Saturday, 28 December 2019 13:00

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰራተኛ ማህበር ለመንግሥት የድረሱልን ጥሪ አቀረበ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

        “የአየር መንገዱ አስተዳደር ኢሰብአዊ ድርጊቶችንና የመብት ጥሰቶችን ይፈጽምብናል”
              የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰራተኛ ማህበር፤ “አየር መንገዱ በማህበሩ አባላትና ሰራተኞች ላይ እየፈፀመ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ተግባርና ዓይን ያወጣ የመብት ጥሰት መንግስት ሊያስቆምልን ይገባል” አለ፡፡
መንግስት በአየር መንገዱ ዋና የሥራ ኃላፊዎች የሚፈፀምብንን ዛቻና ማስፈራራት ሊያስታግስልንና በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ የመደራጀት መብታችንን ሊያስከብርልን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የአየር መንገዱ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ከ4900 በላይ አባላት እንዳሉት የገለፀውና ከነባሩ ማህበር ተገንጥሎ የተቋቋመው አዲሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰራተኛ ማህበር የሥራ አመራር አባላት ከትናንት በስቲያ በጁፒተር ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአየር መንገዱ አስተዳደርና የበላይ አመራሮች የሰራተኛውን በህጋዊ መንገድ የመደራጀት መብት በመጣስ፣ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት እየፈፀሙብንና በደል እያደረሱብን ነው ብለዋል፡፡
የማህበሩ ሊቀ መንበር ካፒቴን የሺዋስ ፋንታሁን በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኤርፖርቶች ድርጅት በተዋሃዱበት ወቅት በሁለቱ ተቋማት ውስጥ የነበሩ የሰራተኛ ማህበራትን ወደ አንድ ለማምጣት ውይይት ሲደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በሂደቱም ይህ ማህበር ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ተደርጓል ብለዋል፡፡ ማህበሩ እውቅናን ካገኘና ከ4900 በላይ አባላትን ከመዘገበ በኋላ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በአየር መንገዱ የበላይ አመራሮች በበጎ እንደማይታይና የማህበሩ አባላት የሚያደርጉትን ማንኛውንም ስብሰባና የመብት ጥያቄ ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ከቀድሞ የሰራተኛ ማህበር ጋር ምንም አይነት ቅራኔም ሆነ እሰጣ አገባ የለንም ያሉት ካፒቴን የሺዋስ፤ ማህበሩ ግን የሰራተኛውን መብት በአግባቡ ለማስከበር ይችላል የሚል እምነት ስለአጣንበት የሰራተኛውን መብት በትክክል የሚያስከብርና ለሰራተኛው መብት የቆመ ማህበር ሆኖ እንዲቀጥል አድርገናል ብለዋል፡፡
ሊቀ መንበሩ በሰራተኛው ላይ በአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ይፈፀማል ካሉት የመብት ጥሰቶችና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት መካከል፡- ዛቻና ማስፈራራት፣ ከስራ ማገድ፣ ማባረር፣ የስራ ቦታ ለውጥ ማድረግና የስራ ልምድ መከልከል የሚሉትን ጠቅሰዋል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲሱ የሰራተኛ ማህበር ከፍተኛ እገዛና ድጋፍ ሲያደርግልን የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት የተቀዛቀዘ መሆኑ በጣም አሳስቦናል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ለጻፍናቸው አምስት ደብዳቤዎች ምላሽ ተነፍጎናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም አቀፍ ደረጃ ላገኘው ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተቀባይነት የሰራተኛው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው ያሉት የማህበሩ ሊቀ መንበር ካፒቴን የሺዋስ ፋንታሁን፤ ለዚህ ደረጃ ያበቃውን ሰራተኛ የሚያዝበትና የሚያስተዳድርበት መንገድ ግን እጅግ የሚያሳዝን ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ አየር መንገዱ በሕዝብና በመንግስት ከፍ ያለ ክብርና ቦታ የሚሰጠው ቢሆንም በከፍተኛ አስተዳደሩ ሲፈፀሙ የኖሩት ሕገወጥ ተግባራት ለብዙ ዘመን ከሕዝብና ከመንግስት እይታ ውጪ ሆኖ ኖሯል ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ የማህበሩ አመራሮች ሰራተኛው ያሉበትን ችግሮች ከአየር መንገዱ አመራሮች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥሪ ብናቀርብም፣ ከፍተኛ አመራሮቹ ለሰራተኛው ባላቸው ንቀትና ማን አለብኝነት ምክንያት ጥረታችን ከንቱ ቀርቷል ይላሉ፡፡ ሰራተኛው እጅግ ተራ በሆኑ ጉዳዮች ከሥራው ይታገዳል፣ ያለአግባብም እንዲሰናበት ይደረጋል ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ በቴሌግራም መልዕክት ጽፏል ተብሎ ከስራው የተባረረ የአየር መንገዱ ሰራተኛ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ መንግስት በሰራተኛው ላይ እየደረሰ ያለውን ሕገወጥ ተግባር በቅርበት በማየት ለከፋ ችግርና ጉዳት ከመጋለጣችን በፊት ይድረሱልን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በማህበሩ ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/እግዚአብሔር በሞባይል አጭር የጽሑፍ መልዕክት ጥያቄያችንን ብናቀርብም ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ ምላሽ አላገኘንም፡፡ የአየር መንገዱ የሥራ አመራሮች በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡    


Read 1094 times