Saturday, 03 August 2019 13:52

የቤንሻንጉል ም/ቤት የአመራሮች ሹም ሽር አደረገ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

 የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ባካሄደው የም/ቤት ስብሰባ የአምስት አመራሮችን ሹምሽር አድርጓል፡፡
ም/ቤቱ ባለፈው ሐሙስ ባጠናቀቀው ስብሰባው የተለያዩ ችግሮችን የገመገመ ሲሆን፤ በተለይ በክልሉ የሠላም ሁኔታና የፍትህ አሠጣጥ ድክመት ላይ በጥልቀት ውይይት ማድረጉን የክልሉ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አዲጐ ሀምሳያ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ አመት ክልሉ ከፀረ ሠላም ሀይሎች ተጠብቆ፣ የተረጋጋና ሠላም የሠፈነበት ክልል እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ም/ቤቱ መወሰኑን ም/ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ የሚያነሳውን የፍትህ ስርአት መዳከምና አፋጣኝ ፍትህ ካለማግኘት ችግር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት፣ የክልሉን የፍ/ቤት ፕሬዚዳንቶች ማንሳቱን የተናገሩት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ከፍ/ቤት ዳኞቹ በተጨማሪ የገቢዎች ባለስልጣን፣ የውሃ ቢሮ፣ የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊዎችም በአዳዲስ አመራሮች መተካታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በመተክል ዞን የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት፤ የአካባቢውን ሠላም በአስተማማኝ ሁኔታ መቆጣጠሩን ገልፀው፤ በአማራና በኦሮምያ ክልል ወሰን አካባቢ በተፈጠሩ ችግሮች ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ በጀት በመመደብ በክልሉ የሚስተዋሉ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን የገለፁት አቶ አዲጐ፤ ከስራ አጥ ወጣቶች ጋር በተያያዘ ክልሉ ለቀጣይ አመት በርካታ ስራዎችን ለመስራት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡


Read 10410 times