የለምና ትውፊታዊ ነው። አብዛኛውን ነገር የሚነግረን ተራኪው እንጂ ገፀ ባሕርያቱ አይደሉም፡፡ ልቦለዱ አሳታፊ ስላልሆነ ዘመናዊ ነው ልንለው አንችልም፡፡ ልታስተላልፍልን የፈለግኸውን ማስተላለፍ በሚፈለገው ደረጃ ለማስተላለፍ ይመስላል… አብዛኛውን ነጋሪው አንተ ነህ፤ ካንተ ባላውቅም፡፡
ይባቤ፡- (ራሱን በአሉታ እየወዘወዘ) አይ ታውቃለህ፡፡ እ… (ሊሞግተው አስቦ መልሶ የዋጠው ይመስላል፡፡ ከዚህ ቀደም በደንብ እንደሚተዋወቁ ያሳብቅባቸዋል፡፡ ለዚያ ይመስላል ካንተ እኔ ባላውቅም የሚል ነገር የሚደጋገመው፡፡ መከባበራቸው ቁልጭ ብሎ ይታይ ነበር፡፡)
የሻው፡- ሌላ ጥያቄ ልጠይቅ
ይባቤ፡- ፕሎቱ…
የሻው፡- (አቋረጠው)  አባቴ ይሙት ወደ ቴክኒክ አልመለስም፡፡ ቴክኒክ ላይ ጨርሻለሁ፡፡ መጽሐፎቹ ተመልሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተዋል። ወደ ኢትዮጵያ በመመለሳቸው ምን እንጠቀማለን? ኢትዮጵያ የምትጠቀመው ነገር ምንድነው?ከዚህ በኋላስ የምንጠቀምባቸው ይመስልሃል?
ይባቤ፡- በጣም እንጂ፡፡ የኔ ትኩረት፣ የጥበብ መጻሕፍት ወይም ጥበብ አለን ወይስ የለንም የሚለውን ብዥታ ማጥራት ነው፡፡ የኔ ትውልድ የሆነ ለውጥ እንደሚያመጣ አምናለሁ፤ እንደዛ ነው የሚሰማኝ፡፡ ለዚህ ትውልድ የማደርገው ቢኖር፣ ያለንን በማሳወቅ፣ በማንነቱ የጸና፣ ብርቱ ግድግዳ የሆነ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ይኼው ነው የመጽሐፉ ትኩረት፡፡
የሻው፡- የመጨረሻ ጥያቄ፣ ይኼን መጽሐፍ ባትጽፈው ኖሮ፣ ምን የሚጎድል ይመስልሃል?
ይባቤ፡- (በተመስጦ ሆኖ ባይጻፍ፣ የሚጎድለው እየታወሰው ይመስላል) ኡ… በጣም ብዙ፡፡ በጣም ብዙ፡፡ ባልጽፈው ኖሮ… ኡ… ምን ልበልህ፤ በጣም እጅግ በጣም የሚጎድል ነገር ነበር፡፡
የሻው፡- (እንደ መነሣት ብሎ) አመሰግናለሁ! ብሎ ደራሲውን ጨበጠው፡፡
ይባቤ፡- እኔም አመሰግናለሁ አለውና፣ ጨበጠው። ከዚህ በኋላ ገጣምያን (ሰሎሞን ሞገስ፤ በላይ በቀለ ወያ፣ መዝገበቃል አየለ…) በጣፋጭ አንደበቶቻቸው በሳል ግጥሞቻቸውን አስኮምኩመውናል፡፡ ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋዕል በበኩሉ፤ ጣፋጭ ወጉን ይዞ መድረኩን ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ እርሱም እንደ የሻው ደራሲውን ይዞት ነው የወጣው፡፡ (እነዚህ ሰዎች ለደራሲው ከሌላው የተለየ ፍቅርና አክብሮት ኖሯቸው ነው ወይስ ስልቱን ለመቀየር በሚል ብቻ ይሆን?)
በመቀጠል የመጽሐፍ ዳሠሣ ያቀረበው ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ ነበር፡፡ እርሱ ከየሻው በብዙ በተለየ አተያይና መንገድ ነው ያቀረበው፡፡ መጽሐፉን በሚገባው ልክ የተረዳው ይመስላል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት  ክፍል ከፈቀደልኝ፣ የአበረን ዳሰሳ ሳምንት  እናየዋለን፡፡ ቸር እንሰንብት!   

Read 1855 times