Saturday, 09 November 2019 11:28

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉትን ውይይት በጥር ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    የፊታችን አርብ የቴክኒክ ኮሚቴው በአዲስ አበባ ይሰበሰባል

              ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ የመጨረሻው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በወቅቱ መስማማት ካልቻሉ ወደ መርህ ስምምነት ሂደት በድጋሚ ይመለሳሉ ተብሏል፡፡
የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የውሃ ሚኒስትሮች፤ በዋሺንግተን የአሜሪካ የግምጃ ቤት ፀሐፊ ስቴቨን ሙኒቸንና የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ በታዛቢነት በተገኙበት በዋሺንግተን ባካሄዱት ውይይት፤ በግድቡ ላይ ያላቸውን ልዩነት በድጋሚ በውይይት ለመፍታት የተስማሙ ሲሆን፤ ላለፉት 6 ዓመታት ሲያደርጉት የነበረውን ውይይትም በጥር መጀመሪያ ላይ ለማጠናቀቅ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ሃገራቱ አራት ስብሰባዎችን በአዲስ አበባ፣ ካርቱምና ካይሮ የሚያደርጉ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ስብሰባም አርብ ህዳር 5 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ሀገራቱ በቀጠሮአቸው ቀን ውይይታቸውን አጠናቀው ስምምነት ላይ ካልደረሱ ደግሞ በድጋሚ ከ4 አመት በፊት ወደተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ተመልሰው እንደገና ውይይታቸውን ለመጀመርም ተስማምተዋል ተብሏል፡፡
ሀገራቱ በጥር ወር እንዲስማሙበት የሚፈለገው ነጥብ፣ በግድቡ የውሃ አሞላልና አስተዳደር ጉዳይ ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በዚህ ተስማምተው ድርድራቸውን በጊዜው ካልቋጩ፣ ከ4 አመት በፊት በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት፣ ሚኒስትሮቹ ጉዳዩን ወደየሀገራቱ መሪዎች ይመራሉ ወይም ደግሞ በሌላ ሶስተኛ ወገን እንዲዳኙ ይገደዳሉ ተብሏል፡፡ ከሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የተነጋገሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በሀገራቱ መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል::
ከውይይቱ ፍሬያማ ውጤት መገኘቱን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እስካሁን በግድቡ ግንባታ ላይ የቀየረችው አቋም እንደሌለ አስገንዝበዋል፡፡ ግድቡንም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅም ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ግድቡ ለኢትዮጵያ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም እንዲሁም ለሱዳንና ግብጽ የሚኖረውን በጎ አስተዋጽኦ በሚገባ ማስረዳታቸውን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ይሄን የተቋረጠው ውይይት ቀጥሎ ለአመታት ሲጓተት የቆየው ድርድር በወራት ውስጥ እንዲቋጭ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡
አሜሪካና የአለም ባንክ ሂደቱን በታዛቢነት ከመሳተፍ ውጪ የማሸማገል ሚና እንደሌላቸውና ይህ የታዛቢነት ሚናም በቀጣዮቹ ውይይቶች እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ አንድ የኡጋንዳ የደህንነት ባልደረባ፤ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ከግብጽ ጐን ቆመው በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ድብቅ ሴራ መካሄዱን አጋልጠዋል ሲል የደቡብ ሱዳኑ “ኒውስ ኤጀንሲ” ዘግቧል፡፡
ሶስቱ አገራት በዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ መንገዶች ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ማሴራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ግብጽ ግድቡ ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ የጦር ሠፈር እንደሚፈቅዱና ግብጽ በምትኩ ለሁለቱ ሀገራት መሪዎች በስልጣን መቆየት ድጋፍ ለማድረግ ማቀዷን አመልክቷል፡፡


Read 905 times