Saturday, 20 June 2020 11:12

የትግራይ ክልላዊ መንግስት ለማካሄድ ባቀደው ምርጫ አረና እና አሲምባ ለመሳተፍ አቅደዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    በምርጫው ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል

             የትግራይ ክልላዊ መንግስት ለማካሄድ ባቀደው ምርጫ አረና እና የአሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉላቸው እንደሚሳተፉ ያስታወቁ ሲሆን ባይቶናና ሳልሳይ ወያኔ ከህወኃት ጋር ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል፡፡
የትግራይ ክልላዊ ም/ቤት በነሐሴ 2012 ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ፣ አረና ምርጫው ይሳተፍ እንደሆነ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል::
ምርጫው በህጋዊና ገለልተኝነቱ ተቀባይነት ባገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዳኝነትና አስፈፃሚነት የሚከናወን ከሆነ፣ አረና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚሳተፍ ሊቀመንበሩ ገልፀዋል፡፡
ምርጫው ያለ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናና አስፈፃሚነት የሚካሄድ ከሆነ ግን ፓርቲያቸው በምርጫው ይሳተፍ አይሳተፍ የሚለውን ጉዳይ በማዕከላዊ ም/ቤት ተሰብስቦ እንደሚወስን በዚህ ስብሰባም ያለ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የሚካሄደው ምርጫ አስፈላጊነትን፣ ህጋዊነትን፣ ፍትሐዊነትንና ትክክለኛነትን እንደሚመረምር አስረድተዋል - አቶ አብርሃ፡፡  ፓርቲው ያለ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የሚያካሄደው ክልላዊ ምርጫ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝግጅቱ ተጠናቆ ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? የሚቋቋመው ክልላዊ ምርጫ አስፈፃሚ ገለልተኛነቱ ምን ያህል ነው? እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ? የሚሉትን ሁሉ ይፈትሻል ብለዋል - ሊቀመንበሩ፡፡
“አረና በየትኛውም መንገድ በኢትዮጵያ ሀገራችን አንድነት ላይ አይደራደርም” ያሉት አቶ አብርሃ፤ “ምርጫ የሚካሄደው ትግራይ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ሆና ነው ወይስ ተገንጥላ ነው የሚሉ ጥያቄዎችም በሚገባ እንገመግማለን” ብለዋል፡፡
የተዘረዘሩትን ጥያቄዎችና ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ የሚገኝ ምርጫ ከሆነም ፓርቲው ሊሳተፍ እንደሚችል ጠቁመዋል ሊቀመንበሩ፡፡
ከተመሠረተ አንድ አመት ያስቆጠረው አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ ምርጫው በብሔራዊ  ምርጫ ቦርድ አስፈፃሚነት የሚከናወን ከሆነ በቀጥታ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡
በክልል ደረጃ በሚቋቋም የምርጫ አስፈፃሚ የሚካሄድ ከሆነም ገለልተኝነቱንና ፍትሃዊነቱን ገምግሞ በምርጫው እንደሚሳተፍ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ባይቶና እና ሳልይ ወያኔ ቀደም ብሎ ህወኃት በምርጫ ጉዳይ የያዘውን አቋም ሲደግፉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡



Read 1860 times