Saturday, 03 August 2019 13:49

የችግኝ ተከላ በታሪካዊቷ አንጎለላ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)


                 ‹‹የባህር ዛፍ ችግኝን በየደጅህና በየእርሻ ሥፍራህ ሁሉ የተከልክ ወገኔ፤ ያለብህን የግብር ዕዳ ምሬሃለሁ›› - አፄ ምኒልክ
                     
      በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተደረገው ጥሪ ሕዝቡ አስገራሚ ምለሽ በሰጠበት የሐምሌ 22ቱ የአረንጓዴ አሻራ ቀን፣ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከልም ‹‹ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ›› አንዱ ነው፡፡
የዚህ ድርጅት ሰራተኞች ለችግኝ ተከላው ፕሮግራም የተንቀሳቀሱት ወደ ታሪካዊቷ አንጎለላ ከተማ ነበር፡፡ ማልደው ወደ ሥፍራው የተጓዙት የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ከአንጎለላ ከተማ አስተዳደርና ከነዋሪው ሕዝብ ጋር በመሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች ችግኝ ሲተክሉ ውለዋል፡፡
በድርጅቱ የሪግሪኒንግ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ አስፋው ማርያሜ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገው አገራዊ ጥሪና የሕዝቡ አስገራሚ ምላሽ፣ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሀብታችንን ወደነበረበት ለመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
የአንጎለላና ጠዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዮርዳኖስ ተከስተ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ ለተደረገው አገራዊ ጥሪ እየሰጠ ያለው ምላሽ እጅግ አስገራሚ መሆኑን ጠቁመው፤ በአንጎለላና ጠዳ ወረዳ ውስጥ በ2011 ዓ.ም 17 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ፣ ከ16 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን በመትከል ዕቅዳችንን ከጊዜው በፊት የምናሳካ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ ‹‹ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ›› ይህንኑ አገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ወደ ወረዳቸው በመምጣት፣ በችግኝ ተከላ ስራው ላሳየው ወገናዊ ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል አስተዳዳሪው፡፡
አንጎለላ ወረዳ፤ ‹‹የባህር ዛፍ ችግኝን በየደጅህና በየእርሻ ሥፍራህ ሁሉ የተከልክ ወገኔ፤ ያለብህን የግብር ዕዳ ምሬሃለሁ›› በማለት ሕብረተሰቡ የዛፍ ችግኝ እንዲተክል ያበረታቱት የታላቁ ኢትዮጵያዊ ንጉስ አፄ ምኒልክ የትውልድ ስፍራ ነው፡፡ ‹‹ዎርልድ ቪዥን›› በአገራችን ለበርካታ ዓመታት ሲያከናውን የቆየውን የተተራቆቱ ደኖችን የመመለስና የመጠበቅ ተግባር፤ በዚህች በታሪካዊቷ ከተማ ላይ ማከናወኑ እጅግ ያስመሰግነዋል ብለዋል… የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዮርዳኖስ ተከስተ፡፡

Read 1449 times