Saturday, 23 March 2019 14:54

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል- ፲፭ ለመዘመን መቅዳት ያለብን ‹‹ህሊናን›› ወይስ ‹‹የህሊናን ትሩፋት››?
                                         
           ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የሰው ልጅ ህይወት ሁለት መንገዶች አሉት - አንድም የመንፈስ፣ ሌላም የህሊና›› ይላሉ (2003፡ 64)። ከእነዚህ ሁለት መንገዶች ውስጥም ሁለት ዓይነት ‹‹እውነቶች›› ይመነጫሉ፤ ከህሊና መንገድ ‹‹አመክኖያዊ እውነት›› (Rational Truth) ሲመነጭ፣ ከመንፈስ መንገድ ደግሞ ‹‹ሚስጢራዊ እውነት›› (Mystical Truth) ይመነጫል፡፡ ዘመናዊ ማህበረሰብ የመጣው የሰው ልጅ የህይወት መንገዱን ከመንፈስ ወደ ህሊና፣ የእውነት ምንጩን ደግሞ ከሚስጢራዊነት (ከተአምራዊነት) ወደ አመክኖያዊ እውነት ሲቀይር ነው፡፡
ከዚህ መነሻ ሐሳብ በመንደርደር፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ማዘመን ማለት የኢትዮጵያውያንን ማህበረሰባዊ የመደራጃ መርህን ከ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› ወደ ‹‹አመክኖያዊ እውነት›› ማዘዋወር፣ የሥልጣን ምንጫቸውንም ከመንፈስ ወደ ህሊና መንገድ ማሸጋገር ማለት እንደሆነ በክፍል-14 ፅሁፌ ላይ ተመልክተናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ የሀገራችንን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ክሽፈት በተመለከተ እስከ ዛሬ ድረስ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ አንፃር ሲደረጉ ከነበሩ ጥናቶች ወጣ በማለት፣ የፕሮጀክቶቹን ክሽፈት በሌላ መንገድ ‹‹ከተአምራዊነትና ከብህትውና ባህል›› አንፃር የምናይበት አዲስ መነፅር በመጠቀም፣ የአፄ ቴዎድሮስንና የአፄ ምኒሊክን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶችን መፈተሽ መጀመራችን ይታወሳል፡፡ ዛሬም በዚሁ በአዲሱ መነፅር ይሄንኑ ፍተሻችንን እንቀጥላለን፡፡
የአውሮፓ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በህሊና መንገድ ከአመክኖያዊ እውነት ተቀይሮ የመጣ ነው - የህሊና ትሩፋት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ትክክለኛው የዘመናዊነት ፕሮጀክት የአውሮፓን ህሊና (ምንጩን) መቅዳት እንጂ የህሊና ትሩፋታቸውን (ቴክኖሎጂያቸውን) መቅዳት አይደለም፡፡ ይሄንን ደግሞ የአፄ ምኒሊክ ልዑካን ቡድን፣ የእንግሊዙን ንጉስ ጆርጅ 5ኛ የንግስና በዓል ለማክበር በ1903 ዓ.ም ወደ ለንደን በሄዱበት ወቅት በአስጎብኛቸው በኩል ተነግሯቸዋል፣
‹‹…ከዚያም በለንደን የሚገኘውን አንድ የመኪና ማምረቻ ጎበኘን፡፡ የልዑካችን መሪ የሆኑት ደጃዝማች ካሳም የተወሰኑ መኪኖችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ይችሉ እንደሆኑ ጠየቁ። አስጎብኛችን ካፒቴን ተሲንጀር ግን መኪኖቹን ማዘዝ ቀላል እንደሆነ ተናግረው፣ ‹‹ሆኖም ግን፣ ቢበላሹ እንዲጠግኑላችሁ መኪኖቹን ከመግዛታችሁ በፊት በመጀመሪያ ወጣቶቻችሁን የቴክኒክ ትምህርት ማስተማር አለባችሁ›› የሚል ምክር ስለሰጧቸው ደጃዝማች ካሳ ሐሳባቸውን አነሱ (ኅሩይ 2009፡ 164)፡፡››
በአስጎብኚው አስተያየት መሰረት፣ ትክክለኛው የዘመናዊነት ፕሮጀክት የህሊናን ትሩፋት (ቴክኖሎጂን) መቅዳት ሳይሆን፣ ራሱ ህሊናን (የማህበረሰብ ማደራጃ መርህን) መቅዳት ነው፡፡ በደጃዝማች ካሳ እሳቤ ውስጥ ግን ኢትዮጵያን ለማዘመን የአውሮፓን ህሊና (Rationality) ከመቅዳት ይልቅ የህሊናቸውን ትሩፋት ወደ ሀገር ቤት ማስገባት የተሻለው አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒሊክም ሲያደርጉ የነበረው ተመሳሳይ ነገር ነው - የአውሮፓን ህሊና ከመቅዳት ይልቅ የህሊና ትሩፋታቸውን መቅዳት፡፡ ይሄ ነበር የነገስታቱ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ገና ከመነሻው የፈፀመው ስህተት፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ በተደጋጋሚ በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ የንጉሱ ዋነኛ ትኩረት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ቴክኖሎጂን በሀገር ቤት ማምረት እንጂ፣ አውሮፓውያንን ለታላላቅ ቴክኖሎጂዎች ያበቃቸውን የህሊና መንገድ መቅዳት አልነበረም፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም። አፄ ቴዎድሮስ፣ የአውሮፓን የህሊና ትሩፋት (ቴክኖሎጂን) በሀገር ውስጥ ለማምረት የሞከሩት በኢትዮጵያ ለዘመናት የተነጠፈውን የብህትውናና የተአምራዊነት የባህል መሰረት ሳይነኩ ነው፡፡
በሀገራችን ለ1500 ዓመታት በቆየው በያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ የኢትዮጵያውያን የእውነት ምንጭና የህብረተሰብ የማደራጃ መርህ የሆነው ብህትውናና ተአምራዊነት ሳይጠየቅና ሳይፈተሽ ነው የኖረው፡፡ ይሄንን ፍተሻ በ17ኛው ክ/ዘመን በጣም ለአጭር ጊዜ ያደረጉት ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ናቸው። ከዚህ አንፃር፣ ስለ ህሊና መንገድ አስፈላጊነት በመጀመሪያ የፃፈውና የኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ የማደራጃ መርሁም ‹‹ከሚስጢራዊ እውነት›› ወደ ‹‹አመክንዮአዊ እውነት›› እንዲቀየር ከሁሉ አስቀድሞ ሲከራከር የነበረው ዘርዓያዕቆብ ነው፡፡ የህሊናን መንገድ ለሚከተል ‹‹ተመራማሪ ሰው ግን እውነት (አመክኖያዊ እውነት) ፈጥና ትገለጣለች›› ይላል ዘርዓያዕቆብ፣ በሐተታው ምዕራፍ አምስት ላይ፡፡
ከላይ ከላይ ስናየው ቴክኖሎጂ የቁስ አካል ስብስብ ይመስለናል፡፡ ሆኖም ግን፣ አይደለም። ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ ህሊናን (Rationality) ተሸክሟል፡፡ በግዥና በሽያጭ ወቅትም ይሄ ህሊናና የኑሮ ዘይቤው አብሮት ይጓዛል፤ ልክ አንድ የጀርመን የኤሌክትሮኒክስ የሽያጭ ባለሙያ ‹‹We sell lifestyles, not appliances›› እንዳለው፡፡ እናም ቴክኖሎጂ በዲዛይኑም ሆነ በአገልግሎቱ የአመክንዮን ህግ ያስተዋውቃል፡፡ ይሄም የሚያመላክተን ቴክኖሎጂ የሚመነጨው የህሊናን መንገድ በሚከተሉና አመክኖያዊ እውነትን እንደ ማህበረሰብ ማደራጃ መርህ በሚጠቀሙ ህዝቦች ውስጥ መሆኑን ነው፡፡
ለዚህም ነው ‹‹የአፄ ቴዎድሮስም ሆነ የአፄ ምኒሊክ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ቴክኖሎጂን ከማስመጣቱ በፊት የዘርዓያዕቆብ ዓይነት ፈላስፎችን በመጠቀም፣ በመጀመሪያ ህዝቡን የህሊናን መንገድ ማለማመድ ያስፈልግ ነበር›› የምለው፡፡ እነዚህ ነገስታት ቴክኖሎጂን የቁስ አካል ስብስብ አድርገው ስለሚያዩት፣ ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ የሚመጣውን የህሊና ባህልና አስተሳሰብ ሊረዱት አልቻሉም። ነገስታቱ ቴክኖሎጂን ሲያስመጡ፣ እነሱ ባይረዱትም ሲያስመጡ የነበረው የብረት ቁሳቁስ ሳይሆን የአውሮፓን ህሊና ነበር። እናም የአውሮፓን ህሊና አስመጥተው በኢትዮጵያውያን የመንፈስ (የተአምራዊነትና የብህትውና) መንገድ ላይ አስቀመጡት፡፡ ይሄ ነበር የነገስታቱን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ያጋጠመው ዋነኛ ተግዳሮት!!
በተለይ በአፄ ምኒሊክ ዘመን በርካታ የቴክኖሎጂ ዓይነቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል። ከቴክኖሎጂዎቹ ጋርም የምዕራቡ ዓለም ህሊናና የህይወት ዘይቤ አብሮ ገብቷል። ይሄም ያሬዳዊው ሥልጣኔ ለዘመናት ከተጠቀመበት የብህትውናና የተአምራዊነት እሳቤ ጋር በተቃርኖ የሚቆም ነው፡፡
ለመሆኑ በ19ኛውና በ20ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ለነበሩ ለእነዚያ ኢትዮጵያውያን፣ ቴክኖሎጂ አዲስ ክስተት ስለነበረ ግብረ መልሳቸው ምንድን ነበረ? ሰዎች ለአዳዲስ ክስተቶች መልስ የሚሰጡበትን የአእምሮ መዋቅር የሚያዘጋጅላቸው ባህላቸው ነው፡፡ ባህላቸው ከፈጠረላቸው የአስተሳሰብ መዋቅር በመነሳት ለአዳዲስ ክስተቶች የራሳቸውን ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ የብህትውናና የተአምራዊነት ባህል ላይ የተመሰረቱ ህዝቦችም ለማንኛውም አዲስ ክስተት ‹‹የተአምራዊነት›› ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ነው አፄ ምኒሊክ ሀገር ለማዘመን ያደረጉትን ጥረት ሁሉ ህዝቡ ‹‹የሰይጣን ሥራ ነው›› እያለ ለመቀበል ሲቸገር የነበረው፡፡ የምዕራባውያን የህሊና ትሩፋት የሆነው ቴክኖሎጂ በአገልግሎቱም ሆነ በአሰራሩ ከኢትዮጵያውያን ተአምራዊ የአስተሳሰብ መዋቅር (Mystic thought structure) ጋር በፍፁም ሊጣጣም አልቻለም፡፡ ‹‹ተአምራዊው ዓለም›› የማይተነበይና እንዴት እንደሚሰራም መርሁ የማይታወቅ ነው፤ በዚህም የተነሳ ኑሯቸው ሁሉ በተአምራዊነት ታሪኮች የተሞላ ነው፡፡
በተቃራኒው፣ አፄ ምኒሊክ ያስገቧቸው ቴክኖሎጂዎች ግን የሚተነበዩ፣ በሰው ቁጥጥር ስር ያሉና እንዴት እንደሚሰሩም የሚታወቁ ናቸው። በዚህም የተነሳ፣ ቴክኖሎጂዎቹ የሚሰሩበት አመክኖያዊ መርህ ተአምራዊው የአስተሳሰብ መዋቅር ከሚረዳው ነገር ውጭ ነው፡፡ ለዚህም ነው ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ ‹‹የሀገራችን ሰው ተአምራዊ ትረካን እንጂ (አመክኖያዊ) እውነትን ለመስማት አይወድም፤ ቢሰማም አይረዳውም›› (2002፡ 5) ያለው፡፡ ከዚህም የምንረዳው ነገር ቢኖር፣ የተአምራዊነትና የብህትውና ባህላችን ለአመክኖያዊ እውነት ባዕድ እንድንሆንና ‹‹ተአምራዊ እውነትን ብቻ›› እንድንቀበል አድርጎ እንደቀረፀን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን በኢሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1185 times