Tuesday, 01 October 2019 10:05

ለሲዳማ ህዝበ ውሣኔ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ለሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሣኔ የምርጫ ምልክቶች ይፋ ሆኑ

            የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ለህዝበ ውሣኔው በቂ ዝግጅት እንዲደረግ ያሳሰበ ሲሆን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የምርጫ ምልክትን ይፋ አድርጓል፡፡
ከሰሞኑ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከደቡብ ክልልና ከሲዳማ ዞን አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትና ኮሚሽን፤ ሕዝበ ውሳኔው ህዳር 3 ቀን ከመካሄዱ በፊት በቂ ቅድመ ዝግጅት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
በሕዝበ ውሳኔው አካሄድ ላይ ሕብረተሰቡን በቀጥታ ማወያየት፣ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ጥርት ያለ የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጥ በትኩረት ሊከናወኑ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ አስገንዝቧል፡፡
ቀደም ብሎ ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ቀውስ ምክንያቱ በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚገባቸው አካላት ወቅታዊና ስልታዊ የሆነ ምላሽ አለመስጠታቸው በአንድ ጎን፣ በሌላ ጎን ደግሞ የቀረበውን የክልልነት ጥያቄ በማናቸውም መንገድ እስከ መጨረሻው ከዳር እናደርሳለን በሚል የሚያራምዱ ቡድኖች እንደሆኑ መረዳቱን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አሁንም ከህዳር 3 ሕዝበ ውሳኔ በፊት ሁሉም አካላት የተስማሙበት መርሃ ግብርና የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡  
ለህዝበ ውሣኔው ሁለት አማራጮች መቅረባቸውን የገለፀው ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ አማራጮቹም በጐጆ ቤትና በሲዳማ ባህላዊ ቁስ “ሻፌታ” እንዲወከሉ ወስኗል፡፡
ከደቡብ ክልልና ከሲዳማ ዞን ምክር ቤቶች ጋር በተደረገ ምክክር “ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የጐጆ ቤት እንዲሁም “ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የሻፌታ ምልክት ሆኖ ለህዝበ ውሣኔው ድምጽ መስጫ እንዲያገለግል መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ቦርዱ ከህዝበ ውሣኔው አስቀድሞ እስከ መስከረም 22 ቀን የሃዋሣ ከተማ እጣ ፈንታን አስመልክቶ የክልሉ ም/ቤትና የሲዳማ ዞን ወስነው በህግ ጉዳዩን አስረው ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡለት ማሳሰቡም ይታወቃል፡፡

Read 6526 times