Saturday, 23 June 2018 12:11

የ21ኛውን የዓለም ዋንጫ ዋና መዲና ሞስኮን በጨረፍታ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ክፍል 1
የ21ኛውን የዓለም ዋንጫ መክፈቻና ያስተናገደችውና   የዋንጫ ጨዋታው የሚካሄድባት የራሽያ ዋና  ከተማ ሞስኮ በታሪካዊ ቅርሶች፤ ስነህንፃዎች፤ መሰረተልማቶች እና በሰለጠኑ ህዝቦች ያሸበረቀች ናት፡፡ በሞስኮ ስፖርቲቭና በተባለው  አካባቢ የሚገኘው የራሽያ ብሄራዊ ስታድዬም ሉዝሂኒኪ ከ78ሺ በላይ ተመልካች የሚያስተናግድ ሲሆን ስታድዬሙ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ሰሞን የዓለም ህዝቦች መናሐርያ ሆኖ  ትኩረት ቢስብም ፤ በከተማዋ ከ450 በላይ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማቶችም ይገኙባታል፡፡
ከተማዋ በ1147 እንደተቆረቆረች የታሪክ መዛግብት የሚያመለክቱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል አንዳንድ አርኪዮሎጂስቶች ከተማዋ በሰፈረችበት መሬት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነዋሪዎች እንደነበሩባት ይገልፃሉ፡፡ በቆዳ ስፋቷ ከአውሮፓ ግንባር ቀደም ስትሆን በዓለም ደግሞ 3ኛ ደረጃ የሆነችው 2.511 ስኩዌር ኪሎሜትር በሚሸፍነው ግዛቷ ሲሆን፤  በህዝብ ብዛቷ ከአውሮፓ ከተሞች  በግንባር ቀደምነት የምትጠቀሰው  ከ18 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት ስለሚገመት ነው፡፡ ከራሽያ አጠቃላይ ግዛት 0.25 በመቶውን የምትሸፍነው ሞስኮ ለነገሩ ‹‹ሞስኮቫይትስ›› ወይም ሞስኳዊ  ነን ብለው የሚያስቡ ከ30 ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ከራሽያውን ባሻገር የታታር፤ የጆርጅያ፤ የዩክሬን፤ የቤለሩስ እና የሌሎች የቀድሞ የሶቭየት ህብረት አካል የነበሩ ግዛቶች ተወላጆች ዜጎች በከተማዋ  ነዋሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡
በቢሊዬነሮች ብዛት ከዓለማችን ትልልቅ ከተሞች ግንባር ቀደም ሆናም ትጠቀሳለች፡፡ በመዲናዋ ከ79 በላይ ቢሊየነሮችና ከ68ሺ በላይ ሚሊዬነሮች እንደሚገኙ የሚያመለክቱ መረጃዎች የሃብታቸውን መጠን ከ1 ትሪሊየን  በላይ  ይተምኑታል፡፡ ከተማዋን በዓመት እስከ 6 ሚሊዮን ቱሪስት እንደሚጎበኛት ይገመታል፡፡ ከ3000 በላይ ሬስቶራንቶች እና ከ1000 ሆቴሎች የሚገኙባት ከተማዋ፤ በውድ የአኗኗር ሁኔታዎቿ ትታወቃለች፡፡
ታላቁ ሞስኮቫ ወንዝ የከተማዋን 9771 ስኩዌር ኪሎሜትር  የሚሸፍን ሲሆን ከ49 በላይ ድልድዮች በዙርያው ተገንብተውለታል፡፡ በተጨማሪም ከተማዋ  በዙርያዋ ከ140 በላይ ትንንሽ ወንዞች እና ምንጮች፤ 4 ግዙፍ ሃይቆች፤ 400 ኩሬዎች በተፈጥሮ እና በሰውሰራሽ ሁኔታዎች ይገኙባታል፡፡ የከተማዋ ሲሶ በአረንጓዴ አፅዋት፤ በመናፈሻዎች እና ፓርኮች የተሸፈነ ሲሆን ብዙዎቹ ከፍተኛ የመዝናኛ እና የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሚገኙባቸው ናቸው፡፡ በክረምት ወራት ቅዝቃዜው በአማካይ ከኔገቲቭ 6 ዲግሪ ሴንትግሬድ በታች ሲሆን በበጋ ወራት ሙቀቱ ከ18 እስከ 30 ዲግሪሴንትግሬድ ነው፡፡
ከ400 በላይ ሙዚዬሞችና የኤግዚብሽን አዳራሾች፤ ከ182 በላይ ቲያትር ቤቶች፤ አምስት የሰርከስ አደራሾች፤ ከ16 በላይ ፓርኮች፤ በደን የበለፀጉ ከ118 በላይ የተፈጥሮ ክልሎች  በከተማዋ ዙርያ ገብ ይገኛሉ፡፡
የሞስኮ ከተማ መለያ ከሆኑ ስነህንፃዎች ባሻገር በዋና አደባባዮች፤ በህዝብ መሰብሰቢያ መናሐርያዎች እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተተከሉ እና የቆሙ ሃውልቶች ልዩ መስህብ ያላቸው ገፅታዎቿ ናቸው፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ሃውልቶች በዋናነት በኮሚኒስት ዘመን፤ በዛር የንጉሳዊ አገዛዝ እና ስርዓት፤ በጦርነት ታሪኰች፤  የጦር ጀግኖች እንዲሁም በስነፅሁፍ፤ በጠፈር ምርምርና በሌሎች መስኮች ተምሳሌት በሆኑ ግለሰቦች እና ሁኔታዎች ላይ አተኩረው የተሰሩ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ሞስኮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጦር ጥቃት ድራሻቸው ጠፍተው በመልሶ ግንባታ እንደተሰሩት የበርሊን፤ የፖላንድ ከተሞች አይደለችም፡፡ በተለይ በ1930ዎቹ እና 50ዎቹ ላይ የተሰሩት የከተማዋ ስነ ህንፃዎች እና ሀውልቶች እንደነበሩ መቆየታቸው  ልዩ ውበት አጎናፅፏታል፡፡
በሞስኮ ከተማ ብቻ ከ400 በላይ ካቴድራሎችና ቤተክርስትያናት አሉ፡፡ በክሬምሊን ቤተመንግስት ደጃፍ ላይ የሚገኘው የሴንት ባሰል ካቴድራል  መጠቀስ ያለበት ነው፡፡  ይህ ካቴድራል በየትኛውም አቅጣጫ ሲመለከቱት ተመሳሳይ ውበትና ገፅታ ያለው የላቀ ምህንድስና የሚታይበት ሲሆን፤ የተገነባው ከ1555 እስከ 1561 ባለው ጊዜ ነው፡፡ መታሰቢያነቱም ‹‹ኢቫን ዘቴሬብል›› ተብሎ ለሚጠራው የራሽያ ንጉስ ሲሆን በሌላዋ የራሽያ ግዛት ካዛን በምትገኘው የታታር ከተማ የተሸነፈበትን ጦርነት የሚዘክር እንደሆነ ይገለፃል፡፡ በቀዩ አደባባይ አማካይ ስፍራ የነበረው እና አሁን በሰንት ባስል ካቴድራል ደጃፍ የቆመው የሁለት ፖላንዳዊያን ወራሪ ጦረኞች ሃውልት በኮምኒስት ዘመን ለነበሩ ሰልፎች ባለመመቸቱ ተነቅሎ በዚያ ስፍራ እንዲቆም ተደርጓል፡፡
በሞስኮ ማዕከላዊ ክፍል የሚገኘው የክሬምሊን ቤተ መንግስት የአገሪቱ የፖለቲካ እና የሃይማኖት መሪዎች ዋና መቀመጫ ሆኖ የተመሰረተ ነበር፡፡ በታላቁ የራሽያ ንጉስ  ፒተር  በ1712 የንጉሳዊ ስርዓቱን መቀመጫ በሌላዋ የራሽያ ከተማ ሴንትፒተርስበርግ እንዲሆን ተደርጎም ነበር፡፡ በ1918 እኤአ ላይ የኮሚኒስት መሪዎች የመንግስትን መቀመጫ ከሴንት ፒተርስበርግ አንስተው በክሬምሊን ቤተመንግስት ሞስኮ ላይ መልሰው አድርገውታል፡፡
ከ1839 እስከ 1883 እኤአ ባለው ጊዜ የተገነባው ‹‹ክራይስት ዘ ሴቭዬር›› የመድሃኒያለም  ካቴድራልም በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ተርታ ዋና ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ የፈረንሳዩ ንጉስ ናፖሊዮን የገጠመውን ሽንፈት መታሰቢያ ለማድረግ ተሰርቶ የነበረው ካቴድራሉ  በታዋቂው የሶቭዬት ህብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን የወደመ ነበር፡፡ እንዲወድም የተደረገው ደግሞ በስታሊን ዘመነ መንግስት  315 ሜትር ከፍታ ያለውን የሶቭዬት ሃይሎች ልዩ ቤተመንግስት ለመገንባት እና በደጃፉም 100ሜትር ቁመት ያለውን ግዙፍ የሌኒን ሃውልት ለማቆም በተወጠነ እቅድ ነበር፡፡  በ1931 እኤአ ላይ ስታሊን በእቅዱ መሰረት ጥንታዊውን ካቴድራል እንዲወድም ቢያደርግም የታሰቡትን ቤተመንግስት እና ግዙፉ የሌኒን ሃውልት ሳይሰሩ ቀሩና በምትኩ ለህዝብ  ክፍት የሆነ ግዙፍ የመዋኛ ገንዳ እንዲሰራበት ሆኗል፡፡ በ1995 እኤአ ላይ ግን የመዋኛው ገንዳ ቀርቶ በስፍራው የክራይስት ሴቭዬር ካቴድራልን በድጋሚ እንዲሰራ በወቅቱ የነበሩ የሞስኮ ከተማ ከንቲባ ተወስኖ ከ350 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበት በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ግዙፍ ካቴድረታል በሁለት ዓመት ውስጥ ተገንብቷል፡፡
በሞስኮ ዋና ከተማ ከሚገኙ የመታሰቢያ ሃውልቶች፤ ስነህንፃዎች እና ሌሎች መሰረተልማቶች በሌኒን ስም የተሰየሙት ይበዙ ነበር፡፡ ባለፉት15 እና 20 ዓመታት ግን ከ95  ዓመታት  በፊት  በሞት  ከዚህ ዓለም  በተለየው ሌኒን የተሰየሙ ሆቴሎች፤ ህንፃዎች እና ስታድዬሞች ፋሽኑ አልፎባቸው ስያሜያቸውን እየለወጡ መጥተዋል፡፡ ይሁንና  በራሽያዋ መዲና እንደሌኒን ብዙ ሃውልት ያለው ታላቅ ሰው የለም፡፡ አንዳንድ ኦፊሴላዊ መረጃዎች በሞስኮ ከተማ ብቻ ከ82 በላይ የሌኒን ግዙፍ ሃውልቶች እንዳሉ  ይጠቅሳሉ፡፡ በከተማው የሚገኘው ትልቁ ግዙፍ የሌኒን ሃውልት ከእነቆበት ማማ 37 ሜትር ርዝማኔ ያለውና ዱብና በተባለች የከተማ ማዕከል የቆመው ነው፡፡ በሞስኮ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኘው ቀዩ አደባባይ የሌኒን ሬሳም ይገኛል፡፡ 70 በመቶ ያህሉ ራሽያውያን በአሁኑ ጊዜ የታላቁ መሪያቸው በድን ሬሳ ግባዓተ መሬቱ እንዲፈፀም ይፈልጋሉ፡፡ ግን ይህ ጉዳይ እስካሁን አወዛጋቢ ሆኖ ይገኛል፡፡
ከዓለማችንን ዩኒቨርስቲዎች በግዙፉ ህንፃውና በተማሪው ብዛት የሚጠቀሰው ሎሞኖሶቭ ሞስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ  ከ29 በላይ ፋክልቲዎች፣ 10 የምርምር ተቋማት፤ ከ40ሺ በላይ ተማሪዎች ከ5ሺ በላይ የነፃ ትምህርት እድሎች  በመስጠት የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ በተጨማሪ የዓለማችን ትልቁ ቤተመፅሃፍት  በከተማዋ የሚገኝ ሲሆን ከ17.5 ሚሊዮን በላይ መፅሃፍት ተከማችቶበታል፡፡
                                            ይቀጥላል

Read 5841 times