Saturday, 07 April 2018 00:00

አንገብጋቢው የገለልተኛ ተቋማት ነገር???

Written by  በአብርሃም ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

“አዕምሮ የሌለው ህዝብ ሥርዓት የለውም፡፡ ሥርዓት የሌለው ህዝብ የደለደለ ሃይል የለውም፡፡ የሃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጅ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥርዓት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በህግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች”
 
    ዴሞክራሲ ወፍ ዘራሽ ተክል አይደለችም፤ የትም ቦታ በቅላ የምታብብ፡፡ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከደረጀባቸው አገራት ኢምፖርት የምትደረግ አይደለችም፤ በገንዘብ ገዝተው ወደ አገር ቤት እንደሚያስገቧት ሸቀጥ፡፡ ከሁሉም በላይ የዴሞክራሲ ችግኝ ተዘርቶ የሚያብበው ለማንንም የማይወግኑ፣ ነጻ ተቋማት ዕውን ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ተቋማት ወይም ስርዓታት በእንግሊዝኛ አጠራሩ institutions የሚባለው መሆኑን ነው፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ብዙ ወሳኝ ነጥቦችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ መጣጥፍ ግን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ፣ የገለልተኛ ተቋማት ሚና አንገብጋቢነትና አስፈላጊነትን ይበልጥ አጽንኦት ለመስጠት ይሞክራል፡፡ መታለፍ የሌለበት ጥያቄ፣ በሃገራችን ገለልተኛ በመሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በአንጻራዊ ነጻነት የሚያገለግሉ፣ ተዓማኒነት ያተረፉ ተቋማት በመመስረት ረገድ ምን ያህል ርቀት ተጉዘናል?
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር፤ “የሕዝብ ፍላጎት ከፍትህ የተፋታ ደረቅ ሕግ ሳይሆን፣በፍትህ የተቃኘ፣ ለፍትህ የቆመ የሕግ ስርዓትን ነው። የሕዝብ ፍላጎት የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኛና ለፍትህ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናኢ እንዲሆኑ ነው” በማለት የገለልተኛ ተቋማት ሚና ወሳኝነትን በግልጽ ቋንቋ ተናግረውታል፡፡
ተቋማት በአንድ ሃገር ውስጥ የሰዎችና የማህበረሰብ መስተጋብሮች ደርዝ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ የስርዓታት ስብስቦች ናቸው፡፡ እነዚህ የስርዓታት ስብስቦች እንደ ልማዶች፣ ወጎች፣ ስነምግባሮች፣ ህገ-መንግስቶችና ሌሎች ህጎች… የያዙ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ያብራራሉ፡፡ ዩሱፍ ያሲን ‘‘ኢትዮጵያዊነት፤አሰባሳቢ ማንነት…’’ በተባለው መጽሐፋቸው ስለ ተቋ (ም) ማት ምንነት ሲያብራሩ፤ “የማይዳሰሱ የግንኙነት ክሮች ቁጥርጥር ነው፡፡ የስርዓት አደረጃጀት ነው፡፡…ለዘመናት ሲወርድ ሲወራረድ በተመሰረቱ ግንኙነቶች፤ክሮችና ደንቦች በህብረተሰቡ ቀጣይነት፤ስር በሰደደ ቅቡልነትና ተወራራሽነት አማካይነት በህሊና የተቀረጸ የአኗኗር ስርዓት አደረጃጀት ነው” ይላሉ፡፡
ስለ ተቋማት ምንነት፣ አስፈላጊነትና ሚና በሚመለከት በቅርቡ በጎረቤታችን ኬንያ ተደርጎ  የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጥሩ አብነት ነው፡፡ በወቅቱ ኡሁሩ ኬንያታ በ54.3 በመቶ ድምጽ ምርጫውን ማሸነፋቸው ተበሰረ፡፡ የማሸነፋቸው ብስራት በአገራቸው ብቻ ሳይሆን በአለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ ሳይቀር ምርጫው “ነጻና ፍትሃዊ” ነበር ሲል ዕውቅናን ቸረው። ይሁን እንጂ፣ የኡሁሩ ዋና ተቀናቃኝ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ግን፣ የምርጫው ውጤት ‘‘ተጭበርብሯል’’ በማለት ለሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡ የአገሪቱ ጠ/ፍ/ቤትም፣ አቤቱታውን ተቀብሎ ማጣራት ጀመረ፡፡ በመጨረሻም ምርጫው መጭበርበሩን በመግለጽ፣ ምርጫው እንዲደገም ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ምርጫውን እንዳሸነፉ የተገለጸላቸው ኡሁሩ ኬንያታም፣ የምርጫው ውጤት እየጎመዘዛቸውም ቢሆን በፀጋ በመቀበላቸው፣ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ አድርጎት ነበር፡፡ የጠ/ፍ/ቤቱ ውሳኔም ሰፊ መነጋገርያ ሆኖ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ ለምን መነጋገርያ ሆነ? የሚለው ነው፡፡ በአፍሪካ ምድር በስልጣን
ላይ የነበረ መሪ፣ ለዚያውም እጅግ በጠባብ ውጤት “አሸነፈ” ተብሎ የታወጀው ምርጫ፣ በአገሪቱ ጠ/ፍ/ቤት ውድቅ መደረጉ፣ የኬንያ የፍትህ ተቋማት ገለልተኝነትና ነጻነት ነበር- ጣትን በከንፈር አስጭኖ ያስገረመው፡፡ ይኸው ነው የገለልተኛ ተቋማት ዋና ዓላማና ተግባር፡፡
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁልፍ የቤት ስራ መሆን ይኖርበታል፤ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ተግባር፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድ፣ አንጻራዊ አመኔታን ያገኙ፣ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት ዕውን ሳይደረጉ፣ ህዝብና መንግስት ሊናበቡና ሊደማመጡ ፈጽሞ አይችሉም፡፡ ገለልተኛ ተቋማት በሌሉበት፣ የዜጎች እውነተኛ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ዕውን ይሆናል ብሎ መጠበቅ፤ እንክርዳድ ዘርቶ ስንዴን ለማጨድ እንደመጠበቅ ነው፡፡
ህብረተሰቡ መገፋቱን የሚናገሩለት፤መበደሉን አቤት የሚሉለት ቅቡል የሆኑ ተቋማት አጥብቆ ይፈልጋል። ድምጹን ጮክ አድርገው የሚያስተጋቡለት ተቋማት ይናፍቃል፡፡ ደግሞም ለአመታት ተንከባሎ እዚህ የዘለቀው አመጽ የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች፣ምንጫቸው የቱ ጋ ነው? ብለን ብንመረምር፣ መገፋትንና መበደልን አቤት የሚባልባቸው፣ የገለልተኛ ተቋማት መሽመድመድ ነው - ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እንዲሁም የግልጽነትና የተጠያቂነት መሟሸሽ፣ ከተቋማት ገለልተኝነትና ነጻነት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ እንዳላቸው ሳይዘነጋ፡፡
ገለልተኛ ተቋማት በተዳከሙበትና ባልተፈጠሩበት ህብረተሰብ ውስጥ፣ ፈላጭ ቆራጭነት አንገቷን አስግጋ በኩራት ስትራመድ፣ ፍትህ አንገቷን ትደፋለች፡፡ ንቅዘትና ሌብነት በሁሉም መስክ ተንሰራፍቶ መደላድሉን ሲያበጅ፣ በራስ ልፋትና ጥረት ሰርቶ መክበርን፣ ሰማይን በጦር አነጣጥሮ ለመውጋት የመሞከር ያህል፤ የግለሰቡን ውስጣዊ ሃይል ያልፈሰፍሷል፡፡ አፈ ጮሌነት እንደ ሙያ ተቆጥሮ በየመድረኩ ሲፎልል፣ ምክንያታዊነት ወደ ጎን ይገፋል፡፡ ለዚህም ነው የነጻና ገለልተኛ ተቋማት አስተዋጽኦና ሚና ከፍተኛ ነው የሚባለው፡፡
የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጽንሰት፣ውልደትና እድገት እምብርቱ፣ የገለልተኛ ተቋማት ማበብና መጎልበት ነው። ዛሬ በሃገራችን የህብረተሰቡን የልብ ትርታ በማድመጥ፣ የህብረተሰቡ እውነተኛ ፍላጎትና ጥያቄ የሚነገርበት ሚዲያ ያለመኖር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ እያስከፈለንም ነው፡፡ የህብረተሰቡ አንጻራዊ አመኔታና ተቀባይነት ያላቸው የሲቪክ ተቋማት ባለመኖራቸው፣ በህዝብና በመንግስት መካከል መኖር ያለበት መሸጋገርያ ድልድይ ተሰብሯል፡፡ በዚህ ምክንያት የእርስ በርስ መደማመጥ ጣር ሆኗል፡፡ ተቋማት በአንድ ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚናና አስፈላጊነት አስመልክተው ዩሱፍ ያሲን በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ”በገዥዎችና በተገዥዎች መሃል የመገናኛ አውታር በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያሰፋሉ፤ ግንኙነቱ የተመቻቸ እንዲሆን ያግዛሉ… የተቋማት መኖር በህብረተሰቡ ውስጥ የተሳትፎ ማነስን፣ ኢ-ህጋዊነትንና አለመረጋጋትን ሁሉ ያስወግዳሉ፡፡”
የመንግስት ለውጥ በተደረገ ቁጥር የማይለዋወጡ፣ የህብረተሰቡን ተዓማኒነት ያተረፉ ተቋማት እንዲኖሩ ማስቻል ለነገ ብለው የማያሳድሩት፤ አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፣ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በፓርላማው የመጀመርያ ንግግራቸው አጽንኦት የሰጡት ቢሆንም፣ ንግግራቸው መሬት ወርዶ በተግባር ተተርጉሞ  ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲያውም እቅዳቸው ገቢራዊ ይሆን ዘንድ የተቋማቱ ገለልተኛነት እጅግ ወሳኝ ነው። ያለበለዚያ በቀዳዳ በርሜል፣ ውሃ እንደ መሙላት ነው። ያለ ገለልተኛና ነጻ ተቋማት፣ ስለ ፍትህ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ ስለ ህግ የበላይነት መደስኮርም፣ አንዲት ጋት እንኳ፣ አሁን ካለንበት ፈቅ እንደማያደርገን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እውቁ ምሁር ገ/ህይወት ባይከዳኝ ‘‘አጤ ምኒሊክ’’ በተሰኘው ድርሳናቸው አጽንኦት ሰጥተው ያሳሰቡትን፤”አዕምሮ የሌለው ህዝብ ስርዓት የለውም፡፡ ስርዓት የሌለው ህዝብ የደለደለ ሃይል የለውም፡፡ የሃይል ምንጭ ስርዓት ነው እንጅ የሰራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ስርዓት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በህግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች” ያሉትን ልብ ማለት ያሻል፡፡

Read 599 times