Saturday, 12 May 2018 11:35

የኢትዮጵያ የውጪ እዳ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ነው የተባሉት ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት የውጪ ብድር መጠን እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፤ የኢትዮጵያና የዛምቢያ የውጪ እዳ መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራትን የውጪ ብድር አወሳሰድና የእዳ ምጣኔ የሚዳስሰውና ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የማስጠንቀቂያ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ቀደም ሲል በሃካከለኛ ደረጃ ላይ የነበረው የኢትዮጵያና የዛምቢያ የውጪ እዳ መጠን፣ አሁን በከፍተኛ ደረጃ አስጊ ሆኗል ብሏል።
ተቋሙ ቻድ፣ ኤርትራ፣ ሞዛምቢክ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ሱዳንና ዚምባቡዌ በእዳ አዙሪት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም ጠቁሟል - በሪፖርቱ። የኢትዮጵያ የውጭ እዳ መጠን ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት አንፃር የ56.2 በመቶ ድርሻ መያዙን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህም ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው የእዳ ምጣኔ በ2.2 በመቶ መጨመሩን ያመለክታል ብሏል፡፡
ሀገሪቱ ከ2016 አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርቷ አንፃር የእዳ ምጣኔዋ 55 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2017 56 በመቶ ደርሶ ነበር፤ ጫናው ቀጥሎ ገና በ2018 ሩብ ዓመት ላይ 56.2 በመቶ መድረሱ አሳሳቢ ነው ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
የእዳ መጠኑ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ አኳኋን እየጨመረ የመጣው በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠል ሲባል፣ በብድር አዙሪት ውስጥ በመግባቷ ነው ተብሏል፡፡
ሃገሪቱ ኢኮኖሚዋን የውጪ ብድር ላይ ከማንጠልጠል ወጥታ የሃገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን በማዘመንና በማሳደግ፣ ችግሩን ለመቋቋም ጥረት ማድረግ እንዳለባት ተቋሙ አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያ የውጪ እዳ ጫናዋ በአስጊ ሁኔታ እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር ለመሰረታዊ ፍጆታ የሚውሉ የአገር ውስጥ ሸቀጦች ዋጋም ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ ተጠቁሟል። የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረበት 6.7 በመቶ በአሁኑ ወቅት በእጥፍ ጨምሮ፣ ወደ 13.6 በመቶ ማደጉ ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ 40 በመቶ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆመው አይኤምኤፍ፤ ከዚህ ሁኔታ ውስጥ አገግሞ ለመውጣት በእጅጉ ዋጋ ያስከፍላቸዋል ብሏል፡፡ ባለፉት 8 ዓመታት የአፍሪካ ሃገራት የውጭ እዳ መጠን በአርባ በመቶ መጨመሩም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

Read 8127 times