Saturday, 07 July 2018 10:47

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዳያስፖራው አዲስ የድጋፍ ጥሪ አቀረቡ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(7 votes)


   · ዳያስፖራው ለአገር ግንባታ ከሚያደርገው ድጋፍ አንድ ሳንቲም እንደማይነካ ማረጋገጫ ሰጥተዋል
   · ምክር ቤቱ ለአዲሱ የበጀት ዓመት 346.9 ቢሊዮን ብር አፅድቋል
   · ሜጋ ፕሮጀክቶቹ እስካሁን ከአገር ውስጥ ባንኮች ከ400 ቢ. ብር በላይ ተበድረዋል
   · የተጀመሩትን ሜጋ ፕሮጀክቶች ጨርሶ ወደ ሥራ ለመግባት 7.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል
   · ባለፉት 3 ወራት ብቻ ወደ ውጪ አገር ለመጓዝ ጥያቄ ያቀረቡ 1300 የመንግሥት ኃላፊዎች እንዳይጓዙ ተደርጓል
   · በየቤታቸው ባንክ ገንብተው፣ ብዙ ሚሊዮኖን ገንዘብ ያከማቹ ባለሃቶች እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል
        
    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተለያዩ የዓለም አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የድጋፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ባልተለመደ ሁኔታ ባቀረቡት አዲስ ፕሮፖዛል፤ በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ የውጪ አገራት ኑሮአቸውን እየመሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች፣ አገራቸው አሁን እየተገበረች ያለችውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ፣ ለአገር ግንባታ የሚውል የገንዘብ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ለዚህም ትረስት ፈንድ ተቋቁሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀን 1 ዶላር በማዋጣት፣ የተጀመረውን የለውጥና የዕድገት እንቅስቃሴ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ከዳያስፖራው የሚሰበሰበው ገንዘብ በግልፅና ህዝቡን በቀጥታ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ እንዲውል ይደረጋል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ዲያስፖራው ከሚያዋጣው ከዚህ ገንዘብ ላይ አንዲት ሳንቲም እንደማትነካ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ለምክር ቤቱ ባቀረቧቸው አዳዲስ ፕሮፖዛሎች፤ የአገሪቱ ምሁራን፣ ባለሀብቶችና ወጣቶች ባላቸው ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ አገራቸውን ለመርዳትና የለውጡ አካል ለመሆን መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ በጋራ፣ በአንድነትና በኃላፊነት ስሜት፣ ራሱን ከሌብነትና ከሌሎች ህገ ወጥ ድርጊቶች ነፃ አድርጎ ቢሰራ፣ አገሪቱ በቅርብ አመታት ውስጥ እጅግ አስገራሚ ለውጥ የማታሳይበት ምክንያት አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ለ2011 በጀት ዓመት 346.9 ቢሊዮን ብር በጀት በፀደቀበት በትላንትናው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ ዶ/ር ዐቢይ እንደገለፁት፤ በመጪው በጀት ዓመት የሚጀመሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አይኖሩም፡፡ ባለፉት የበጀት ዓመታት ተጀምረው ከፍፃሜ ሳይደርሱ የቀሩ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ዝርዝር ሁኔታ ጥናት ይደረግበታልም ብለዋል፡፡ በሜጋ ፕሮጀክቶቹ ላይ የሚታየው ችግር፣ መጀመርን እንጂ መጨረስን ግብ ያደረገ አለመሆኑ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩትን ሜጋ ፕሮጀክቶች አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት 7.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ እስከ አሁን ከአገር ውስጥ ባንኮች ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ እንደተበደሩ ጠቁመው፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶችም ካላቸው አጠቃላይ ሀብት የበለጠ ዕዳ ስላለባቸው ይህ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ፣ አዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር ፍትሃዊ አሰራር አይደለም ብለዋል፡፡
የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ያለአግባብ ብክነት እየደረሰበት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፉት 3 ወራት ብቻ ወደተለያዩ አገራት ለመሄድ ተዘጋጅተው የነበሩ 1300 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጉዞ እንዲሰረዝ በማድረግ፣ ወጪዎችን ለመቀነስ መቻሉን በመጥቀስ ይህ አሰራር በቀጣዩ አመትም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ለህገ ወጥ ነጋዴዎች በሰጡት ማሳሰቢያም፤ አገሪቱ አሁን ለገጠማት የውጪ ምንዛሬ እጥረት አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ያሉ ባለሀብቶች፤ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “ዶላራችሁን በብላክ ማርኬት ለመመንዘር ያስቀመጣችሁ ህገ ወጦች፣ ገንዘቡን ቶሎ ካላወጣችሁት ችግር ነው” ብለዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የራሳቸውን ባንክ በየቤታቸው አቋቁመው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስቀምጡ ባለሃብቶች፣ ከድርጊታቸው ታቅበው፣ ወደ ህጋዊው አሰራር የማይመጡ ከሆነ፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ እንደሚወስድም ገልፀዋል፡፡
በጅቡቲ ወደብ ተከማችተው የሚገኙ ከ1.5 ሚሊዮን ቶን በላይ ንብረት በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ባለመቻሉ፣ አገሪቱ በየዕለቱ ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረገች መሆኑን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሀብቶች ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት ካልቻሉ፣ መንግስት ሌሎች አማራጮችን ለመውሰድ ይገደዳል ብለዋል፡፡
አሁን በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን የሠላም፣ የአንድነትና የህብረት ሁኔታ ለማደፍረስ እዚህም እዚያም የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ሙከራዎቹ የትም እንደማያደርሱና የተጀመረውን ለውጥ የሚገታ ኅይል እንደሌለ አስገንዝዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አዳዲስ ባህሪያት እየታዩ መሆናቸውንም ጠቁመው፤ ራሳቸውን አስተካክለው ወደ ትክክለኛው መንገድ ቢገቡ የተሻለ እንደሆነና ማንም ይሁን ማን ከምክር ቤቱ በታች መሆኑን እያሰበ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በምክር ቤቱ ለ2011 በጀት ዓመት ከፀደቀው 346.9 ቢሊዮን ብር ውስጥ 10.96 በመቶ የሚሆነው ለመንግስት ዕዳ ክፍያ የሚውል መሆኑም ታውቋል፡፡     

Read 9147 times