Sunday, 02 June 2019 00:00

የረድኤት ድርጅቶች ከ8 ወራት በኋላ ተፈናቃዮችን ማግኘት ችለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  በምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት 6 ሰዎች ተገደሉ

              በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢ ባለፈው ረቡዕ በታጣቂ ቡድኖች በደረሰ የቦንብ ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸው የተገለፀ ሲሆን በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊቱ እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማየሉን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ተቋም አስታውቋል፡፡
ባለፉት 8 ወራት በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋትና የመንገድ መዘጋት ሳቢያ ተፈናቃዮችን ማግኘት እንዳልቻለ የጠቆመው ተቋሙ፤ ከባለፈው ሣምንት አጋማሽ ጀምሮ ከተፈናቃዮች ጋር መገናኘት እንደቻለና ያሉበትን ሁኔታ እያጠና መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአካባቢው የተፈጠረውን አንፃራዊ መረጋጋት ተከትሎ ወደ ካማሺ ዞን ያቀኑት የድርጅቱ ኤክስፐርቶች በዋናነት የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉምዝ አዋሳኝ ወረዳዎች የሆኑት፡- ሴዳል፣ ያሶ፣ ጌልምቲና ከማሺ ከተማ ተፈናቃዮች በብዛት የሚገኙባቸው መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ ባለፉት 8 ወራት በቂ ምግብና እርዳታ ያላገኙት ተፈናቃዮቹ፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ መመልከቱንና አስቸኳይ የህክምናና አልሚ ምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግም ገልጿል - ተቋሙ፡፡
ይህ እንዲህ እንዳለ በምዕራብ ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ሀይሎች በመከላከያ ሠራዊት እርምጃ ከተወሰደባቸው በኋላ በአካባቢው አንፃራዊ መረጋጋት መፈጠሩን ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገባው ቢቢሲ፤ ባለፈው ረቡዕ ግን በደፈጣ ተዋጊ ታጣቂ ሃይሎች በተፈፀመ የቦንብ ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል፡፡
ቢቢሲ የቄለም ወለጋ ዞን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሃምዛ አብዱልቃድርን ዋቢ አድርጐ ባቀረበው ዘገባ የደፈጣ ታዋጊ ታጣቂ ቡድኖቹ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የወረወሩት ቦንብ ፈንድቶ በአካባቢው የሚገኙ ስድስት ሰዎች መገደላቸው አመልክቷል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው የአፀፋ እርምጃ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኦነግ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመጨረሻውን በሠላም የመታገያ ስምምነትን መፈፀማቸውን ተከትሎ፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጦር መሪ የሆኑት ጃል መሮ “እኛ ትግላችንን እንቀጥላለን” ሲሉ አቋማቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡

Read 2825 times