Saturday, 21 December 2019 11:55

የማንን ሃብት ማወቅ ይፈልጋሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

                 - የ200 ሺ ሰዎች የሃብት ዝርዝር መዝገቢያለሁ ይላል - ፀረ ሙስና ኮሚሽን
                 - የማንኛውም ባለሥልጣን የሃብት ብዛትን ለማወቅ ምን ያስፈልጋል?
                 - በአካል መቅረብ፣ ‹‹ምክንያታዊ ሆኖ መጠየቅ››

           ከፌዴራል እስከ ክልል፣ ከፕሬዚዳንትና ከጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ታች ሃላፊዎች ድረስ፣ የምክር ቤት አባላትንና የመንግሥት ሰራተኞችን… በአጠቃላይ የ200 ሺህ ሰዎችን የሃብት አይነትና ብዛት የሚዘረዝር የመረጃ መጋዘን - የብዙ መቶ ሚሊዮን መረጃዎች ጥንቅር ነው፡፡ ስም፣ ዕድሜ፣ የቤተሰብ ሁኔታና አድራሻ የመሳሰሉት ነገሮችን ጨምሮ የንብረት አይነትና ብዛትን ያካትታል፡፡ የተመዘገቡ መረጃዎችን አጠናቅሮ በቅጡ እንዳሰናዳ የገለፀው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የባለሥልጣናትን የሀብት መረጃ ለሕዝብ ከፍቻለሁ ብሏል፡፡
አላንዳች ምክንያት የሰዎችን ሀብትና የጓዳ ንብረት ለማወቅ እንኳን በተከፈተ በር በጭላንጭል አጮልቆ የማየት ሱስን ለማርካት የተዘጋጀ መረጃ አይደለም፡፡ ይልቅስ፣ ሰዎች በጥረታቸው ንብረት እንዲያፈሩ እንጅ፣ ስልጣንን ለስርቆትና ለጉቦ እንዳይጠቀሙ  ለመከላከል ያግዛል ተብሎ የተዘጋጀ መረጃ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ፣ የባለሥልጣናትና የበታች ሃላፊዎችን የሃብት መጠን ለማወቅ የፈለገ ሰው ምን ማሟላት አለበት? ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ ሌለ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ዜጎች ወደ ኮሚሽኑ በአካል በመቅረብ፣ ‹‹ምክንያታዊ ሆኖ በመጠየቅ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ›› የባለሥልጣናትን ሃብት መመልከት እንደሚቻል የኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ወደፊት፣ ለሁሉም ሕዝብ፣ በያለበት ተደራሽ ለማድረግ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ጥንቅር  እየተከናወነና እየተሰናዳ ነው ብለዋል - ዳይሬክተሩ፡፡ በኮሚሽኑ የተሰበሰበውና የተሰናዳው መረጃ፤ ሦስት የመንግሥት አካላትን ይመለከታል፡፡ 1ኛ፣ የሕዝብ ተመራጮች (የፌዴራል ፓርላማ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ተመራጮች)፣ 2ኛ፣ የፌዴራልና የክልል የመንግስት ተሿሚዎች፣ 3ኛ ደግሞ፣ ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣን ያላቸው የመንግስት ተቀጣሪዎች፣ አማካሪዎችና ሠራተኞች ላይ ያተኮረ ነው የኮሚሽኑ መረጃ፡፡
በዚህ መሠረት፣ ከ2 መቶ ሺህ በላይ ባለሥልጣናት፣ የምክር ቤት አባላትና የመንግስት ሰራተኞችም ሀብት ተመዝግቦ በኮሚሽኑ የመረጃ ቋት ውስጥ እንደሚገኝ አቶ መስፍን አስታውቀዋል፡፡

Read 11164 times