Saturday, 21 April 2018 12:22

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከባህር ዳር ህዝብ ጋር ይወያያሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

 “የወልቃይት ጉዳይ በህገ መንግሥቱ መሰረት ምላሽ ያገኛል”
               የጎንደር ህዝብ አዲስ ታሪክ እንደሚሰራ አምናለሁ
           ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በትላንትናው ዕለት ከጎንደር ህዝብ ጋር የተወያዩ ሲሆን ከተሳታፊዎችም በርካታ ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል፡፡ “የወልቃይት ጉዳይ ለምን ምላሽ አላገኘም?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “የወልቃይት ጉዳይ በህገ መንግሥቱ መሰረት ምላሽ ያገኛል” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ ሁለት የወልቃይት ኮሚቴ አባላትንም ለብቻቸው አነጋግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ጎሃ ሆቴል 200 ከሚደርሱ የህዝብ ተወካዮች ጋር ነው የተወያዩት። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም “በኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚ አይደለንም፤ የፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት አለብን፣ የኑሮ ውድነቱ ከአቅም በላይ ሆኖብናል” የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
“በህገ መንግስቱ የተሰጠንን በነፃነት የመናገርና የመቃወም መብት ተጠቅመን ጥያቄዎቻችንን ስናቀርብ ምላሽ አይሰጠንም” የሚል ቅሬታም ከተወካዮች ቀርቧል፡፡
“በሙስና ጉዳይ ክስ ቀርቦባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ለምን አይፈቱም?” የሚል ጥያቄም ከተሳታፊዎች - ተነስቷል፡፡
“ጎንደር በኢንዱስትሪ መንደር እቅድ ውስጥ አለመካተቱ ኢ - ፍትሃዊ ነው፣ በእስር ላይ የሚገኙ የደርግ ባለስልጣናትን ጨምሮ ፖለቲከኞች በሙሉ ሊፈቱ ይገባል፣ የአማራ ክልልን ከሱዳን የሚያዋስነው ድንበር መፍትሄ ማግኘት አለበት፣ የመከላከያ ሰራዊቱ ለአንድ ወገን ያደላ ሳይሆን ህዝባዊ ወገንተኝነት የተላበሰ መሆን አለበት” የሚሉት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ “ኢትዮጵያ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋታል፤ ይህን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊሰሩበት ይገባል” የሚለውም ተደጋግሞ የቀረበ ሃሳብ ነው፡፡
“ከሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ መፍትሄ መሰጠት አለበት ብዬ አምናለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ድንበር ላይ ያሉ የሁለቱም ወገን ወታደሮች ከአካባቢው እንዲርቁና ህዝቡ በሰላም እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይህንንም ከነገ ጀምሮ እሰራለሁ” ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡ በጣና ፎረም ስብሰባ ላይ ከሚሳተፉት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ጋርም በጉዳዩ ላይ እንደሚነጋገሩ ዶ/ር አብይ አስታውቀዋል፡፡
“ሌሎች ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በተመለከተ ከቃል ምላሽ ይልቅ በተግባር ማሳየቱን እመርጣለሁ” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት የወልቃይት ኮሚቴ አባል አቶ አታላይ ዛፉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀሌ ላይ ስለ ወልቃይት በተናገሩት ነገር ማፈራቸውን ጠቁመው፤ “ከወልቃይት የማንነት ጠያቂዎች አንዱ እኔ ነኝ፣ ብዙዎች የታሰሩበትና የተገደሉበት ጉዳይ ነው፡፡ ጥያቄው የዳያስፖራ አይደለም” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ቀደም ብለው በጎንደር አፄ ፋሲል ስታዲየም ባደረጉት ንግግር፤ “በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎንደር ጉልህ ድርሻ አላት” ብለዋል። የአማርኛን ቋንቋ ወደ ፅሁፍ ቋንቋነት በመቀየር፣ የጎንደር ሊቃውቶች ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የጠቀሱት ዶ/ር አብይ፤ የመነጋገር፣ የመደማመጥ፣ የመከራከርና የመወያየት ባህልም በጎንደር ስር የሰደደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“ጎንደር የድንቅ ታሪክ ባለቤት የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፅኑ መሰረት፣ የጥበብና ውበትም ቤተ እምነትና የድል ተምሳሌት ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአንድነት ምሳሌም ነች ብለዋል፡፡
የጎንደር ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራ ያፈሰሰው ደም፣ የከሰከሰው አጥንትና የከፈለው መስዋዕትነትን የሚመጥን ዲሞክራሲ፣ ልማት፣ ፍትህና ሰላም እንዲያገኝ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል፡፡
“ፍቅርና ሰብአዊነት ከምንግዜውም በላይ ዛሬ ያስፈልገናል” ያሉት ዶ/ር አብይ፤ “ኢትዮጵያ የጋራ ኪዳናችን መነሻና መድረሻችን፤ ብዙ ስንሆን አንድ የመሆኛ ሚስጥራችን - ኖረን በስሟ መጠሪያችን - ሞተን ምድሯ መሆናችን - አብረናትም ሆነን ስስታችን ተደስተንም ናፍቆታችን ለሆነች ውብ ሃገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግና ሁላችንም እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ህዝቡ ለለውጥ ተስፋ ማድረጉን ገልፀው፤ “ይህ ህዝብ ለውጥ በመፈለጉ እርስዎን የለውጥ ምልክትና ተስፋ አድርጎ በመመልከት፣ ከዳር እስከ ሹመቱን ዳር በደስታ ተቀብሎታል” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሃገራችን ህዝብ የለውጥ ፍላጎት ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል ያሉት አቶ ገዱ፤ “እርስዎ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ነፃነትን ለማስፈን በሚያደርጉት ትግል፤ የጎንደር ህዝብ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል አያቅማማም” ብለዋል፡፡
በጎንደር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የአቀባበል ስነ ስርዓት ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መሰንበቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ 1 ሺ ያህል ሰዎች ለበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ መመልመሉ ታውቋል፡፡
ለአቀባበል ከወጡት ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶች “የቅማንት ህዝብ ድምፅ ይከበር”፣ “ለቅማንት ብሔረሰብ የራስ አስተዳደር መፍትሄ ይስጡልን” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ነበር ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ከህዝቡ ጋር እንደሚወያዩ የተገለፀ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን፤ ዛሬ እና ነገ በሚካሄደው 7ኛው ጣና ፎረም ጉባኤ ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

Read 7672 times