Saturday, 21 December 2019 12:00

ወደ ከፍታ መምጠቅ ለኢትዮጵያ የሚመጥን የነገ ታሪክ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

          - ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ገና ከጅምሩ፣ እንዲሁም ስልጣን ከያዙ በኋላ የሳተላይት ፕሮግራምና የህዋ ፕሮጀክት እንዲፋጠን አድርገዋል
          - የሕዋ ምርምርን የሚወዱ የፊዚክስ ምሁር፣ ወጣት ምሩቃንና አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ የህዋ ሳይንስ ማህበርን በመመስረት አስተዋጽኦ አበርክተዋል
          - ሼህ መሀመድ አልአሙዲ፣ በተለመደው ልግሳና፣ ለኢትዮጵያ የህዋ ተቋም 5 ሚሊዮን ዶላር በመስጠት ህይወት ዘርተውበታል
          - የሳውዲ መንግስት፣ በተሟላ ምህረት ነፃነታቸውን እንዲመልስላቸው፣ ጠ/ሚ ዐቢይ፣ በተለመደ ብልህነታቸው ቢጥሩ ለኢትዮጵያ ኩራት ነው

            72 ኪሎ ግራም ሳተላይት ለማምጠቅ 6 ሚሊዮን ዶላር፣ በአዲስ አበባ እንጦጦ ላይ የመከታተያና የመረጃ ጣቢያ ለማደራጀት 3.ሚ ዶላር፣ (በድምር 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ) ገንዘብ ወጥቷል። ቀላል ሀብት አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ እንደገፁት፣ የሳተላይት መረጃዎችን ለመግዛት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 350 ሚሊዮን ብር ትከፍላለች፡፡
ለህዋ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመደብ ገንዘብ፣ ሳተላይት ለማምጠቅ የሚውል ሀብት፣ በቀጥተኛ የኢኮኖሚ ስሌት ብቻ ቢታይ እንኳ፣ ያዋጣል፡፡ ጠቀሜታው ግን ከዚያም በላይ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡
ደረጃውና መጠኑ ይለያይ እንደሆነ እንጂ፣ ከህዋ ሳይንስ ውጭ፣ የሰው ልጅ ሕይወት እጅግ ጨለማ ነው፡፡ የሰዓትና የቀን፣ የወቅትና የዓመት ቆጠራ፣ በመቼ ወራት ቁር ወይም ሃሩር እንደሚሆን፣… የእርሻ ዝናባማ ወራትን፣ የአበባና የፍሬ ጊዜያትን፣ የአዝመራ ነፋሻማ ቀናትን አስቀድሞ መገመት፣ አድራሻንና የጉዞ አቅጣጫን መለየት… የሚቻለው ቀና ብለው ህዋን የሚቃኙ በሚመረምሩ፣ የፀሐይና የጨረቃ እንዲሁም የከዋክብት ሁኔታን እየተከታተሉ መረጃ የሚያደራጁ፣ በስሌትና በቀመር ጭምር ቅጥ ያለው እውቀትን በሚያዳብሩ ጠቢባን አማካኝነት ነው፡፡
ከሜስፓታሚያ እስከ ግብፅ፣ ከኢትዮጵያ እስከ አዝቴክ፣ ከዚያም እስከ ግሪክ ድረስ፣ ከህዋ ምርመርና እውቀት ተጠነጥሎ የተፈጠረ የጥንት ስልጣኔ የለም፡፡ ኢትዮጵያም ከጥቂት ከአለማችን የጥንታዊ ስልጣኔ ማዕከላት አንዷ እንደመሆኗ፣ በጥንታዊ የህዋ ሳይንስ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ጋር ስሟ ይነሳል፡፡  ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ የትኛውም የስልጣኔ ጉዞ፣ ሁሌም ከህዋ ሳይንስ ጋር የተቆራኘ ነው። ዛሬ ደግሞ ቁልፍ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚያ ላይ የደህንነትና የህልውና  ቁልፍ አለኝታና መሳሪያ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት፣ የኢትዮጵያ የሳተላይት ፕሮጀክት ትርጉሙ ሰፊ ነው፡፡ የእውቀትና የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ፍቅርን በህጻናት ዘንድ ለማስፋፋት ይረዳል፡፡ በህዋ መስክ፣ የኢትዮጵያን አቅም ያሳድጋል - 20 ወጣቶች በዚህ አጋጣሚ በህዋ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ የእውቀትና የክህሎት ብቃትን አግኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በብዙ ገፅታዋ ትልቅ አገር ናት፡፡ በህዋ ሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ከቀዳሚዎች የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ መሆን አለባት:: ለዚህም፣ የአሁኗ ሳተላይት መነሻ ትሆናለች ብለዋል - የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን፡፡
በ10 ዓመታት ለተለያየ አገልግሎት የሚጠቅሙ፣ በመጠናቸውም የገዘፉ 15 ሳተላይቶችን የማምጠቅ እቅድ እንዳለ አብራርተዋል፡፡
‹‹ETRSS - 1 ›› የተሰኘችው የኢትዮጵያ ሳተላይት፣ ለግብርናና ለደን ልማት፣ ለአየር ፀባይ ክትትልና ለማዕድን ጥናት ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘት እንደምታገለግልም ተናግረዋል፡፡
ሳተላይቷ ግብርናን በተሻለ ምርምር ለማዘመንና በጠንካራ መረጃ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንዳላት ገልፀው፣ በማዕድን ጥናት በኩልም መሬት ሳይቆፈርና ብዙ ወጪ ሳይወጣ የት ቦታ ምን ማዕድን አለ እንዳለ ለመለየት እንደምትጠቅም ዶ/ር ሰለሞን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት መረጃዎችን የምታገኘው እስከ 350 ሚሊዮን ብር በየአመቱ በመክፈል ነው፤ ሳተላይት ለማምጠቅ የሚወጣው ገንዘብ አዋጪ ይሆናል ብለዋል፡፡
ሳተላይት ለማምጠቅ አራት ዓመታት መፍጀቱ የተለፀ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ወደ ህዋ የሚላኩት የኮሚኒኬሽን፣ የብሮድካስቲንግና ተጨማሪ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ግን ይሄን ያህል ጊዜ እንደማይፈጁ ተገልጿል፡፡  

Read 12565 times