ዘጋርደያን ከሁለቱ ራፕሮች ማን ይበልጣል በሚል ከአንባቢዎቹ ድምፅ አሰባስቦ በሰራው ዘገባ ጄይዚ በ54 በመቶ ድምጽ 46 በመቶ ያስመዘገበውን ካናዬ ዌስት መብለጡን ሲያትት ካናዬ ዌስት ከራፕርነት ይልቅ ምርጥ የፊልም ፕሮዲውሰር መሆኑን ገልፆ የራፕሮች ንጉስ ያለጥርጥር ጄይ ዚ ነው በሚል ደምድሟል፡፡ከዓመት በፊት ለገበያ የበቃው የጄይ ዚ እና የካናዬ የጋራ አልበም ‹ዎች ዘ ትሮን› በሰሜን አሜሪካ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ቅጂ የተሸጠ ሲሆን በመላው ዓለም በነበረው ገበያ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደተገኘበት ይገለፃል፡፡
እሰከ 2015 እኤአ ያለው ሃብት 1 ቢሊዮን በመድረስ የመጀመርያው ጥቁር አሜሪካዊ ራፕር ሊሆን እንደሚበቃ የተተነበየለት ጄይዚ አምና ፎርብስ ባወጣው የራፕሮች ሃብት ደረጃ ባስገባው 37 ሚሊዮን ዶላር መሪ ነው፡፡ ካናዬ ዌስት በበኩሉ 35 ሚሊዮን ዶላር ካስመዘገበው ፒ ዲዲ ቀጥሎ በ16 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢው ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሙዚቃ ሙያው 23 ዓመታትን ያስቆጠረው የ42 ዓመቱ ጄይዚ 11 አልበሞችን የሰራና በመላው አለም 50 ሚሊዮን ቅጂ የሸጠ ራፕር ሲሆን 14 የግራሚ ሽልማቶችን የሰበሰበ ነው፡፡ የ34 ዓመቱ ካናዬ ዌስት በበኩሉ በሙያው 16 ዓመታትን ሲያሳልፍ 6 አልበሞች ከመስራቱ ም በላይ በዲጅታል ገበያ በአሜሪካ ብቻ 30 ሚሊዮን ዘፈኖችን የሸጠና 18 የግራሚ ሽልማቶችን በመሰብሰብ በሽልማቱ ታሪክ ከፍተኛውን ክብር ያገኘ ነው፡፡