Tuesday, 02 January 2018 09:33

ፓርቲዎች በድርድር የተስማሙባቸው 3 የምርጫ አዋጆች በፓርላማው እንዳይፀድቁ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፤ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ድርድር፤ የሰጥቶ መቀበል መርህን ያልተከተለ በመሆኑ፣ በፓርቲዎች ስምምነት ተደርሶባቸዋል የተባሉ የምርጫ ስነ ስርአት ህጎች በፓርላማው እንዳይፀድቁ ጠየቀ፡፡
በቅርቡ ኢህአዴግና ኢራፓን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስማምተውባቸዋል የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፤ ሰጥቶ መቀበል የሚለውን የድርድር አለማቀፍ መርህ በተከተለ መልኩ በተደረገ ድርድር የተሻሻሉ አለመሆናቸውንና በስፋት የገዥው ፓርቲ ፍላጎት ብቻ የተንፀባረቀባቸው መሆኑን ያተተው ፓርቲው አዋጆቹ እንዲፀድቁ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መላካቸውን ተቃውሟል፡፡
ኢራፓ “የህውሓት/ኢህአዴግ ከኔ ውጪ ለአሳር የፓርቲዎች ድርድር” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫው፤ በተቃዋሚዎች እየቀረበ ያሉ አጀንዳዎችን ኢህአዴግ በዘፈቀደ ወደ ጎን እየገፋቸው የራሱን ብቻ እያቀረበ ነው ብሏል፡፡
በእነዚህ ሶስት የምርጫ ጉዳይ አዋጆች ላይም ኢራፓ ያቀረባቸው አንኳር ነጥቦች ተቀባይነት ማጣቱንና አዋጆቹ በስፋት በኢህአዴግ የበላይነት ተንፀባርቆባቸው የተሻሻሉ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
“ፍሬ አልባና ፋይዳ ቢስ በሆነ መልኩ የፓርቲዎች ድርድር እየተካሄደ መሆኑ በእጅጉ አሣዛኝ ነው” ያለው ፓርቲው፤ በቀጣይ ለድርድር በተመረጡት የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅና የብሄራዊ መግባባት አጀንዳዎች በመሠረታዊ የድርድር ሰጥቶ መቀበል መርህ የማይከናወኑ ከሆነ፣ ከድርድሩ አቋርጦ ለመውጣት እንደሚገደድ አስታውቋል፡፡
ድርድሩ አንድ ዓመት ያህል ማስቆጠሩን የጠቀሠው ፓርቲው፤ በተቀመጠለት አላማና የጊዜ ሰሌዳ ወቅቱን ጠብቆ እየተካሄደ አለመሆኑንም ጠቁሟል፡፡
በፓርዎች ስምምነት ተደርሶባቸዋል በተባሉት ሶስት የምርጫ ጉዳይ አዋጆች ላይ ያለውን ልዩነት ማስመዝገቡን ያመለከተው ፓርቲው፤ በቀጣይም አዋጆቹ ወደ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ መላካቸውን በመቃወም አዋጆቹ እንዳይፀድቁ ጠይቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ መላኩ መሰለ፤ “እኛ ወደ ፓርላማው የተላከው የህግ ረቂቅ ሰነድ ህገ ወጥ ነው የሚል አቋም ነው ያለን፤ ስለዚህ ፓርላማው እንዳያፀድቀው እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡

Read 1994 times