Saturday, 12 October 2019 12:27

ነፍሱን ለሙዚቃ የሰጠው ኤልያስ መልካ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  በአገራችን የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በድንገት ተከስተው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሙዚቃ አብዮት በማቀጣጠል ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን በብዛትም ሆነ በጥራት ለማበርከት ከታደሉ ጥቂት የጥበብ ፈርጦች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል - የሙዚቃ ባለሙያው ኤልያስ መልካ፡፡ በጥበብ ሙያ ውስጥ አድጎና ኖሮ፣ ሕይወቱን  ለጥበብ አሳልፎ የሰጠ ድንቅ ሙዚቀኛ  ነበር፡፡
እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ፣ ሰባተኛ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ኤልያስ መልካ፤ ከሙዚቃ ሙያ በተለይም ከጊታር ጋር በፍቅር የወደቀው ገና በማለዳ ዕድሜው ነበር:: የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑት ቤተሰቦቹ፣ ከሌሎች የሃይማኖቱ ተከታዮች ጋር እየተሰባሰቡ፣ ዝማሬና ምስጋና የሚያቀርቡበትን ፕሮግራም በየሳምንቱ ያካሂዱ ነበር - ብዙውን ጊዜ ደግሞ በእነ ኤልያስ ቤት:: መንፈሳዊ የኪ-ቦርድና የጊታር ተጫዋቾችም ከቤታቸው አይጠፉም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለእምቦቀቅላው ኤልያስ፣ መልካም አጋጣሚን ፈጠረለት፡፡ ከእነዚህ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች እግር ስር ቁጭ ብሎ የሚሰሩትን ሁሉ በጥሞና እያስተዋለ እንዲያድግ አደረገው፡፡  
ታዳጊው ኤልያስ በልጅነት ዕድሜው በፍቅር የወደቀላትን ሙዚቃ የመማር እድል ያገኘው የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ነበር:: ተፈጥሮ የቸረችውን የጥበብ ፀጋ በትምህርት ለማበልጸግና በሰፊው የሙዚቃ ባህር ውስጥ ጠልቆ ለመጠመቅ፣ ብቸኛውንና አንጋፋውን ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ተቀላቀለ፡፡ ከአራት ዓመታት ትምህርት በኋላ በጥሩ ውጤት የተመረቀው ኤልያስ፤ በአገሪቱ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መትጋቱን ተያያዘው፡፡   
አርቲስት ኤልያስ መልካ በባንድ ታቅፎ መጫወት የጀመረው በፅዮን መንፈሳዊ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ነበር፡፡ ከዚያም መዲና የሙዚቃ ባንድ፣ ላስታስ ባንድና አፍሮ ሳውንድ በተሰኙ የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ሰርቷል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃ የማቀናበር አቅሙን የተፈተነው ደግሞ በትዝታው ንጉስ ማህሙድ አህመድ ‹‹ሁሉም ይስማው››  የተሰኘ አልበም ሲሆን በዚህ ሥራ ድምፃዊውም ሆነ ኤልያስ ተወዳጅነትን ተቀዳጅተዋል፡፡
የኤልያስ መልካ የሙዚቃ ጥበብና የቅንብር ችሎታ ይበልጥ የተለካበትና ከፍተኛ እውቅናን ያስገኘለት የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሁለተኛ አልበም የሆነው ‹‹አቡጊዳ›› የተሰኘው አልበም ነበር፡፡  ከተለመደው ወጣ ያሉት የሙዚቃ ቅንብሮቹም፣ አዲሱን ከያኒ ለማንገስና የተወዳጅነት ማማ ላይ ለመስቀል በእጅጉ አግዘውታል፡፡
ኤልያስ፤ በላቀና በረቀቀ ችሎታው፣ ሥራዎቻቸውን አቀናብሮ ለውጤት ካበቃቸው ድምፃውያን መካከል ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ትዕግስት በቀለ፣ ሃይሌ ሩት፣ ሚካኤል በላይነህ፣ አብነት አጎናፍር፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ይርዳው ጤናው፣ ፍቅረ አዲስ ነቃጥበብ፣ ጌቱ አንለይ፣ ሃይልዬ ታደሰ፣ ምናሉሽ ረታና ደረጀ ዱባለ ይጠቀሳሉ፡፡ ከውጤታማ የሙዚቃ ቅንብሮቹ ጎን ለጎን፣ ባለተሰጥኦዎችን በሙያው ገርቶና አርቆ፣ የራሱን የሙዚቃ ጀግኖች በመፍጠርም ይታወቃል - አርቲስቱ:: ለአብነት ያህልም ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ፣ ድምፃዊ እዮብ መኮንንና ድምፃዊት ሚኪያ በኃይሉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዝነኛዋና ተወዳጇ ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ቲያትር በተካሄደው የሽኝት ፕሮግራም ላይ ‹‹ኤልያስ ሕይወቱን ለሙዚቃ የሰጠና ራሱን መስዋዕት አድርጎ፣ ሺዎችን ያፈራ ድንቅ ባለሙያ ነበር›› ብላለች - በእንባ እየታጠበች፡፡
ኤልያስ ለበርካታ ድምጻውያን መነሻና መታወቂያ ምክንያታቸውም ነበር፡፡ ጀማሪ ድምጻውያንን እያበረታቱና እየደገፉ ለስኬት ማብቃት የዘወትር ተግባሩ ነው፡፡ ለሥራው የማይመጥን አነስተኛ ክፍያን እየተቀበለ፣ ብዙዎችን ለስኬትና ለዝና አብቅቷል:: በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚሰሩ ህብረ ዝማሬዎች ኤልያስ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡ ለዚህም ‹‹ማለበባስ ይቅር››፣ ‹‹መላ መላ በሉ››፣ ‹‹አሽከርክር ረጋ ብለህ›› የተሰኙት ህብረ ዝማሬዎች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ አንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ በተጫወተውና ከስኳር ህመም ጋር ተያይዞ በተሰራው ‹‹ስኳርን ታዘብኩት›› ህብረ ዝማሬ ውስጥም አሻራውን አሳርፏል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ምስረታን ምክንያት በማድረግ የተሰራውና ‹‹የአዲስ አስተሳሰብ ብስራት›› የተሰኘው ህብረ ዝማሬም ላይ ተሳትፏል፡፡  
ኤልያስ በ19 ዓመት የሙዚቃ ሕይወቱ ከ40 የሚበልጡ ሙሉ አልበሞችንና ከ400 በላይ ሙዚቃዎችን በማቀናበር፣ የማይደበዝዝ አሻራውን ለሙዚቃ አፍቃሪውና ለሚወዳት አገሩ ትቶ ያለፈ ድንቅ ባለሙያ ነው፡፡ ሁሉም በአንድ ቃል ከተስማማበትና ከተደነቀበት የሙዚቃ ቅንብር ችሎታው ባሻገር ሙዚቀኞች በየሙያቸው ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የሮያሊቲ ክፍያ እንዲፋጠን ከሙያ አጋሮቹ ጋር ሲታገልና ሲጥር የቆየው ኤልያስ፤ ልፋቱ ፍሬ ሊያፈራ ጫፍ ላይ በደረሰበት ወቅት ነው ሕይወቱ ያለፈው፡፡ የሙያ አጋሩ አንጋፋው አርቲስት ዳዊት ይፍሩም በስንብት መድረኩ ላይ ከሲቃ ጋር እየታገለ የተናገረው ይህንኑ እውነት ነበር፡፡ አብረውት የሰሩ ብዙ አርቲስቶችም፣ ‹‹ኤልያስ ለራሱ ሳይሆን እንደ ሻማ ቀልጦ ለእኛ ብርሃን የሰጠን መነሻ ምክንያታችን ነው›› ሲሉ ያወድሱታል፡፡
ድምፃዊት ጌቴ አንለይ፤ ‹‹እኔ ዛሬ  ያጣሁት ክንዴን ነው፤ ኤልያስ ለእኔ ምርኩዜና ድጋፌ ነበር›› በማለት ስሜቱን በሃዘን ገልጿል፡፡ ድምፃዊ ግርማ ተፈራ ደግሞ ‹‹ኤልያስ ከዕድሜው በላይ የሰራ ድንቅ ልጅ ነው፤ በእኔ ስራዎች ውስጥ ኤልያስ አለ፤ በእኔ ከፍታ ውስጥ ኤልያስ አለ፤ ለእኔ የዕድሜ ልክ ባለውለታዬ ነው፡፡ ዛሬ የአገራችን ሙዚቃ አንድ አብዮተኛ ነው ያጣው›› ብሏል፡፡
ሙሉ ሕይወቱን ለሙዚቃ ፍቅር አሳልፎ የሰጠ፣ በሕመም እየተሰቃየ ሙያውን አክብሮ ለሙያው ታምኖ የኖረ፤ በሙዚቃ ፍቅር መንኖና መንምኖ ሕይወቱን ያጣ፤ ዘመን የማይረሳው፣ ድንቅ የሙዚቃ አብዮተኛ ነበር - ኤልያስ መልካ:: ታላቁ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ እንዲሁም ፕሮዲዩሰር ኤልያስ መልካ፤ ባለፈው ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር የክብር ሽኝት ተደርጎለት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ተፈጽሟል፡፡ ነፍስ ይማር!


Read 2610 times