Monday, 28 January 2019 00:00

ቀታሪ ግጥም

Written by  አንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(4 votes)


         “የአንድ ባለቅኔ ግለ ታሪክ ግጥሞቹ ናቸው፤ ሌላ ሌላውማ የግርጌ ማስታወሻ ነው”
           

    [በበዕውቀቱ ስዩም «ዘመን ሲታደስ»]
   ግጥም የጊዜን ቋንጃ መስበሪያ ደንዳና የጥበብ ውጤት ነው፡፡ ከእስትንፋሱ ጋር የተቆራኘ መላ ዓለሙ ነው፤ ለሰው፡፡ ዘመን አብቅሎ፤ ዘመን ያፈራል፡፡ እናም ጣዕሙ ለተፈጥሮ መሞሸሪያ ነው፡፡ የገመናዋ ልክ፤ስፍር፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ገጣሚ በድሉ ዋቅጅራ፤ «ግጥም ተፈጥሮ እራሷን የቆለፈችበትን ቁልፍ  ያስቀመጠችበት ሙዳይ ነው» የሚለን፤ የተለያዮ ባለሙያዎችን ሀሳብ በመጭመቅ፡፡ ለካ በተፈጥሮና በግጥም መካከል ትር(ቀዳዳ) የሚባል ነገር የለም፡፡ ግጥምን ያየ ተፈጥሮን አየ፤ ተፈጥሮን ያየ ግጥምን አየ --- ወደ ሚል ድምዳሜ ይወስደናል፡፡ በርግጥ የግጥም ባህርያት ምንጭ ተፈጥሮ ናት፡፡ ዜማው ከነገሮች ድግግሞሽ ሲቀዳ፣ እምቅነቱ ደግሞ ተፈጥሮ ካቀፈቻቸው ዝቅ ነገሮች ጋር ያመሳስለዋል። ምናባዊነቱን ከተፈጥሮ ምስጢራዊነት ጋር አጋብቸዋለሁ፤ ሁለቱም ጥልቅ ዓለሞች ናቸው፡፡ እንግዲህ ተፈጥሮ የምትሞሸረው በግጥም ከሆነ፣ የጊዜ ብርታት ምኑ ላይ ነው?
ወቅት በግጥም የሚቃኝ ከሆነ፤ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሏል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነዋ በድሉ፤ ተፈጥሮ ቁልፏ ግጥም ነው -- የሚለን፡፡ እንግዲህ ተፈጥሮ በውስጧ መንፈስ የተሸከመች መሆኗ፣ ለስሜትና ለምናብ ቅርበት  እንዲኖራት አድርጓታል፡፡
ይህ ደግሞ በግጥም ይበረበራል፡፡ ይፈተሻል። ይመረመራል፡፡ ጠማማው ይታረቃል፡፡ የጎደለው ይሞላል፡፡ ተፈጥሮ ትሞሸራለች። ትሽቀረቀራለች፡፡ ምናብ፣ ስሜትና አዕምሮ ይቀተራሉ፡፡
[ቀታሪ÷ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ÷እኩል ለመሆን ተከታተለ÷ተቀታተረ÷ተመለካከተ÷ተወዳደረ÷ተተካከለ÷ተመዛዘነ÷ተፈካከረ÷ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር፡፡ ( ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷የዐማርኛ መዝገበ ቃላት÷ገፅ ፫ ፻ ፹ ፬÷2008 ዓ.ም) ግጥም ምንጬ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብን እና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል።) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ፣ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው፡፡ መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው። ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል። ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም፡፡ አይታኘክም - የተመጠጠ ነውና፡፡]
ቁጥር፡-3
 * * *                                                                                             
                  ዘመን ሲታደስ
        እኛኮ ለዘመን
        ክንፎቹ አይደለንም
        ሰንኮፍ ነን ለገላው
        በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው
   (በዕውቀቱ ስዩም፣ ኗሪ አልባ ጎጆዎች፣ገፅ12፣ 1995 ዓ.ም)
«...ግጥም  የህያው ስሜቶች ምስክርነት እንደሆነ እናምናለን...» ይላል -- እራሱ በዕውቀቱ፡፡
የሰው ልጅ ዘላለማዊ ህልውናውን የሚተክልበት ብርቱ በትር ነው -- እንደ ማለት፡፡ «ዘመን ሲታደስ» የጊዜን ግስጋሴ፣ የነገሮችን ምትሀታዊ ለውጥ፣ የታሪክ ባለቤትነትን ድርሻ (ኢትዮጵያን ልብ ይሉአል)፣ የሰውን ንቃተ ህሊና ማዕበል፣የኔነትን ቦታ ከታሪክ ውስጥ ማሰስን ይወክላል፤ መለየት፡፡ በጊዜ መርከብ ያጓጉዘናል። «እኛኮ ለዘመን...» የሚለው  ሀረግ ጠቋሚ ነው፤ እኛ ለዘመን ሳይሆን ዘመን ለእኛ ያለው ቦታ  ምን እንደሆነ የሚያሳይ፡፡ ክንፎቹ አይደለንም -- በማለት የእኛ ህልው መሆን ትርጉሙ ቀሊል መሆኑን ይነግረናል፡፡ ጊዜና ውጤት ተቆራኝተዋል (መስፈሪያና ስፍሩ)፡፡ ሀይሉን ለዘመን ይሰጣል፡፡ ግጥሙ ጊዜን የሁሉም ነገር ምንጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በርግጥ ስለ ጊዜ ብዙ ተብሏል፡፡ በተለያየ ምልከታ፡፡ ለምሳሌ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ፤ «ጊዜ በረርክ በረርክ» ግጥሙ ላይ:-  ጊዜ በረርክ በረርክ /ጊዜ በረርክ በረርክ/ግና ምን አተረፍክ/ግና ምን አጎደልክ?/ሞትን አላሸነፍክ/ህይወትን አልገደልክ  በማለት ጊዜን የህይወትና የሞት እስረኛ በማድረግ ከንቱ፣አቅመ ቢስ ያደርገዋል፡፡ ከሞትና ከህይወት የበላይነት ባሻገር የመኖሩን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ በርግጥም የጊዜ ሀይል ደብዝዞ ብቻም ሳይሆን ተነጥሎ፤ በባይተዋር ህልው መልኩ ለመቆም ሲንገታገት ይታየናል፡፡ ግጥሙ እዚህ ዓለም ላይ ሦስት ትላልቅ ጉዳዮች እንዳሉ ይነግረናል፡፡ ሞትና ህይወት ባላንጣዎች ሲሆኑ ለሁለቱም ጊዜ መርከባቸው ይመስላል፡፡ እንደ ፈለጉ የሚዘውሩት፡፡ ይህ ምልከታ ህሊናን ከጊዜ እስረኝነት ነፃ ያወጣዋል፡፡ እፎይታ ይሰጠዋል፡፡ ሞትንም ከጊዜ ውጭ ያደርገዋል፡፡ ደበበ፤  ለሰው ልጅ ትልቁ ባላንጣ ሞት መሆኑን ይጠቁመናል። ግብግቡ በህይወትና በሞት መካከል የሚደረግ መሆኑን ያበስረናል፡፡ ምናልባትም ጊዜ የኛ ምልከታ እንጂ በራሱ ህልው አይደለም ያለ ይመስለኛል፡፡ ደበበ፤ በጊዜ ላይ ህይወትን አሰለጠነ፤ አበረታ፡፡ ሰውንም ከጊዜ እስረኝነት አላቀቀው፡፡ እራሱን አስችሎ አቆመው፡፡ የሁሉም ነገር ምንጭ አደረገው፡፡ ነፃ አወጣው፡፡ ጊዜን ባይተዋር በማድረግ፡፡ ነገር ግን ደበበ፤ ሊሸሸው ያልቻለው ሀቅ ከፊቱ ተጋፈጠው -- ሞት፡፡
የህይወት ብቸኛ ተገዳዳሪ፡፡ የሞትን ሀይል ባዶ ለማድረግ ሲል ጊዜን ባይተዋር አደረገው። ሞትን በሬሳ እንደ መደለል ---አይነት፡፡ ገበረለት፤ ለህይወት ካለው ስስ ስሜት የተነሳ፡፡
በ»ዘመን ሲታደስ» ግጥም ሁሉም ነገር በሂደት የሚሸሽ፣ የሚገረሰስ መሆኑን አስረግጦ ይነግረናል ---ተራኪው፡፡ የህይወት ትር ትር ማለት ከሰንኮፍ ጋር በንፅፅር የቀረበ ይመስለኛል። ሰንኮፍ ነን ለገላው ---በሚል፡፡ ዘይቤያዊ አገላለፅ ነው --አያዎ፡፡ ዘመን ሰንኮፍ አለው እንዴ ? ኦ... ለካ ሰው ነው፡፡ ኦ...ለካ ታሪክ ነው፡፡ ይገርማል-- ያላወቁ ÷አለቁ -- አሉ፡፡ የኢትዮጵያ የታሪክ ቦታ እያደር መደብዘዙ አሳስቦታል --- ተራኪውን፡፡ ህመሙንም --በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው -- በማለት ያጋራናል፡፡ በርግጥ ይህ ስንኝ በርካታ ሀሳቦችን የተሸከመ ነው፡፡ የትውልድ ቅብብሎሹን (መተካካት) እንደ ዘበት ሹክ ብሎን ያልፋል፡፡ በሂደት በሰመመን ተጉዘን የምናሸልብ መሆናችንን ይጠቁመናል፤ ለዚህ ዓለም የማናስፈልግበት ጊዜ ሲመጣ፡፡ ያለ ዘዴ ÷ጋሻ እንቅብ ነው -- ያለ ይመስለኛል፤ ዘመን። ያው የህይወት ሀቅ ነው፡፡ ይቀትራል፡፡ የከረረ ስሜት ነው፡፡ ግጥሙ ሰውን ደካማ አድርጎ የሳለ ነው፤ አቅመ ቢስ፡፡ የጊዜን ጡንቻ ያበረታል፡፡ ህልውናውን ሲያድስ ሰንኮፉ ያደርገናል፡፡ እሱ ይሞሸራል እኛ እንቆሽሻለን፡፡ ለዚህ ይሆን ገጣሚ ከበደ ሚካኤል፤በ»ብርሃነ ሕሊና» የግጥም ስብስብ:-
ገና፡ነው፡እያሉ፡ካልሸፋፈኑት፡
እንደምን፡ያዩታል፡ሞትን፡ፊት፡ለፊት፡፡--የሚለው፡፡ ይገርማል በዕውቀቱ፤ ከታሪክ ምልከታው ባሻገር እኛን (የቁልቁለት ታሪክ ባለቤቶችን) ደካማ ሲያደርገን ፣ የጊዜ ባሪያ አድርጎ ነው፡፡ ደበበ፤ (አፈሩን ያቅልለት) ደግሞ ሀያል ያደርገናል (ሁላችንን የሰው ልጆች)፤ የሁሉም ነገር ምንጭ በማድረግ  በጊዜ ላይ ያሰለጥነናል፡፡ «የአንድ ባለቅኔ ግለ ታሪክ ግጥሞቹ ናቸው፤ሌላ ሌላውማ የግርጌ ማስታወሻ ነው» ይላል - Yevtushenko. የኛዎቹ ገጣሚዎች፤ በአንድ ሰብአዊ ጉዳይ ይሄን ያህል በስሜት ተራርቀዋል፡፡
  «ዘመን ሲታደስ» ዜማዊ ግጥም ሲሆን ስሜት ንክር ነው --ያቃስታል፡፡ ያሽሟጥጣል። ይጋልባል፡፡ ጣቱን ይቀስራል (ከገናናዎቹ አያቶቻችን ውጭ ያለነውን)፡፡ ይቀትራል፡፡
ቀለሙ የተስተካከለ በመሆኑ ምጣኔው ውብ ነው፡፡ ምቱ በሀረግ ደረጃም ጭምር የተዋቀረ በመሆኑ ሙዚቃው የልብ ምግብ ነው፡፡ የተሸከመው ሀሳብ የትየለሌ በመሆኑ እንቡጥ አመልማሎ ነው --- እያደር ይፈካል፡፡ ግጥሙ ከስርዓተ-ነጥብ የመከነ ነው፤ስሜቱ ይዋልላል፡፡ በርግጥ በግጥሙ የሀገራችን ወደ ኋላ መቅረት ታሪካዊ አንድምታው ተተርጉሞበታል፡፡ ሀቅ ነውና ትውልዱ አደራውን መውሰድ  ይገባዋል።
(ይህ ፅሁፍ የዕዝራ አብደላ ማስታወሻ ይሁንልኝ)
***
ከአዘጋጁ፡ ጸሃፊውን በኢ ሜይል አድራሻው፡-   This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1494 times